አራቱስ እንዴት?

0
468

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባሳለፍነው ሳምንት ዕትሙ በአገራችን ከሚገኙ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰሩ 193 ፕሮፌሰሮች መካከል ሴቶቹ አራት ብቻ መሆናቸውን፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን ጠቅሶ ገልጿል። “አራት ብቻ” በጣት የሚቆጠሩ ብሎ ለመግለጽ እንኳን የሚያስቸግር ቁጥር ነው።

የሴቶች ቁጥር የማነሱ ምክንያትም የሚሰጠው ድጋፍ አናሳነት እንዲሁም የሴቶቹ ወደ ጥናትና ምርምር የማዘንበሉ ልምድ አነስተኛ መሆን እንደሆነም በዜናው ተካትቷል። እንግዲህ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተዘልቆና ሦስተኛ ዲግሪ ተሠርቶም ድጋፍ ያስፈልጋል ማለት ነው?

መቼስ ይሁን! በአዳጊ አገር ላይ በመሆናችን የሴቶች እኩልነት ስላልተከበረ ነው በሉኝ። በዛም መሰረት ከሆነ በፕሮፌሰርነት ደረጃ በቁጥር ከአንድ ወደ አራት ከፍ መባሉ ቀላል አይደለም። እንደውም በዜናው እንደቀረበው ከሆነ በአሁኑ ወቅት 277 ሴቶች በመሪ ተመራማሪነት ደረጃ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየሠሩ ይገኛሉ። እናም በምርምር እንዲሳተፉ ልዩ ሥልጠና እና ድጋፍ እየተሰጣቸው ነው መባሉም ጥሩ ይሆናል።

ታድያ ፕሮፌሰር ለመሆን ለወንዱ ቀላል ሆኖ ለሴቶች ሥልጠና እና ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን ስመለከት፤ አራቱ ሴቶችስ እንዴት ፕሮፌሰር ሆኑ ስል አሰብኩ። በዘመድ ነው? አይ! በልዩ ድጋፍ? ሥልጠና አግኝተው? ነው ወይስ ቅድሚያ እየተሰጣቸው? እሺ በቃ እንደው ሴት ስለሆኑ ብቻ?

አይመስለኝም። በጀመሩት መንገድ ሊደርሱበት ከሚችሉት ጥግ ድረስ መራመድ በመቻላቸው ነው። በትምህርትና በምርምር ዓለም ራስን በሥራ መግለጥ፣ መመራመርና መጣር ያስፈልጋል። በጥቅሉ የሴት ፕሮፌሰሮች ቁጥር ለማነሱ ምክንያት በሴቶች እኩልነት ላይ ምንም አለመሠራቱ ሳይሆን ሴቶች ራሱ በሚገባ ያለመሥራታቸው ነው ባይ ነኝ።

ለምን በሉኝ፤ ሦስተኛ ዲግሪ መያዝ የቻሉ ሰዎች እየገፉ በሔዱ ቁጥር ያለውን ድካምና ፈተና ስለሚያውቁት፤ ዳገቱ እንደመጀመሪያው ከባድ አይሆንባቸውም ብዬ ስለማምን። በእርግጥ የሴቶቹ ብዛት ይቅርና 193 ፕሮፌሰር በአገር ደረጃ አለ ብሎ መኩራትም አይቻልም። ይሁንና ግን ያም ደረጃ ቢሆን በጥረትና በትጋት እንጂ በዕድል የሚገኝ አይደለም።

እንግዲያው እነዚህ አራት ሴቶች ብርቱ በመሆናቸው ከደረሱበት ደርሰዋል። የእነዚህም ሴቶች ስኬት ማድመቅ ሌሎችም ወደ ደረጃው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረብ ነውና ትኩረት መደረግ ያለበት እዛ ላይ ነው። እውነተኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ብዙ እህቶች ባሉባት አገር፤ የተማራችሁና በመንገዳችሁ ለስኬት የቀረባችሁ ሴቶች ሆይ! ራሳችሁን ደግፋችሁ ከፍ በሉ። በሸመታችሁት እውቀትና ትምህርት አርአያነታችሁና ድጋፋችሁ ለብዙ እህቶቻችን እንደሚያስፈልጋቸው አትዘንጉ። “አልተደረገልንም!” ብለን አሻግረን ስንጠቁም፤ የቀሩት ሦስት ጣቶች “እናንተስ ምን አደረጋችሁ!” እያሉን ነው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here