201 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የታሸጉ ምግቦች ተወገዱ

0
820
  • በዐሥራ አንድ የምግብ አምራቾች ላይ ጊዜያዊ እገዳ ተጥሏል

ባለፉት ስምንት ወራት 2 ሺሕ 389 ቶን ምግቦች የተበላሹና ጥራታቸውን ያልጠበቁ ሆነው በመገኘታቸው እንዲወገዱ መደረጉን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

የተበላሹና ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉት ምግቦች ውስጥ ዘይት፣ ዱቄት፣ ወተት፣ ሩዝ፣ ጁስ እና የተለያዩ የፍራፍሬና የምግብ ጥሬ ዕቃ ሲሆኑ እነዚህም የተበላሹ ምግቦች በአጠቃላይ 201 ሚሊየን 725 ብር እንደሚገመቱ ተናግረዋል።

ሩዝና አኩሪ አተር በነቀዝ ከመበላታቸው ባሻገር 686.8 ሊትር ዘይት በጉዞ ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት እንዲሁም፣ 4 ሺሕ 950 ኪ.ግ የምግብ ጥሬ ዕቃ፣ ከውጪ አገር የመጣና እና የአምራች ካምፓኒው የማይታወቀው 180 ሜ.ቶን እና 2056 ቶን ዱቄት በጉዞ ወቅት በመበላሸታቸው እና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው በመቃረቡ ምክንያት በአገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጉን የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አበራ ደነቀ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በኹለት የምግብ አስመጪና አከፋፋይዮች ላይ አስከ ሦስት ወር የሚደርስ እገዳ፣ አንድ አስመጪ ላይ የብቃት ማረጋገጫ በድጋሜ እንዲያስተካክል የተወሰነ ሲሆን ለኹለት አከፋፋዮች የጽሑፍ ማስጠንቀቅያ እንደደረሳቸው አሳውቀዋል።

በተያያዘም በዐሥራ አንድ የምግብ አምራቾች ላይ ጊዜያዊ እገዳ፣ በ7 ቀላልና ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቅያ እንዲሁም በአንድ የምግብ አምራች ላይ የብቃት ማረጋገጫው የተሰነረዘበት ሲሆን፣ በተጨማሪም መሥፈርቱን ሳያሟሉ እንዲሁም፣ በኦዲቲንግ ኢንስፔክሽን ወቅት ችግር ያለበትና ሕግ ወጥ መሆናቸው የተረጋገጡ 22 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ መድኀኒቶች ጥቅም ላይ እንዳይውሉና በአግባቡ እንዲወገዱ ተደርጓል።

አወጋገዳቸውም በኹለት መንገድ ሲሆን፥ ምግቦቹ ወይም መድኀኒቶች በሚወገዱበት ጊዜ ኅብረተሰቡ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ከሆነ ወደ መጡበት አገር እንዲመለሱ ሲደረግ፣ ማኅበረሰቡ ላይ ጉዳት የማያደርሱ ከሆነ በመቃጠል የሚወገዱ ይሆናል።

በዚህም ዙርያ የኢትዮጵያ ምግብና መድኀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕገ ወጥ አቅርቦት ለመከላከል ከፌደራል ፖሊስ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካለት ጋር በመሆን ሕገ ወጥ ምግብና መድኀኒቶች በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ተለይተው እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየሠራ ሲሆን መግቢያና መውጪያ ኬላዎች ላይ ምርቶችን ለማጣራት ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ መሥሪያ ቤቱ ገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here