በ“ዘር” እና በ“ብሔራዊ ማንነት” መካከል

0
656

በአገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው በዘር ወይም በብሔርና በማንነት የማመን ጎራ መነሻ በማድረግ፥ ቤተልሔም ነጋሽ ኹለት የመንግሥት አወቃቀሮችን በማነጻጸር ምናልባት አስታራቂ ሊሆን የሚችል ሐሳብ ለማምጣት የሚቻልበትስ ሁኔታ አለ ሲሉ ይጠይቃሉ።

 

 

“የሰው ልጅ አመክንዮ ስህተት ሊሆን መቻሉና አመክንዮን የመጠቀም ነፃነቱ እስከቀጠለ ድረስ የሐሳብ ልዩነት መኖሩም ይቀጥላል።”

ጀምስ ማዲሰን
“ስለ መሪነት ካሉኝ እምነቶች አንዱ ይህ ነው፤ መሪነት ስለተከታይ ብዛት አይደለም፤ የተለያየ ሐሳብ ያላቸው ምን ያህል ሰዎች አሰባስበህ በጥሞና መስማት ስለመቻል እንጂ”

ሮበርት ክራፍት
ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ ሲባል ብሔራዊ ማንነት በሚል የተገለፀው በአኀዳዊ ሥርዓት ወይም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ጎልቶ ይውጣ በሚለው የአንድነት አቀንቃኝ አስተሳሰብን ለመግለጽ ጥቅም ላይ መዋሉን ለማስገነዘብ እወዳለሁ።

የኢትዮጵያ ብሔር ተኮር ወይም ማንነትን መሠረት ያደረገ የፌደራሊዝም አወቃቀርና ችግሮቹ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከአካዳሚክ ማኅበረሰብ እስከ ጋዜጠኛና የተማረ ተራ ዜጋ ብዙ ከሚልባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ መሆኑን አንስተውም።

ሐሳብን ከመግለጽ አንስቶ መልካም ጎን አለው ወይ የሚለው ጥያቄ እስኪሆን ድረስ ፈፅሞ አያስፈልግም ከሚል አንስቶ በሌላው አገር ያልተለመደና የማይሠራ ሥርዓት መሆኑን እየገለፀ እስከሚተች ድረስ ምናልባት ከፍተኛ ተቃውሞ የሚያስተናግድ ጉዳይ ነው ለማለትም ይቻላል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ የፌደራል ሥርዓቱን ችግሮች በሚመለከት መዘርዘርና ሐሳብ መስጠት ሳይሆን ይልቁንም እየጨመረ በመጣው በዘር ወይም በብሔርና በማንነት የማመን ጎራ እና በአኀዳዊና በብሔራዊ ማንነት ወይም በማዕከላዊ አገዛዝና በአገር የሚወከል ማንነት የሚሉት ኹለት ጽንፍ የያዙና የማይታረቁ የሚመስሉ ሐሳቦች ላይ በኹለቱም ወገኖች የሚባሉትን ጥቂት ሐሳቦች አቅርቦ የፖለቲካ ሥርዓቶቹን በሚመለከት አንዳቸው ብቻ ልክ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚ መኖር አለመኖሩን ለመጥቀስ እንዲሁም ምናልባት አስታራቂ ሊሆን የሚችል ሐሳብ ለማምጣት የሚቻልበትስ ሁኔታ አለ የሚለው ላይ ጥቂት ለማለት ነው።

ክንፈ ኪሩቢል የተባሉ ፀሐፊ ለምሳሌ በሚያዝያ 2010 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “የኢትዮጲያ ፌደራሊዝም አወቃቀርና ችግሮቹ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጽሁፍ የፌደራሊዝሙ ችግሮች ያሏቸውን እንዲህ ዘርዝረዋል፡
“በዛሬው የፌዴራል ዘጠኝ የክልሎች አወቃቀር መሠረተ ሰፊ የመሬት ስፋትና ሕዝብ ካላቸው እንደ ደቡብ ሕዝቦች ዋና ከተማ ሐዋሳ፣ የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር፣ የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅግጅጋ፣ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ፊንፊኔ የመሳሰሉት ልማቶቻቸው በዋና ከተሞቻቸው ላይ ያተኮረ በመሆኑ፣ የገጠሩ ሕዝብ ፍልሰት ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ወደ ከተሞቹ ይታያል። ከተሞቹ በሥራ ፈላጊ ሕዝብ ተጨናንቀዋል። የመሬት ወረራ በሕገ ወጥ መንገድ ተበራክቷል። በማኅበራዊ አገልግሎት ተደራሽነት በመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት፣ በትራንስፖርት፣ ወዘተ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል። እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ በሽታዎች እየጨመሩ መጥተዋል። ወንጀል እየተበራከተ ነው። የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና የጫት ተጠቀሚነት ከ50 በመቶ በላይ ወጣቱን ሰለባ አድርገውታል። ኢትዮጵያን ተረካቢ ትውልድ የሚያሳጣ ድርጊት ሲከናወን መንግሥታችን ዝም ብሎ ማየቱ እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢ ሁኔታ ሆኗል።”

“ይህ ቋንቋን መሠረት አድርጎ የተዋቀረ የክልል መንግሥታት የአስተዳደር መቀመጫ ዋና ከተሞች ከሰፊው ሕዝባቸው አሰፋፈር እጅግ የራቁ በመሆናቸው ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ለኢኮኖሚያዊ ልማቶች ቁጥጥር፣ ለፍትሕና ለማኅበራዊ አገልግሎቶች መዳረስ ያልተመቹ ሲሆኑ፣ በዋና ከተሞቹና በዞኖቹ መካከል ያሉት የአስተዳደር የግንኙነት ሰንሰለቶች የሳሱ ናቸው። ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የቀድሞ ዋና ከተሞች እንደ ነቀምት፣ መቱ፣ ጅማ፣ አሰላና ባሌ ጎባ የመሳሰሉት ዛሬ ወደ ዞን ከተማነት ወርደዋል። እነዚህ ከተሞች እንደ ዋና ከተማነታቸው ቢቀጥሉ ልማቱን በአካባቢያቸው በማፋጠን፣ የሥራ ዕድሎችን ለወጣቶቻቸው በቅርብ በመፍጠር ወደ ክልል ከተሞች የሚታየውን የሕዝብ ፍልሰት መግታት በቻሉ ነበር” ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር የነበሩት እና በወቅቱ በሰላም ደኅንነት የዶክትሬት ተማሪ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኀይል ዋና አዛዥ፣ ሜጀር ጀነራል አበበ ተክለ ሃይማኖት በበኩላችን በአገራችን ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረውን ግጭት አስመልክቶ በወቅቱ ለመገናኛ ብዙኀን ሰጥተውት በነበረው ቃለ ምልልስ ፌደራል ስርዓቱንና ያስከተላቸውን ችግሮች በሚመለከት ተጠይቀው እንዲህ ብለው ነበር።

“የፌደራል ስርዓት ካለ ዲሞክራሲ የሚመራ አይደለም። ማዕከሉ ዲሞክራሲ ነው። ዲሞክራሲ ደግሞ የግለሰብ መብትና የቡድን መብት ነው። የፌደራል ስርዓት ሲሆን ደግሞ መሰረቱ፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የጋራ አስተዳደር ነው። ይህን ኹለቱን የሚያያይዘው ደግሞ ዲሞክራሲ ነው። ዲሞክራሲው ችግር ሲኖርበት፣ ፌደራሊዝሙ ችግር ይኖርበታል። ስለዚህ የፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር ሳይሆን ዋናው ችግሩ የዲሞክራሲ እጥረት ነው። በእርግጥ ሙሉ ለሙሉ የተሟላ የፌደራል ስርዓት በዓለም ላይ የለም። ሕገ መንግሥቱ ወይም ፌደራል ስርዓቱና ፖለቲካው ተጣጥመው አብረው መሔድ ከጀመሩ በእኔ አመለካከት፣ የኢትዮጵያ አንድነት የበለጠ እየተጠናከረ ይሔዳል። ምክንያቱም ማናቸውም ብሔርና ብሔረሰብ ሊጠቀሙ የሚችሉት እኩልነትን ማዕከል ካደረገው የኢትዮጵያ አንድነት ነው። አንድነቱ ልዩነቱንም ማስተናገድ ሲችል፣ ኢትዮጵያዊ አንድነቱ የበለጠ ሊጠነክር ይችላል። ግን ፖለቲካው ላይ በዋናነት የዲሞክራሲ እጥረት ስላለ ስርዓቱ በከፍተኛ ውጥረት ላይ ይገኛል ማለት ይቻላል።”

በግሌ ሐሳባቸው ይስማማኛል። በዲሞክራሲ ምዕተ ዓመታትን ያስቆጠሩ አገሮች ይበጀናል ያሉትን የፖለቲካ ስርዓት ሕዝብ አምኖበት ተወያይቶበት ይቀጥል አይቀጥል በሚል በየጊዜው ሐሳብ እየተሰጠበት በሚቀጥልበት ሁኔታ እንኳን አንድ አሠራር እንከን አልባ ሊሆን አይችልም። ጂኦግራፊያዊም ይሆን ዘርና ቋንቋ ተኮር ፌደራሊዝም አልያም አኀዳዊ ሥርዓት ለሕዝቡ ሙሉ በሙሉ መልስ ሊሰጥ አይችልም። ከላይ በመግቢያዬ የተቀመጠው ጥቅስ እንደሚለው የሐሳብ ልዩነት ዲሞክራሲ እስካለና ያንን ሐሳብ መግለጽ እስከተፈቀደ ድረስ ይኖራልና አሠራርና ስርዓቱን መቃወምም እንዲሁ።

ነገር ግን በተለይ በአሁኑ ወቅት በአንፃራዊ መልኩ በአገራችን ሐሳብን በነፃነት መግለጽ በመጀመሩ ድሮም በተለያየ መልኩ በተለይ በዳያስፖራ ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከልና በወቅቱ የነበሩ የስርዓቱ ደጋፊዎችና ሌሎች ክልልና ራስን ማስተዳደር ይበጀናል የሚሉ ኢትዮጲያውያን መካከል የነበረው መካረር ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አንዳንዱ ደፍሮ የብሔር መጠሪያ ሥም እየጠራ “እገሌ እገሌ የሚባል ሰው የለም” ብሎ በድፍረት ይናገራል ደጋፊዎቹም የብሔር ወይም “ዘር ተኮር ፖለቲካ ይታገድልን” ሲሉ ይሰማል፤ የፌደራል ስርዓቱ ፈርሶ አንዲት ኢትዮጵያ ትኹንልን ይላሉ። ሌሎች ለብቻችን በቋንቋችን ተከልለን እንኑር፣ ከሌሎች አንጋባ “አንቀየጥ” በራሳችን ተወስነን እንኑር ይላሉ እኔ ኢትዮጵያዊ ከመሆኔ በፊት የእንቶኔ ዘር ነኝ፣ የጠራሁ እንትን የእግዜር አምሳያ ይላሉ። አንዱ ሌላውን ጎራ ዓይንህን ላፈር ይላል አመክንዮውንም ለመስማት የእሱን እውነት ለማየት ዝግጁ አይደለም። የሐሳብ ብዝኀነት፣ ሌላውን መስማት እዚህ ጋር የሚሠራ አይመስልም። ይህ ቀርቶ አንዱ ሌላውን የሚቃወምበት ጥንካሬ ዕድሉን ቢያገኝ ሐሳቡን ጭኖ በእሱ ሥር አዳሪ ሊያደርገው ይችላል የሚያስብል ነው። የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳው በኹለቱም ጎራ ያለው አስተሳሰብና ታሪክ የኖረ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለያ ጊዜያት የተከሰተ ነው።

ለምሳሌ
“በእናታችሁ ብሔሬን አትጠይቁኝ። አማራ ኦሮሞ ትግሬ … ምናምን ነህ ወይ እያላችሁ አታደንቁሩኝ ሲሆን ከምድር የሚያልፍ ሐሳብ እንዲኖረኝ ነው የምሻው። ያ ካልሆነ ደግሞ ሰውነት ብሔሬ ነው፤ ሠፈሬ ደግሞ ኢትዮጵያ ነች። ከዚህ የሚጠብ ማንነት ግን ፈጽሞ እንዲኖረኝ አልፈልግም” ይላል ስላላስፈቀድኩ ሥሙን መግለጽ የማልችለው ሰው የማኅበራዊ ሚዲያ ጽሁፍ።
ነገር ግን ብሔሬ ተጠርቶ፣ በዛ ተለይቼ ልጠራ አስተዳደርና ግዛቴ እንዲያ ይሁን ለሚለውስ ምናልባት በአግባቡ የተካሔደ ሕዝበ ውሳኔ ብናደርግ የትኛው ጎራ ይሻል ይሆን። በሕግ ስለተከለከለ በዘርና በቋንቋ መደራጀት ይቀራል። ግጭትስ ይጠፋል?
የወቅቱ የኢትዮጵያ ውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታዎች አንዱን ይዞ አንዱን ጥሎ፣ ሌላውን አዝሎ ወደ ፊት ለመራመድ አይፈቅዱም። ሁኔታውም የሚያመለክተው የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች ከኹለት አማራጮች ፊት እንደ ቆሙ ነው።

ደርግና አፄ ኃይለ ሥላሴ አኀዳዊ መንግሥታት ነበሩ ፀረ ዲሞክራሲያዊና አፋኝ ጨቋኝም ነበሩ። እንግሊዝን በምሳሌ ብናይ ብዙ ሥርዓቶች በአንዴ መጥተው ዲሞክራሲያው ሥርዓት የመሰረቱበት የፖለቲካ ሥርዓት መሆኑን እንረዳለን።
ምሁራን የራሳቸውን አስተሳሰብ የበላይነት ማረጋገጥና እኔነትን ትተው ቀናነት በተመላበት መንገድ ተወያይተው፥ ሕዝቡንም አሳትፈው የተሻለው መንገድ የቱ ነው የሚለውን የማሳየት ኃላፊነት አለባቸው።

ይልቁንም ከላይ የተጫነ የመሰለው ሕዝብን ያላሳተፈ ፌደራሊዝም ለብዙ ዓመታት ሕዝብ ሳይወያይ ከፈረሱ ጋሪው ቀድሞ ምርጫ የለህም የተባለበት አሠራር ሊፈተሸ፣ መነሳት ካለበት ሊነሳ ጊዜው አሁን ነው። ተሻሽሎ ለሕዝብ እንዲሆን የሚደረግበት አሠራር ካለ በጥናት የተደገፈ መፍትሔ ቀምሮ መሔድ ግድ ይላል። ምናልባት ዲሞክራሲ ማስፈን የፌደራል ስርዓቱን የተሻለ ማድረግ ይችል እንደሆነ ወይም አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ችግሩ ንድፈ ሐሳባዊን (ʻቲዮሪʼውን) በአግባቡ መተግበር አለመቻል ከሆነ ይህ ሊታይ ይገባል። እንደሚገባኝ የፌደራሊዝሙ መሠረት የሆነውን ሕገ መንግሥት እንዲህ በቀላሉ ማሻሻል አልያም ቁጥሩን በውል በማናውቀው የዘርና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ ደጋፊ ሐሳብ ትቶ ወደ አኀዳዊ እንዲመጣ ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም። ከኹለቱ አንዱ የሚበጀን ለውጥ እስኪመጣ ያለውን ጊዜ ግን ዘር ይሻላል ብሔራዊ ማንነት የሚለው ክርክር አንዱ ሌላውን ወደ ማሳመን እንኳን ባይሆን ተቀራርቦ ለመረዳትና ለመግባባት ቢቻል አማካይ መፍትሔ ለማምጣት ብንጠቀምበት እናተርፋለን።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here