በጉሙዝ በብሔር ግጭት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ17 መብለጡ ታወቀ

0
526
  • በበቀል እርምጃ በጃዊ ወረዳ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል

በሳምንቱ መጀመሪያ በምዕራብ ኢትዮጵያ በአማራና በጉሙዝ ብሔረሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት ከ17 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸዉ የአማራ ክልላዊ መንግስት ገለፀ። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸዉ የክልሉ ቃል- አቀባይ አሰማኸኝ አስረስ በምዕራብ ኢትዮጵያ በሁለቱ ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰዉ ግጭት የጀመረዉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳንዱር በተባለ የገጠር መንደር አንድ ነዋሪ ከተገደለ በኋላ ነበር ብለዋል።

ከግድያዉ በኋላ ነገሩ ወደ ብሄር ግጭት ማምራቱን የተናገሩት አሰማኸኝ ግለሠቦች በቀስት (ጦር) እና በጦር መሳርያ ለቀናቶች ጥቃቶች ሲሰነዘሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። ግጭት የፈጠሩት ቡድኖች በየፈርጃቸዉ የመኖርያ ቤቶችንም አቃጥለዋል ተብሎአል። በአሁኑ ወቅት ቦታዉ ላይ ያለዉ ዉጥረት ግጭቱ በተነሳበት አካባቢ መብረዱን እና የጥናት ስራዎች እየተሰሩ ነው ቢሉም ከአካባባው እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግጭቶቹ በአዳዲስ ቦታዎች አገርሽተዋል፡፡

የተባባሰውን ግጭት ተከትሎም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ሰራዊት በብዛት ገብቶ በአካባቢው መግባቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰዎችን ህይወት የቀጠፈው ግጭት የተቀሰቀሰው በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ አይሲካ ቀበሌ በሚያዝያ 18/2011 ነበር። በቀበሌው ባሉ እቃ ወደመኪና በጫን እና በማውረድ በሚተዳደሩ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ወደ ብሔር ግጭት መቀየሩን እና የሰው ህይወት ማለፉንም የክልሉ መንግስት አስታውቋል። ግጭቱ አንዴ እየቆመና እያገረሸ ባልታሰበ ሰዓት ጥቃት እየተፈጸመ ለበርካታ ንጹሐን ዜጎች እልቂት ምክንያት መሆኑንም አሰማኸኝ አስታውቀዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አዲጎ አምሳያ በጥቃቱ የሞቱ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ማጣራት እያደረጉ እንደሆነ ቢገልጹም የአማራ ክልል ቃል አቃባይ አሰማኸኝ አስረስ ግን በግጭቱ ከ17 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል። ከግጭቱ በኋላ ሁኔታውን ለማጣራት የአማራ ክልል ልዑክ ወደስፍራው አቅንቷል፡፡ ልዑኩ በአካባቢው የተፈጠረውን ቀውስ መርምሮ ሲያበቃ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ አሰማኸኝ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል፡፡

ከግጭቱ በኋላ የኢትዮጵያዉን በየትኛዉም የሐገሪቱ ክፍል በሰላም የመኖር መብታቸዉ ሊጠበቅ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚንስር ደመቀ መኮንን አሳስበዋል። ደመቀ በአማራ ክክል በየጊዜዉ የሚከሰተዉን አለመረጋጋት ለማስቆም ባሕርዳር ዉስጥ በተደረገ ዉይይት ላይ ከተካፈሉ በኋላ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት የተጀመረዉ ለዉጥ እንዲቀጥል ከተፈለገ ዜጎች በሁሉም ቦታ ሰላማቸው ሊጠበቅ ይገባል። ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈጠረውን ግጭት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ተጨማሪ ጦር ኃይል ወደ አካባቢዉ መዝመቱንም ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታዉቀዋል። ሰዎችን የሚገድሉ፣ የሚያቆስሉና የሚያፈናቅሉ ወገኖችን መንግሥታቸዉ ለፍርድ እንዲቀርብም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ማለዳ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቃል አቀባይ ገለታ ሀይሉ እንደሰማችው በአማራ ክልል ጃዊ ወረዳ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ በደረሰ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን እና የሟቾች ቁጥር ተጣርቶ ባያልቅም ከ80 በላይ የሚሆኑ ግን ቆስለው በጃዊ ሆሰፒታል እየታከሙ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ “የደረሰው ጥቃት በሁለት ቀበሌዎች የተከሰተ እና እጅግ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ነው” ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ወደ 90 የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች እንደሚገኙም አክለው ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ ባካባቢው መድረሱን እና ከምርመራ ስራዎች ባሻገርም ቀጣይ የአፀፋ ጥቃት እንዳይደርስ ጥበቃ ላይ መሰማራታቸውንም ገልፀዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 26 ሚያዚያ 26 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here