የዘውግ ፖለቲካ፣ ጠባብ ብሔርተኝነትና ዴሞክራሲ

0
998

በአገራችን የፖለቲካ ተዋስዖ ውስጥ የሚታወቁትን ወሳኝ ቃላት በመበየን የሚንደረደሩት መላኩ አዳል፥ የአገራችን ዋናው ችግር እንደ ሕዝብ የብሔረ መንግሥትነት ተግባር አለመፈጸሙና ከብሔር ደረጃ አለመድረሳችን ነው ሲሉ ይሞግታሉ። ብሔር ግንባታ የተሳካ የሚሆነው የዳበረ የካፒታል ልማትና መስፋፋት ከጥሩ የፋይናነስ አስተዳደርና አድሎዓዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ ወካይ ከሆነ አስተዳደር ጋር ሲጣመር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ብሔርተኝነት የብሔር እኩልነትን የሚያቀነቅን ርዕዮት ሲሆን ዴሞክራሲ ደግሞ የዜጎችን እኩልነት በቀዳሚነት ለማረጋገጥ የሚያገለግል ፖለቲካዊ ስርዓት ነው። በመሆኑም ብሔርተኝነት በወሳኝ ፖለቲካዊ ባሕርይው የቡድን ወይም የማኅበራዊ ስብስብ መብቶች መከበርን መሠረት ያደርግና የራስን በራስ ማስተዳደር መብትን ይጨምራል። ዲሞክራሲ ባንፃሩ በወሳኝነት የግለሰቡን መብቶችን ነፃነቶች መሠረት ያደረገ በሕዝብ ለሕዝብ የቆመ መንግሥት መመስረትንና የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባትን መሠረት ያደርጋል። ብሔር የተለያዩ የጋራ የሆኑ ልዩ ልዩ ባሕሪያትን የሚጋሩ፣ ልማታዊ ሥራዎች ለእነሱና በእነሱ ላይ በመሠራታቸው ምክንያት የሰዎቹ የአንድነት ስሜታቸውና ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ያለ፣ የራሳቸው መስተዳድር እንደሚያስፈልጋቸው የተገነዘቡና በአንድ ግዛት ወይም በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ የበርካታ ሰዎች ስብስብ ነው።

ብሔር ማለት በቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብና ባሕል፣ መልከዓ ምድር፣ ሀብትና የገቢ መጠን፣ የፍላጎቶች ልዩነት ውስጥ አንድ ጥቅልና ብሔራዊ ደረጃ ያለው፣ እርስ በርስ የተሳሰረ፣ የፍላጎትና የምርጫዎች አንድነት ወይም ተመሳሳይነት ያለው ሕዝብ መጠሪያ ማኅበራዊ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን ይህም ልዩነት ለአገር ደኅንነት አደጋ የማይሆኑበትን ትስስር ይፈጥራል። የብሔር ግንባታ ያለ ግዳጅ፣ ዘመናዊት ትምህርትን፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታን (የኮሚኒኬሽን አውታሮች፣ መንገድ)፣ የገጠሩን የእርሻ ዘዴዎች ማሻሻል፣ ነፃ ገቢያንና የኢኮኖሚ ትስስርን፣ መልካም አስተዳደርን ግብዓት ያደርጋል። እነዚህ ግብዓቶች አብዛኛው ሕዝብ የግልና የጋራ ደኅንነቱን፣ ኑሮውን ከውጭ ኩነቶች ጥገኝነት የሚላቀቅበት የተግባር ደረጃ ይፈጥራል። የብሔር ግንባታ ሕዝብ የጋራ ማንነት የሚፈጥርበትና የሚያዳብርበት የረጅም ጊዜ ተግባር ነው።

የአገራችን ዋናው ችግር እንደ ሕዝብ የብሔረ መንግሥትነት ተግባር አለመፈጸሙና ከብሔር ደረጃ አለመድረሳችን ነው። ይህንንም ክፍተት የዘውጌ/ዘር ፖለቲከኞች ለራሳቸው ከፋፋይ ፖለቲካ መጠቀማቸው ነው፣ የሌለው ብሔር መሰረት ያደረገ የብሔር ጭቆና ነበር የሚል የሐሰት ትርክት። ብሔር ግንባታ የተሳካ የሚሆነው የዳበረ የካፒታል ልማትና መስፋፋት ከጥሩ የፋይናነስ አስተዳደርና አድሎዓዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል፣ ወካይ ከሆነ አስተዳደር ጋር ሲጣመር ነው። ስለዚህም ለዚህ የብሔር ግንባታ ጠንክረን በኅብረት መሥራት ይጠበቅብናል።

ኢትዮጵያ በጣም ቀደምት አገር በመሆኗ ምክንያት ውስብስብ የታሪክ ሒደቶችን ያለፈች አገር ነች። የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስትና ጋር የተያያዘውና በአክሱም፣ ላሊበላ፣ ሸዋና ጎንደር ሆኖ ያስተዳደረውን የሰለሞንና የዛግዌ ስረዎ መንግሥታት፤ ከእስልምና ጋር የተቆራኘውንና ቅድሚያ በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ከደቡብ አረብያ የገባውንና በፈጠጋር፣ በኢፋት፣ በአዳል፣ በሶማሌና በሐረር ያስተዳደሩት ኤምሬቶችንና የግራኝን ኢትዮጵያ ግዛት፤ ከባሌና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ተነስቶ በግራኝ አሕመድ የተዳከመውን የአገሪቱ ክፍል በገዳና ሞጋሳ ሥርዓትና በጦርነት የተቆጣጠረው የኦሮሞ መስፋፋትን፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብንና በእያንዳንዱ ብሔረሰብ መካከል የተደረጉትን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ መሰተጋብሮች የሚያጠቃልል ነው። ይህም የሚያሳየው በጣም ሠፊ፣ የተለያዩ ቡደኖችን ውስጡ የያዘ በመሆኑ የእያንዳንዱን ኅብረተሰብ ታሪክ በትምህርት ስርዓታችን ለማካተት የፖለቲካ ታሪክ ብቻ ከመፃፍ ወጥተን የሁላችንንም የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባሕልና ልማድ ታሪካችንንም በማካተት ለሁላችን የሚሆን የተስማማንበት በታሪክ ሙያተኞች የተፃፈ ታሪክ እንዲኖረን ሁላችንም ግፊት ማደረግ ይጠበቅብናል።

በ1960ዎቹ በግራ ዘመም ወጣቶች በኢትዮጵያ የተጀመረው የዘር ፖለቲካ የሶቪየት ኅብረቱ መሪ ከነበረው ስታሊን የብሔር ብሔረሰብ አስተሳሰብ የተወሰደ ነው። የዘር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ዋናው ማጠንጠኛውም የብሔር ጭቆና ነበር የሚል የሐሰት የታሪክ ትርክት ነው። የዘር ፖለቲካ ዋናው ምክንያት ድኅነት ነው። በመሰረቱ የዘር ፖለቲካ በአቅመ ደካማ ወይም ራስ ወዳድ ምሁራን የሚቀነቀን አላማውም የግል ሥልጣንና ጥቅም ነው። ʻበእኛ እነሱʼ ከፋፍለህ ግዛ ሀብትን ለራስ ለመዝረፍና
በስሜት ሕዝብን ገፋፍቶ ለመመረጥ ይጠቀምበታል። የዘር ፖለቲካ ለክርክር፣ ለውይይትና አሳምኖ ለማመን የማይመች፣ በሰጥቶ መቀበል ላይ የማይመሰረት፣ በስሜት የሚመራ መንጋነትን የሚያበረታታ በመሆኑ ለሕግ የበላይነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተግዳሮት ነው። የዘር ፖለቲከኞች መደበቂያ ብሔር የሚባል ዋሻ ስላላቸው የሞራል ገደብ የላቸውም።

በችሎታ፣ በፈጠራና የሰው ልጅ አዕምሮ ለደረሰበት ክህሎት ቅድሚያ የማይሰጥ ፖለቲካ በመሆኑ፣ ችሎታ ያላቸው የብሩህ አዕምሮ ባለቤቶች እየተበደሉ አፈጮሌዎች በሥልጣን ላያ ተፈናጠው ለብሔሩ ተቆርቋሪ እኛ ነን በማለት ለጥፋትና ውርደት ይዳርጉታል። የዘር ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሸን አንዲበዙ፤ በሰዎች መሃል አለመተማመን፣ አለመደማመጥና መከባበር እናዳይኖርና መንግሥት የተቀዋሚውን ፓርቲ የማዳከሚያ መንገድ እንዲያገኝ አድረጎታል። የዘር ፖለቲካችን ሕዝባችንን አስተባብረን ድኅነትን፣ ኋላ ቀርነትንና ችጋርን መታገል የምንችልበትን የሰው ሀብት እያባከነ ነው። የዘር ብሔርተኝነት ብዙ አገሮችን አፍርሷል። ሕዝቦችንም አጫርሷል፤ እኛም የገፈቱ ቀማሽ ሆነናል። ይህንንም በሕወሓት 27 ዓመት አስተዳደር አይተነዋል።

በጠቅላላው በአገራችን፣ በተለይም በተለያዩ ክልሎች ያለው ሕዝብ የተለያየ ቋንቋ የሚናገር አንድ ወጥ ብሔር እንዳልሆነ ይታወቃል። ባለብዙ ብሔር ብሔረሰብ ባላቸው አገሮች የዘር ብሔርተኝነት ለዜጋዊ ብሔርተኝነትና ለዲሞክራሲ ግንባታ ተግዳሮት ነው። አንድነትም ይህን ልዩነት የሚያመጣውን አሉታዊ ችግሮች ለመግታት የሚውል ስልት እንጂ ጠባብ ብሔርተኞች አንደሚሰብኩት ልዩነትን ለመጨፍለቅ የሚውል ስልት አይደለም። የኢትዮጵያ አንድነት መሰረቱም ልዩነትን አቅፎ በመያዝ ውስጥ ነው። ብዝሃነትን ለማስተናገድም የዘር ብሔርተኝነት የግድ አይደለም። የዘር ፖለቲካ አዋጭ አክሳሪ ስለሆነ አንድነት ተመራጭ ቢሆንም፣ አሁን ባለው ሁኔታ የዘር ፖለቲካው አብሮን ለዓመታት የሚቆይ መሆኑን አውቀን አንድነታችንና የዘር ፖለቲካውን እንዴት ሚዛኑን ጠብቀን ማስኬድ እንዳለብን ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህም ማለት የዴሞክራሲ ግንባታው እያካሄድን ጎን ለጎን የብሔርተኝነት ጉዳይ የሚስተናገድበትን መንገድ መፈለግ ይኖርብናል።

ስለዚህ የዘር ፖለቲካ አራማጆችም የሚያመነጯቸው ርዕዮቶች ከግል ጥቅም የወጡና የራሴ ዘር ለሚሉት ያደሉ እንዳይሆኑና ለሁሉም የአገሪቱ ሕዝብ የሚጠቅሙ እንዲሆኑ መሥራትን ይጠይቃል። ያሉንን የተለያዩ ሀሳቦች እርስ በርሳቸው በማፋጨት፣ ብሎም በማቀራረብ በጋራ ለጋራ የሚሆኑ አማራጭ ሐሳቦችን በመፍጠር ሕዝብን መጥቀምም ይቻላል። የዘር ብሔርተኝነትና የፌዴራል አወቃቀር በትንሹ የሚገናኙ፣ የዘር ፖለቲካ ቀረ ማለት የፌዴራል ሥርዓቱና አስተዳደር ይቀራል ማለት እንዳልሆነ መረዳት ይኖርብናል። ወጣቱ በደሙ ታግሎ ሕወሓት የጠነሰሰውን ጠባብ የሆነ ስግብግብ የዘር ፖለቲካ ካንበረከከ በኋላም በተቀደደለት የዘር ብሔርተኝንት ቦይ መፍሰስ መቀጠሉ መቆም አለበት።

ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመገንባትና የሕግ የበላይነትን በማስፈን፣ ዕውነተኛ ፍትሐዊ አስተዳደር እንዲኖር በማድረግ፣ የሕንኛውንም ቡድን ባሕልንና ቋንቋን በማክበር፣ ጥያቄዎችን በመመለስ፣ ሰብኣዊ መብቶችን በማክበር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት በሃይማኖትና ዘር መሠረት እንዳይሆን በርዕዮት ብቻ እንዲሆን በመሥራት፣ ልማት ለሁሉም እንዲዳረስና ለእኩል ተጠቃሚነት በመሥራት፣ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ፣ ድኅነትን በመቀነስና መሰረታዊ የዴሞክራሲ ሥራዎች (ነፃ ምርጫ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት) በመሥራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና ምሁራን ባሳተፈ መልኩ የእውቀት፣ የክህሎት፣ የግብረገብና የሞራል ወዘተ ለውጥ እንዲኖር በመሥራትና የታሪክ የተቃርኖ ትርክቶችን ወጥ በማድረግ ከፖለቲካ ታሪክ በተጨምሪ የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና የባሕል ታሪኮችን በማካተት በሕብረ ብሔራዊ ዴሞክራሲ በመኖር ውስጥ የቡድን መብት እንደሚከበር በማሳየት የዘር ብሔርተኝነት በራሱ ጊዜ ሊያከትም የሚችል ነው። ነገር ግን የዕድገት እንቅፋት እንዳይሆን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here