አወዛጋቢው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ምርጫ ጉዳይ

0
850

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋን ምርጫ ለዘንድሮ አስተላልፎ ነበር። ይሁን እና ዓመቱ ቢጋመስም በ2011 ይካሔዳል ስለተባለው የኹለቱ ከተሞች ምርጫን በተመለከተ ከምርጫ ቦርድ በኩል የተሰማ ነገር የለም።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች አንዱ የሆኑት አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ምርጫው ከአገራዊው ምርጫ ጋር ቢካሔድ እንደሚሻል ተናግረዋል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦኦፌኮ) ከፍተኛ አመራር ሙላት ገመቹ ደግሞ በዚህ ዓመት መካሔዱን መርጠዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያውያን ዴመክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ከበደ ጫኔ (ዶ/ር) በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ ዜጎች መፍትሔ ሳይገኝ የእነዚህ ኹለት ከተሞች ምርጫ ብቻ ሳይሆን አገራዊውንም ምርጫ ማካሔድ አይገባም ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን በይፋ እስካላነሳው ድረስ፤ የገዢዉ ይሁን፤ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች፤ ነፃ ይባሉ የመንግሥት መገናኛ ዘዴዎች፤ የግል ይሁኑ የድርጅት ተቋማት በኹለቱ ትላልቅ ከተሞች ምርጫ ስለመደረግ አለመደረጉ ያሉት ነገር የለም።

ኢትዮጵያን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሕዝባዊ ተቃውሞ፤ ግጭት እና ውጥረት የአገሪቱን ፖለቲከኞች ትኩረት በመሳቡ የኹለቱን ከተሞች አስተዳደር፤ ምርጫ እና ሒደቱን ለማጤን ጊዜ አልነበራቸዉም መባሉ ያስኬድ ይሆናል የሚሉት ፖለቲከኛው ሙላት፥ ይሁንና ሕዝብን ለተቃውሞ ያሰለፈ፣ ያሳደመ፣ ለሞት፣ ለጉዳት እና እስራት የዳረገዉ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲያዊና የሰብኣዊ መብት ጥያቄ መሆኑ እንደማይካድ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያን በፖለቲካ ይሁን በምጣኔ ሀብቱ የሚዘውሩት የኹለቱ ከተሞች ነዋሪዎች የመምረጥ አለመምረጥ መብትም እነዚያ ሕዝብን ለተቃውሞ ያሳደሙ ጥያቄዎች አካል መሆናቸዉን ይናገራሉ።

ፖለቲከኛው ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው፣ ኹለቱን ከተሞች የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና የሚቆጣጠራቸዉ ተቋማት የኹለቱን ከተሞች ምርጫን ርዕስ ያላደረጉት ሕዝብ ያነሳባቸውን ጥያቄዎች እስከሚያዳፍኑ ነው። ገዢዉ ፓርቲ እና ተቋማቱ ግፊት ካልተደረገባቸው በፈለጉበት ጊዜ ማንሳት እና መጣል የሚችሉትን ጉዳይ ርዕሥ የሚያደርጉበት ምክንያት የለም ባይም ናቸዉ።
የኢዴፓ ሊቀመንበር የነበሩት ከበደ ጫኔ (ዶ/ር) ግን በኹለቱም ሐሳብ አይስማሙም፤ የጸጥታ ችግር ባለበት፣ የሕዝብ ቆጠራ ባልተካሔደበት፣ ፓርቲዎች እራሳቸውን በደንብ ባላስተዋወቁበትና ምርጫ ቦርድ እራሱን ባላሰናዳበት ወቅት ምርጫ ይካሔድ ማለቱ ወደ ባሰ አመጽ መጋበዝ እንደሆነ በማስገንዘብ፣ ሁሉም ነገር በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሲካሔድ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ አመቺ መሆኑን ይጠቁማሉ።

መችና እንዴት እንደሚካሔድ የታወቀ ነገር የለም
በ2010 ለአንድ ዓመት የተሸጋገረው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምርጫ በዚህ ዓመት መካሔድ የነበረበት ቢሆንም እስካሁን አለመካሔዱ አነጋጋሪ ሆኗል። እንዲሁም በመላ አገሪቱ የሚካሔዱ የአካባቢና ማሟያ ምርጫ በአንድ ዓመት እንዲራዘሙ ፓርላማው ቢወስንም ዓመቱን ጠብቆ ምርጫው እንዲካሔድ ውሳኔ አለማስተላለፉ ጥያቄ አጭሯል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው የድሬዳዋው ነዋሪ መሳይ ተክሉ ደግሞ ምርጫው እንዲራዘም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወሰነ በኋላ እንኳን ስለ ተራዘመበት ምክንያት፤ ምርጫዉ እስኪደረግ ከተማይቱን ስለሚያስተዳድረስ ባለሥልጣን ወይም አካልም ሆነ፤ ከተማይቱን ስለሚያስተዳድርበት ደንብ ለከተማይቱ ሕዝብ ያስረዳ ወገን የለም።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ባሳላፈዉ ውሳኔ መሰረት ለ2010 ተይዞ የነበረዉ የኹለቱ ከተሞች አስተዳደሮች የምክር ቤት አባላት እና ለተጓደሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ የሚደረገዉ በያዝነዉ ዓመት ነበር። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ ለምክር ቤቱ አባላት እንደነገሩት ምርጫው እንዲራዘም ካስገደዱት ምክንያቶች አንዱ የፀጥታ መደፍረስ ነው።

የድሬዳዋው መምህራን ማኅበር ሊቀመንበር እና የቀድሞው የከተማይቱ ምክር ቤት አባል መምህር አበበ ታምራት እንደሚሉት ግን ድሬዳዋ ሰላም ናት። ለምርጫው በቂ ዝግጅት አልተደረገም ካልተባለ በስተቀር የፀጥታ ችግር ለድሬዳዋ ምክንያት ሊሆን አይችልም ሲሉም አክለዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አዲስ ዓለም እንቻለው፣ የምርጫው ጊዜ ተራዘመ እንጂ በዚህ ጊዜ ይካሔዳል ተብሎ ቀን እንዳልተቆረጠለት ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ነግረውናል።

ሰይፈ ገብረ ማርያም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የአፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ምርጫ አሁንም በተወሰነበት ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በ2010 ከተወሰነው ውሳኔ ውጪ ያሉት ነገሮች ሁሉ ስህተት መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሸጋገረውን ምርጫ እንደገና መካሔድ እንዳለበት ይወስናልም ብለዋል። መቼና እንዴት ለሚለው ግን እሳቸውም መልስ የላቸውም።

የተራዘሙት ምርጫዎች በ2011 እንደሚካሔዱ ቢገለጽም ከዓመት በኋላ ምርጫዎቹ በየትኛው ወር እንደሚካሔዱ ግን በግልጽ አልተቀመጠም። ወሩ መቼ ነው በሚልም ከፓርላማ አባላት ለቀረበው ጥያቄ አሁን መወሰን አይቻልም የሚል ምላሽ ከምክትል አፈጉባኤዋ መሰጠቱ ይታወሳል። ምክትል አፈ ጉባኤዋ ሽታዬ ማናለ በጉዳዩ ላይ የብዙ አካላት ምክክር ስለሚያስፈልግ ቀኑን መወሰን አልተቻለም ነበር ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሚውኒኬሽን አማካሪ የሆኑት ሶሊያና ሽመልስ በተለይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፤ በ2010 ይካሔድ የነበረው የአዲስ አበባ ምርጫ በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ለአንድ ዓመት መራዘሙን፤ በአሁኑ ወቅትም የቦርዱ አባላት ካልተሟሉ ምርጫው መቼ እንደሚካሔድ ማወቅ እንደማይቻል ይገልጻሉ።

የአማካሪዋ አሁን ባለው ሁኔታ የተቀየረው የቦርዱ ሰብሳቢ ብቻ በመሆኑና ሌሎች የቦርድ አባላት ባለመሟላታቸው ሕጉ ከጸደቀ በኋላ ተቋሙ ውስጥ ባለው አዲስ የማደራጀት ሥራ ʻሪፎርምʼ አዲስ የቦርድ አባላት ለውጥ እንደሚደረግ ገልፀው፤ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ የትኛውንም ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ተናግረዋል። የቦርዱ አባላት ሲሟሉ ወደ ምርጫ እቅድ ሥራዎች እንደሚገባ፤ ነገር ግን ባልተሟሉ የቦርድ አባላት የምርጫን ውሳኔ ማሳለፍ እንደማይቻልና በሕጉ መሰረት የሚሾሙ የቦርድ አባላት ሳይኖሩ ምርጫን ማካሔድ ሕጋዊ አለመሆኑን ሶሊያና ጨምረው ጠቅሰዋል።

“የቦርዱ አዲስ አደረጃጀት የተለያዩ ክፍልፋዮች ያሉት ሲሆን፤ የመጀመሪያው የምርጫ ሕግ ማሻሻል፣ የተቋሙን መዋቅር መቀየር ቅድሚያ የተሰጣቸው ሲሆኑ፤ ኹለቱ ሥራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ምርጫ ቦርድ ይሠራቸዋል የሚባሉትና በሕግ የሚሰጡ ኀላፊነቶች የሚከናወኑት የተቀየረውን የምርጫ ሕግ መሰረት አድርገው ይሆናል። አሁን እየተከናወኑ የሚገኙ ሥራዎች የቦርዱ አጋር አካላት ከሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻልን ያካተቱ ናቸው” በማለት የኮሙኒኬሽን አማካሪዋ ከምርጫው በፊት ቦርዱ እያከናወነ ያለውን የለውጥ ሥራዎች አስመልክተው ገልጸዋል።

መጋቢት 27 /2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው 4ኛ ልዩ ስብሰባው ለረቂቅ አዋጁ የተዘጋጀውን ሪፖረትና የውሳኔ ሐሳብ አድምጦ ስድስት የተለያዩ አዋጆችን መርምሮ ባጸደቀበት ወቅት፥ የሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፎዚያ አሚን፤ እስካሁን ለምክር ቤቱ የቀረበው አዋጅ ምርጫ ቦርዱን ስለማቋቋም የሚጠቅሰው ረቂቅ ብቻ እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ሕጎችና አዋጆች ለቋሚ ኮሚቴው አለመድረሳቸውን ጠቁመው፤ የምርጫ ሒደቱን ለማካሔድ የቦርድ አባላት መሟላት የሚለው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀው ነበር።

“የምርጫ ቦርድ ተቋሙ አለ። አልተሟላም የሚባል ነገር የለም። በተነሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ምትክ አዲስ ሰብሳቢ ተተክቷል። ሌሎቹ የቦርድ አባላት ደግሞ በሕጋዊነት ሥራ ላይ አሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው። አዲሷ ሰብሳቢም ከእነርሱ ጋር እየሠሩ አዲስ ቦርድ የሚተካ ከሆነም ይቀጥላሉ፤ ካልሆነ ደግሞ አልተሟላምና ተቀምጫለሁ የሚል ነገር አይኖርም። ስለዚህም የቦርድ አባላት እንዳሉ ነው ምክር ቤቱ የሚያውቀው” ሲሉ ምርጫ ቦርድ አባላት አልታሟሉልኝም ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።

የሕጋዊነት ጥያቄ ስለማስነሳቱ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2010 መካሔድ የነበረበትን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተሞች ምክር ቤትና የአካባቢ ምርጫን ያራዘመበት መንገድ የሕጋዊነት ጥያቄ አስነስቷል። አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሔድ በሕገ መንግሥቱ መደንገጉን በመጥቀስ፣ ከሕገ መንግሥቱ የሚቃረን መሆኑን በጥያቄ መልክ ማቅረባቸው ይታወሳል። በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች ሥልጣን የሚያዝበት የምክር ቤቶች ምርጫ ላለፉት ኹለት ጊዜያት የተካሔደው በሚያዝያ ወር ውስጥ ሲሆን፣ ከተሞቹ የተቋቋሙባቸው ቻርተሮችም ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንደሚካሔድ ደንግገዋል።

በወቅቱ ለተነሱት የሕጋዊነት ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት መካከል ስብሰባውን የመሩት ምክትል አፈ ጉባዔ ሽታዬ ምናለ ሲሆኑ፣ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ምርጫው እንዲራዘም ብቻ በመሆኑ፣ በዚህ ላይ ብቻ መወያየት እንደሚሻል በመግለጽ የምርጫ ዘመናቸውን ስለጨረሱ ባለሥልጣናት ጉዳይ የተነሳውን ጥያቄ ዘግተው አልፈዋል።

ምርጫ የሚካሔደው በየአምስት ዓመቱ መሆኑን ሕገ መንግሥቱ እንደሚደነግግ በማውሳት ማራዘሙ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ግጭት እንደሚፈጥር ለቀረበው ጥያቄ ምንም ዓይነት የሕግ መጣረስ እንደሌለ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንዲራዘምለት ጥያቄ ማቅረቡን ያስታወቁት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አማኑኤል አብርሃም መሆናቸው ይታወቃል።

የፖለቲካ ተንታኙ ሙሼ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፣ በ1997 ምርጫ ወቅት ቅንጅት አዲስ አበባን አልረከብም ብሎ እራሱን ሲያገል፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመርጦ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ያለው ካቢኔ ግን ጊዜውን ጨርሶ አሁንም በማስተዳደር ላይ እንደሚገኝ በማውሳት፣ ለአምስት ዓመት አገለግላለሁ ብሎ ቃል የገባው ካቢኔ መበተን እንደነበረበትና በጊዜያዊ አካል መመራት እንደነበረበት ይገልጻሉ።

በ97 በሕጉ መሰረት ካቢኔው ተበትኖ እንደ አዲስ ካቢኔ ተዋቅሮ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ያስታወሱት ሙሼ፣ የለውጥ ሒደት ላይ ስለነበር ሁኔታዎች እንዳልፈቀዱ ግልጽ ቢሆንም፣ ይሄን ያህል ጊዜ መቆየት እንዳልነበረበት ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው እንዲራዘምለት ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ፣ ምርጫ ቦርዱ በአዲስ መልክ እየተዋቀረ መሆኑን፣ የቦርድ አባላት መሟላት አለመቻሉንና የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸው ለምርጫው የሚደረጉ ዝግጅቶች የተሟሉ እንዳይሆኑ ተፅዕኖ ማሳደሩንና ምርጫውን ለማካሔድም እንደማይቻል ገልጿል። በመሆኑም በምርጫ አዋጅ ቁጥር 532 አንቀጽ 28(2) እና አንቀጽ 29፣ እንዲሁም በፓርላማው የአሠራርና የአባላት ደንብ አንቀጽ 64 መሠረት ምክር ቤቱ ውሳኔውን በማሳለፍ ምርጫውን እንዲያራዝምለት ጠይቋል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያው ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) የተጠቀሱት አንቀጾች ምርጫውን ለማራዘም የሕግ መሠረት የላቸውም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 28(2) “ጠቅላላ ምርጫ በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሔዳል። ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ጉዳዩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ እንዲካሔድ ሊያደርግ ይችላል” ነው የሚለው ብለዋል።

የምርጫ ሕጉ አንቀጽ 29 ደግሞ ስለአካባቢ ምርጫ የሚደነግግ እንጂ የምርጫ ጊዜን ስለማራዘም ፈጽሞ አይገልጽም። የተጠቀሰው የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 64 ላይም የተጠቀሱት ምርጫውን ለማራዘም እንደማይችሉ ታደለ (ዶ/ር) ገልጸዋል። አንቀጽ 64 የሚደነግገው ስለምክር ቤቱ ውሳኔ ነው ሲሉም ያክላሉ።

ምክር ቤቱ ውሳኔ የሚያሳልፈው ፖሊሲ ለማፅደቅ ወይም ውድቅ ለማድረግ፣ እርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ፣ ለአንድ ጉዳይ ወይም ሁኔታ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጥ ለመጠየቅ፣ አንድን የመንግሥት ተግባር ለመደገፍ ወይም ለመቃወም፣ የአቋም መግለጫን በተመለከተና በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ እንጂ ሕግ የማሻሻል ተግባርን ለመፈጸም አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ሕገ መንግሥቱ ሥልጣን የሚመሠረተው በየወቅቱ በሚካሔድ ምርጫ እንደሆነ በአንቀጽ 38 ላይ መደንገጉን ያስረዱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ሚዛኔ አባተ (ዶ/ር) በማናቸውም ደረጃ በየጊዜው በሚካሔድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት ዜጎች እንዳላቸው፣ እንዲሁም ምርጫ መራጩ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበትና ዋስትና የሚሰጥበት እንደሆነ ገልጸዋል።

“ፓርላማው ይህንን በየወቅቱ የሚካሔድ ምርጫ ዛሬስ ይለፈን ብሎ ነው የወሰነው” ሲሉ ተችተዋል። ይህ መሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 13 ሥር ተቀባይነት ካገኙ የሰብኣዊ መብቶች ጋር ጭምር እንደሚጣረስ ተናግረዋል። “ከምርጫ መሠረታዊ መርሆዎች አንዱ በየጊዜው (Periodic) መሆኑ ነው፤” ያሉት ሚዛኔ “ይህንን መርህ እስቲ ዛሬ ተውኝ፣ ይለፈኝ እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ ከማንም እንዳይመጣ የሚፈራ ነው” ብለዋል።

ምርጫው ወደ 2011 ሲራዘም የሥልጣን ጊዜያቸውን የጨረሱ አመራሮች ምን እንደሚሆኑ ውሳኔ አለመሰጠቱ ሌላው ስህተት መሆኑን ሚዛኔ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ትልቁ ቦታ የሆነው የከንቲባው ወንበር ክፍት ሆኖ እንዲቆይ የተደረገው በየትኛው የሕግ አግባብ ነው? ሲሉ የሚጠይቁት ሙሼ አካሔዱ ጤናማ አለመሆኑን ይገልጻሉ። እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች ሕገ መንግሥቱን መሰረት ያደረጉ አይደሉም ሲሉም ይተቻሉ።

የሞግዚት አስተዳደር በሕግ ሲሰየም ሥልጣኑ እንደሚገደብ፣ በሌላ በኩል ፓርላማው የምርጫ ዘመኑን ሳይጨርስ በሚበተንበት ወቅት እንኳን ምርጫ በስድስት ወራት ውስጥ እንደሚካሔድ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ያለምክንያት አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በ2011 ምን ወር ላይ ነው የሚካሔደው የሚለውን ፓርላማው አለመወሰኑ ደግሞ በስህተት ላይ የተሠራ ሌላ ስህተት ነው በማለት ተችተዋል።

“ፓርላማው የኹለት ሰዓት ስብሰባ አድርጎ እንደ ተራ ነገር ምርጫውን ማራዘሙ ያለመብሰላችንንና የምርጫ ሕጋችን ገና ብዙ የሚቀረው መሆኑን ያሳያል” ነው ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here