የአገር ግንባታ ስንክሳሮች ከተቋማት ግንባታ አንፃር

0
1194

የአገር ግንባታ ጉዳይ የአንድ ጊዜ የቤት ሥራ አይደለም፤ ቀጣይና የማያቋርጥ ሒደት ነው። የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ከተመሠረተ ጀምሮ በርካታ የአገር ግንባታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ኢትዮጵያ አሁንም ፖለቲካዊ ለውጥ እያስተናገደች እንደመሆኑ፥ የአገር ግንባታ ሒደቱ አዲስ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል በማለት፥ ሐይማኖት አሸናፊ ጉዳዩን ከዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ አንፃር በማገናዘብ እና የአገር ግንባታ ላይ የተጻፉ የጥናት መዛግብትን በማገላበጥ በሐተታ ዘ ማለዳ ቃኝታዋለች።

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከባድ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ያስከተለ ሥልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ወንጀል እና ሌሎችንም የሕግ መተላለፎችን በመፈፀም ጠርጥሯቸው፣ ነገር ግን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሊያውላቸው ያልቻለውን የቀድሞውን የመረጃ እና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው አሰፋን በሌሉበት ከሷቸዋል። በተለያዩ አጋጣሚዎች አገር ውስጥ እንዳሉ የሚነገረው እኚህ ሰው በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ የደኅንነት አማካሪ በመሆን እያገለገሉም ጭምር እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል።

መንግሥት ጌታቸውን በቁጥጥር ሥር ያላዋለው “አንድን ሰው ለመያዝ ብዙ ደም መፍሰስ የለበትም” በሚል ምክንያት መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ፀጋዬ እና ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተከታታይ ገልጸው ነበር።

በመቀጠልም በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን፣ የፊቼ ጫምባላላ የዘመን መለወጫ በዓልን ተከተሎ በተከሰቱ ተከታታይ ግጭቶች በወንጀል 100 ሰዎች ተጠርጥረው የነበር ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ወቅት ድረስ 86 ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው 14 እስካሁን አልተያዙም።

ሐምሌ ወር፣ 2010 በጅጅጋ ከተማ የነበረውን አሰቃቂ ግጭት ተከትሎም በቀድሞው የክልሉ ፕሬዘዳንት የነበሩት አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) መዝገብ 47 ሰዎች ተጠርጥረው ስምንት ሰዎች ብቻ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ኢትዮጵያን በአገር ውስጥ መፈናቀል በዓለም አንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጡት እነዚህ ተከታታይ ግጭቶች ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሱ 2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ቤት ንብረቱን አስጥሎ በመጠለያ ውስጥ አስቀምጧል። ብዙዎችን አነጋግሮ የነበረው የጌታቸው በአንድ ክልል ውስጥ ተደብቆ መቆየት በየክልሉ፣ በየዞኑ ወረዳ እና ቀበሌ ተባብሶ መቀጠሉን የሰላም ሚኒስቴሯ ሙፈሪሃት ካሚል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጸዋል።

ባለፉት 9 ወራት ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ 468 ያህል ሰዎች ዜጎችን በማፈናቀል ወንጀል በቁጥጥር ሥር ሲውሉ 420ዎቹ ክትትል ላይ መሆናቸውን ሚኒስቴሯ ተናግረዋል። ባጠቃላይም ባለፉት 9 ወራት ብቻ 2563 መዝገቦች ዜጎችን ከማፈናቀል ጋር በተያያዘ ክስ ሲከፈት፥ ካለፈው ዓመት ተሸጋግረው ከመጡት ጋር ሲደመር 4043 በሚሆኑ መዝገቦች ላይ ፖሊስ የምርመራ ሥራ የሠራባቸው ሲሆኑ 2276ቱ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠርት ተልከውለታል።
በወላይታ ሶዶ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ማርሸት መሐመድ በተለይም በአገር ውስጥ አሳልፎ የመስጠት ሕጎች ላይ ጥናት አድርገዋል። አንድ መንግሥት ዜጎቹን እኩል ሊያደርግ ከሚገባባቸው ጉዳዮች የመጀመሪያው የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ነው ይላሉ።

የሶማሌ ክልል ከሲዳማ እና ከትግራይ እንደሚለይ የሚናገሩት ማርሸት ከክልሉ ከማስፈፀም አቅም ማነስ እና ከአካባቢያዊው ነባራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም በክልሉ ካለው ሰፊ የሥም መመሳሰል ጋር መያያዙ ነው። ሲዳማ እና ትግራይ ግን ተፈላጊዎቹ የት እንደሚገኙ እየታወቀ ለፍርድ ማቅረብ ያለመቻላቸው ነው።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 51 መሠረት የፌዴራል መንግሥቱ በማንኛውም የፌደራል ጉዳዮች ላይ ሥልጣን እንዳለው ገልጸው ለክልሎች ከተሰጠው አካባቢያዊ ሥልጣን የፌደራሉ ለሚለየው ያለምንም የአካባቢ ወሰን በማንኛውም የፌደራል ጉዳዮች ላይ ሥልጣን መሰጠቱ ነው። እንደሚታወቀው የፌደራሉ መንግሥት እስከዛሬ አስተዳደራዊ ወሰን የሌለው ሲሆን አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ ናት።

ይህንን በመተግበር ሒደት ውስጥ የሚነሱ የተጠርጣሪውን መብት ለመጠበቅ የሚሆኑ ዝርዝር ሕጎች ያለመኖራቸው ጉድለት ቢሆንም፥ ሕገ መንግሥቱ ባቋቋማቸው ኹለቱ አገራዊ የፀጥታ ኀይሎች ተጠቅሞ በቁጥጥር ሥር ማዋል መዘግየት ያልነበረበት ተግባር ነበረ ሲሉም ያስረዳሉ።

ፍትሕ ወይስ ሰላም የሚለው ምርጫ ውስጥ የፌደራሉ መንግሥት በመግባቱ እንዳይደርሰ ለማድረግ የቻለው አደጋ ሊኖር እንደሚችል ዕውቅና ሰጥተው፥ ይህ ውሳኔ ግን አሁን እየታዩ ላሉ ከባድ እና አሰቃቂ ወንጀሎች የይለፍ ቃል መስጠቱን ይገልጻሉ።

ሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 51 ንዑስ አንቀፅ ስድስት ያቋቋማቸው የፌደራል ፖሊስ እና መከላከያም አገር ዐቀፍ ሆነው እንዲዋቀሩ የሚደረገው አገር ዐቀፍ ሚና እንደሚጫወቱ በመገንዘብ ነው የሚሉት ማርሸት፥ በተመሳሳይም አንቀፅ 50 ንዑስ አንቀፅ ስምንት “ለፌደራሉ መንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በክልሎች መከበር አለበት፤ ለክልልች የተሰጠው ሥልጣንም በፌደራል መንግሥት መከበር አለበት” ሲል ይደነግጋል።

ማርሸት “የፌደራል መንግሥቱ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በትብብር ላይ ተመርኩዞ እንጂ አግባብ ባለቸው ሕጎች ላይ መሠረት ማድረግ አለመቻሉ አሁን ለሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት ሆኗል። አገሪቱም በእውነተኛ የፌደራሊዝም ስርዓት ላይ ተመሥርታ ሳይሆን በፓርቲ መዋቅር ስትተዳደር መቆያቷ ስርዓቱ እንዳይዳብር፣ እንዲሁም ዜጎች ወይም የክልል መንግሥታት መሠረታዊ የሆኑትን የፌደራሊዝም መርሖዎች ሳይረዱ እንዲቆዩ አድርጓል” በማለት ያስረዳሉ።
ለዚህም እንደማሳያ በየክልሉ የፌደራል መንግሥቱን ስርዓት የሚያስፈፅሙ ፍርድ ቤቶች፣ ፌደራል ፖሊስ እና የፌደራል ዐቃቤ ሕግ መመሥረት እንደነበረባቸው እና ያ ባለመሆኑ ዋጋ ማሰከፈሉንም ይገልጻሉ። መንግሥት ፍርድ ቤቶች እስኪመሰረቱ በሚል ተዘዋዋሪ ፍርድ ቤቶችን በክልሎች የመሰረተ ሲሆን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በየክልሉ ያሉ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን ከወራት በፊት መዝጋቱ ይታወሳል።

የፌደራል ስርዓት እና ብሔር ግንባታ
አገረ-መንግሥት ምሥረታ (state formation) ማለት ከዚህ በፊት ተለያይተው የሚኖሩ የተለያዩ ሕዝቦችንና አካባቢዎችን በአንድ አዲስ ግዛት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ የማጠቃለል ሥራ ነው። ይህም በግልጽ የተቀመጠ ድንበርን በማበጀት፣ በረጅም ግዜ ስርዓት መሰባሰብ ሲሆን አንዳንዴም ከፈረሰበት መልሶ መመሥረት ሊሆን ይችላል። አንድ አገረ-መንግሥት በምሉዕነት ተመሠረተ የሚባለው የራሱ ግዛት፣ ሕዝብ፣ መንግሥት እና ሉዓላዊነት ሲኖረው ነው።

ብሔር-ግንባታ (Nation-building) ከአገረ-መንግሥት ምሥረታ በመቀጠል የሚመጣ እና በዋናነት በተመሠረተው አገር ጥላ ሥር ያሉ ግለሶበች ወይም ቡድኖች የእኔነት ስሜት እንዲያድርበቸው የሚያደርግ ነው። የአገር ባለቤትነት ስሜትን፣ እንዲሁም በጋራ በሚያሥማሙ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመሥራት ጠንካራ የሆነ የትስስር ስሜት የሚፈጠርበት ነው። ብሔር-ግንባታ እንደ አገረ-መንግሥት ምሥረታ በአንዴ የሚጠናቀቅ ሳይሆን፥ ቀጣይ እና እየተሻሻለ የሚሔደ የማያቋርጥ የስርዓተ ማኅበር ዝርጋታ ነው። (ኢትዮጵያ ብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ባሕሎች፣ ሃይማኖቶች እና ልማዶችን አቅፋ የያዘች አንድ ሉዓላዊት አገር እንደመሆኗ መጠን በዚህ ሐተታ ውስጥ ‘ብሔር-ግንባታ’ የሚለውን ሐረግ ስንጠቀም አገር ዐቀፍ የሆነ አስተሳሳሪ ስርዓተ ማኅበር ስለመገንባት እንጂ የቋንቋ፣ ባሕል ወይም ሃይማኖታዊ ውሕደት ወይም አንድ ዓይነትነት ማለታችን እንዳልሆነ አንባቢያንን እናሳስባለን።)

ሀብታሙ አለባቸው “ታላቁ ተቃርኖ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ስኬታማ የብሔር-ግንባታ መገለጫዎቹ “በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የሥራ ድርሻ ልውውጥ ሲደረግ ነው ይላሉ። የአገረ-መንግሥቱን ሕልውናና ደኅንነት የማስጠበቁ ተግባር እና ኀላፊነት ከመንግሥት ጦር ኀይል ወደ ሕዝቡ ይተላላፋል። ይህ የሚሆነው ሕዝቡ ከውስጣዊ የሃይማኖት፣ የጂኦግራፊ፣ የብሔር ወይም የገቢ ደረጃ ልዩነቶቹ በላይ የጋራ ዕሴቶቹን ያዳብራል” ሲሉ ያብራሩታል።

በአጠቃላይ ብሔር ማለት ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዘር ሐረግ፣ በታሪክ፣ በባሕል ወይም በቋንቋ ተሳስረው በአንድ አገር ወይም ግዛት ውስጥ ሲኖሩ ነው። ይህም ይበልጥ እየጠነከረ ሲሔድ ከላይ የተጠቀሱት የአገረ-መንግሥት ምሥረታ አላባዎች አንዱ እና ዋናኛ የሆነው ከውጪ ኀይል የሉዓላዊነት ጣልቃ ገብነት ነጻ በመውጣት የኢኮኖሚ፣ የደኅንነት እንዲሁም ከውስጥ ሊነሱ ከሚችሉ እና ሁሉንም ካላማከሉ የቡድን የበላይነት ስጋቶች ነጻ ያደርጋል።

ጠንካራ ብሔር በፌደራል መንግሥት ስርዓት ውስጥ ጠንካራ የሆኑ የዲሞክራሲ እና የሕግ ተቋማት ሲኖሩ ብቻ የሚተገበር መሆኑን ማርሸት ይከራከራሉ። ሁሉም የጥንካሬ መለኪያዎች በተቋማት ላይ መመሥረት ያለባቸው ሲሆን፥ ይህም የፌደራል ክልሎችን አዳክሞ ለብቻው የሚጠነክርበት ወይም ክልሎች የፌደራል መንግሥቱን አዳክመው ለብቻቸው የሚጠነክሩበት ሳይሆን፣ ሁሉም የቤት ሥራውን ጠንቅቆ የሚሠራበት መሆን አለበት ይላሉ።

“የፌደራል ስርዓቱን ያለሥልጣን ተዋረድ መረዳትም ሌላኛው አደጋ ነው። ፌደራሊዝም የግድ በክልሎች መካከል ወይም ክልሎች ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ያላቸው ግንኙነት ማለት ብቻ ሳይሆን፥ እስከ ዞን፣ ወረዳ፣ ቀበሌ በመጨረሻም እያንዳንዱ ዜጋ ድረስ ይሔዳል” ሲሉ ያስረዳሉ።

የአንድ ቀበሌ ነዋሪዎች ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ቢኖራቸውም በዞናቸው እና በክልላቸው የሚወሰኑ ውሳኔዎችን የሚፈፅሙበት የሥልጣን ተዋረድ የለም ማለት ግን አለመሆኑን የሚናገሩት የሕግ ባለሞያው፥ በነዚህ ውሳኔዎች ላይ ግን በአግባቡ መወከል የዴሞክራሲና የፌደራላዊነት መገለጫዎች ናቸው ብለው ያስረዳሉ።

እነዚህ ተቋማት እነማን ናቸው?
ምርጫ ቦርድ፦ የፈረሱ፣ የደከሙ ወይም በጥልቅ መለያየት ውስጥ ባሉ አገራት ለሚጀመር የብሔር ግንባታ የመጀመሪያው እርምጃ በአብላጫ ድምፅ ውክልና ተሰጥቶት የሚንቀሳቀስ መንግሥት ማቋቋም ነው። ይህንን ያለ ውጪ ወይም የውስጥ ጣልቃ ገብነት ማካሔድ የሚችል በፋይናንስ፣ በሰው ኀይል፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በቁርጠኛ አመራር ላይ የተመሠረተ የምርጫ ቦርድ አስፈላጊነት መሠረታዊ ነው።

ምርጫ አንድን አገር ሊያፈራርስ ወይ ጥልቅ ልዩነት ውስጥ ሊከት የሚችል ከመሆኑም በላይ፥ ዜጎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ መንግሥታቸውን ለማመን ወይም ላለማመን የሚያስችል ውሳኔያቸውም ላይ ጥልቅ ተፅዕኖ አለው። ለዚህም ነው አንድ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ከዕለት ተዕለት ሥራው ባለፈ ለትውልድ የሚተላላፍ ጠንካራ የምርጫ ባሕል እና ስርዓት ማስተላለፍ ያለበት።

ፍርድ ቤት፦ ለአንድ አገር ሕልውና የሆነውን የሕግ የበላይነት በማስፈፀም ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ብቃት ያለው እና ገለልተኛ ፍርድ ቤት የጀርባ አጥንት ነው። ሁል ጊዜም በጠንካራ ብሔር-ግንባታ ውስጥ የሚፈጠሩ ያለመግባባቶችን በሕግ እና በአመክኒዮ ላይ ተመሥርቶ እልባት ይሰጣል። ዜጎች የሚተማመኑበት የፍትሕ ስርዓት ሲኖር የደኅንነት ስሜታቸው እየጨመረ ይሔዳል፤ ሕግ አውጪው በወረቀት ያከበራቸውን መብቶች ማጣጣም እንደሚችልም ያምናል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በሕገ መንግሥቱ ከተሰጡ መብቶች መካከል አንዱ የሆኑት እና ንብረት የማፍራት መብት እንዲሁም፥ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመሥራት መብቱ ያልተከበረለት ዜጋ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ግንባታ ላይ የመሳተፍ ሚናው ቀርቶ የሚያስጠልለው ሌላ አገር ሲኖር ዜግነቱንም ይቀይራል።

ፍርድ ቤቶች በሌላው ዓለም መንግሥትን፣ የተዛነፈ የምርጫ ስርዓትን እና በተለይም ፌደራላዊ ስርዓቶች ውስጥ ክልሎች እርስ በርስ እንዲሁም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ያለመግባባቶች ሲኖሩ በሰላም ለመፍታት ዋነኛውን ሚናም ይጫወታሉ።
የፀጥታ መዋቅር፦ ይህ በተለይም ሕጋዊ የሆነ የኀይል ምንጭ ባለቤትነትን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ብቻ በማዋል እና ለዚህም አደጋ የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር መቻል ነው። በተለያዩ አማራጮች የሚፈፀመው የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ በተለይም የፖሊስ እና የመከላከያ ኀይል የዕለት ተዕለት ሥራ ይሆናሉ።

መከላከያው የአገርን ሉዓላዊነት በተለይ ሊፈጠር ለሚችሉ ጥቃቶች ምላሽ ለመስጠት ታስቦ የሚቋቋም ሲሆን በአካል ከሚታዩ ድንበሮችም ባሻገር የተለያዩ አገራዊ የደኅንነት ስጋቶችን ታሳቢ በማድረግ ይቋቋማል። የፖሊስ ውስጣዊ የሕግ ማስከበር ሥራ የሚሠራ ሲሆን እንደየደረጃው የኀይል ባለቤትነቱም ይለያያል።

በቅርቡ በረቀቀው የጦር መሣሪያ አዋጅም የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ኀይሎች ከፍ ያለ የጦር መሣሪያዎችን ይይዛል። ከመከላከያና ከደኅንነት ወጪ ያለ ማንኛውም የፀጥታ ኀይል አደገኛ ግዳጅ ላይ ካልተሰማራ በቀር የጦር መሳሪያ መያዝም እንዳይችል ረቂቁ ይደነግጋል።

ሕገ መንግሥቱ እንደሚለው “ክልሎች የየራሳቸውን የፖሊስ ኀይል ያደራጃሉ፣ ይመራሉ ሰላም እና ፀጥታ ያስጠብቃሉ። በተመሳሳይ ክልሎች የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ክልሎች ያቋቋሙት ልዩ የፖሊስ ኀይል ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ባይኖረውም የትጥቅ አመዳደብን በተመለከተ ግልጽ ሕግ ባለመኖሩ ብዥታዎች ሲፈጠሩ ሰንብተዋል።

ይህም የመንግሥትን ሕጋዊ የሆነ የኀይል ምንጭ ባለቤትንት፣ የኀይል ተዋረድ ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል። የፌደራል መንግሥትም የፀጥታ ሃይሎችን የኀይል አጠቃቀም የሚወስን አዋጅ እየረቀቀ መሆኑን ከገለፀ ሰንብቷል።

የኢኮኖሚ፦ አንድ አገር ጠንካራ የብሔር-ግንባታ ለማካሔድ አስተማማኝ የማክሮ ኢኮኖሚ መሠረት ሊኖራት እንደሚገባ ባለሞያዎች ይናገራሉ። በየዓመቱ ኹለት ሚሊዮን ሥራ ፈላጊ የሚፈጠር ሲሆን ኢኮኖሚው ግን መቅጠር የሚችለው ግማሹን ብቻ ነው። የትኛውም የአገር ግንባታ ከፍተኛ የሥራ አጥነት ጥያቄዎችን ካላቃለለ ስኬቱ ሩቅ ነው። በኢትዮጵያ የከተማ የሥራ አጥነት መጠን 16 በመቶ ሲሆን የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ደግሞ 22 በመቶ ነው። ይህ ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት ሥራ የማይፈለጉ ኅብረተሰብ ክፍሎችን ለምሳሌ እንደ የቤት እመቤቶችን የማያጠቃልል ነው። ወደ ሥራ ኀይል ያልገባ ነገር ግን በቅርቡ የሚገባው ቁጥር አንደ ኢትዮጵያ ላሉ እና ከ35 ዓመት በላይ የሆነው የሕዝብ ብዛቷ 70 በመቶ ለሆነ አገር የወጣቱን የሥራ ፍላጎት ማቃለል አገር እንድትቀጥል እስትንፋስ መስጠት ነው።

ሌላው የሕግ የበላይነትን በማስጠበቅ በተዘዋዋሪም የዋጋ ግሽበቱን በመቆጣጠር መንግሥት ሌላኛውን በተለይም የከተሜውን የኑሮ ጫና ማቃለል እንዳለበት አጥላው አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ቦታ የተትረፈረፈ ምርት በሌላ ቦታ እጥረት ሊኖር ይችላላም ይላሉ። በክልሎች መካከል በነፃ ገበያ መርህ ላይ ተመስረቶ ያመረቱትን ካልተለዋወጡ ኑሮ ውድነቱ ላይ ሌላ ጫና ይፈጥራል ይላሉ።

የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ባሳለፍነው ጠቅላላ የዋጋ ግሽበት በአምስት ወር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሲሆን፥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም 11 ነጥብ አንድ በመቶ እንዲያሻቅብ አድርጎታል።

ከሥራ አጦች ቁጥር ባሻገር 2.5 ሚሊዮን ተፈናቃይ በጊዜዊ ሥፍራዎች ተቀምጦ የመንግሥትን እጅ ይጠባበቃል። ይህ ሁኔታ ከሥራ አጥነት የከፋ የሚሆነው በአብዛኛው ሙሉ የቤተሰብ አባል አብሮ መሰደዳቸው፣ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸው በሌሎች ሰዎች እጅ ላይ መውደቁ እና ሥራ ለመፍጠር ወይም ለመቀጠር ተስፋቸው እጅግ የሳሳ በመሆኑ ነው።

ተፈናቀዮች ለረጅም ዓመታት በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ተሠማርተው ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን፥ በድንገት የሰው እጅ ተመልካች መሆናቸው በተለይ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የነበሩ ሰዎች ላይ ከባድ የሥነ ልቦና ጫና መፍጠሩም አይቀሬ ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው ገዢ ፓርቲ ምንም እንኳን ሙሉ ለሙሉ የፓርላማ ወንበሮች በመቆጣጠር በምርጫ 2007ን “አሸንፌአለሁ” ቢልም ታላቅ ተቃውሞ ግን መግጠሙ አልቀረም። ይህ ተቃውሞ እምብዛም ሳይቆይ የገዢው ግንባር ኢሕአዴግ አመራሮች በአዲስ ተተክተው የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ ሆል። ያለ ፓርቲ ለውጥ ወይም ሕዝባዊ ምርጫ ወደ ፊት የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር የመጀመሪያ ወራት ብዙ ተስፋ የተሞላበት እንደ ሕዝብም፣ አገራዊ መሥማማት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን የታየበት ነበር።

የሕግ የበላይነት
በዘመናዊው ዓለም አንድ አገረ-መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ በኹለት እግሮቹ ያቆሙታል ተብለው ከሚታመኑት ጉዳዮች አንዱ የሕግ የበላይነት ነው። የሕግ የበላይነት በሰፊው ትርጉሙ ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈፃሚው እና ተርጓሚው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሥራቸው አንዱ ያለሌላው ጣልቃ ገብነት እንዲሁም ሁሉም ከሕግ በታች የሆነው ሕዝብ የሚያገለግሉበት ነው።

ከዚህም ባሻገር ግብር የመሰብሰብ አቅም እና የንግድ መሥመር ሕጋዊነትን በበላይነት በመቆጣጠር ካልተቸለ የሕግ የበላይነት መከበር እውን አይሆንም።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 25 የተቀመጠው መርሕ ካልተተገበረ ባጭሩ የሕግ የበላይነት የለም ለማለት እንደሚቻል ማርሸት ይናገራሉ። የፌደራል መንግሥቱ በሕገ መንግሥቱ እንደሁም በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ካልቻለ የዜጎችን የእኩልነት መብት እየጣሰ ነውም ብለው ያምናሉ።

“በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በቀለም፣ በፆታ፣… በመሳሰሉት ልዩነት ሳይደረግ ዜጎች እኩል መብት የማግኘት መብት አላቸው” የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 25 እንደሚደነግገው።

ከዚህ በተጨማሪ የሕግ የበላይነትን ቅድሚያ መስጠት ያልቻለ እና በተለያዩ ማንነቶች ምክንያት ወንጀለኞችን የሚደብቅ ማኅበረሰብ ከመንግሥት የመፈፀም አቅም ማነስ ባለፈ የሕግ የበላይነት እጦትን ዕውቅና በመስጠት አገር በማፈራስ ሒደት ውስጥ ትልቁን ሚና ይጫወታል።

ማርሸት በአሜሪካ የፌደራል ስርዓት በየክልሉ የፌደራል ቅርንጫፎች እንደሚገኙ እና ይህም የፌደራሉን መንግሥት ተቋማት በክልልች ውስጥ ማጠንከር ይችላል ብለው ያምናሉ።

የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያልቻለው የፌደራሉ መንግሥት እንደ ምክንያት ከሚያስቀምጣቸው ነገሮች አንዱ የፌደራል ስርዓቱን መጠበቅ የሚለው ነው።

ብሔራዊ ጥቅም፦ ብሔራዊ ጥቅምን በተመለከተም መንግሥት በዜጎቹ ላይ የሚጭነው ዕዳ ሳይሆን ዜጎች በመሠረቱ መጠቀማቸውን አረጋግጠው ለመጪው ትውልድም የሚጠብቁት ዕሴት ነው። የሕዳሴውን ግድብ የብሔራዊ ጥቅም ሥዕል መንግሥት መስጠቱ ከላይ ወደታች በመምጣቱ ብቻ ብዙዎች አንደ ዕዳ ሲቆጥሩት እንደነበር ማርሸት ያነሳሉ። ግድቡ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ ኀይል ችግሩን ፈቶ እና የተባለውን የኢኮኖሚ ጥቅም አምጥቶ ሲያይ ሕዝቡም እንደ የጋራ ጥቅም በጋራ ሊጠብቀው እና ሊንከባከበው ይችላልም ይላሉ።

ኢሕአዴግ ከላይ እና ከታች
ገዢው ፓርቲ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ከሚታወቅባቸው መገለጫዎቹ መካለል ከማዕከላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ቀበሌ ካድሬዎች ድረስ ሳይነጋገሩ የሚግባቡ፣ “ለበጎም ይሁን ለክፉ” መተባበርን የሚያውቁ የነበሩ መሆናቸው ነው። ይሁንና አመራሮቹ በሕዝባዊ ተቃውሞዎች በመናጣቸው እና ተቋማዊ የአሠራር ለውጥ ለማምጣት ቃል በመግባት ለኹለተኛ ጊዜ በሕዝብ ይሁንታ የተተወላቸውን የለውጥ አመራር ከማስቀጠል ይልቅ በሚያደናቅፍ አካሔድ እየተጠመዱ ያሉት ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም።

ኢሕአዴግ ባልታሰበ መንገድ ከአንድ ዓመት በፊት ሊቀ መንበሩን ከቀየረ በኋላ የተወሰኑ ዋና ዋና የሥልጣን ሽግሽጎችን ያደረገ ቢሆንም፥ የስረኛው መዋቅር ግን በነባር ሰዎች ተይዞ እንደሚገኝ ይታወቃል። የቡድን ፖለቲካን የሚያቀነቅኑት የተለያዩ ትርክቶች እየተዘወተሩ መምጣታቸውን እና አቃፊ ብሔር-ግንባታ ፈንታ፣ ክልላዊ ማንነትን ብቻ መሠረት ያደረገ የአገረ-መንግሥት ግንባታ እየተዘወተረ መምጣቱን ተከትሎ የስረኛው መዋቅር የራሱን አጀንዳ በመያዝ አገሪቱን ወደ ግጭት አዙሪት ከቷታል።

ፓርቲው ሌላኛው የሚታወቅበት እና የቆየው የምስጢር ባሕሉ በፈጠረው አካሔድ፣ የዐቢይን አስተዳደር ወደ ፊት ያመጣውን የፓርቲ ውስጥ ትግል የፓርቲው የስረኛው መዋቅር ከሕዝብ እኩል የሰማው እንግዳ ዜናም ነበር። ይህም ለውጡ ካመጣጡ ጀምሮ ከሥር ወደ ላይ የተገነባ ሳይሆን ከለውጡ በኋላ በሚገነባው ከላይ ወደታች የሚመጣው የለውጥ ሽግግር የሚገነባ ሆኖ ይታያል።

ኢትዮጵያውያን ከአረብ አብዮት ምን ይማራሉ?
ዴሞክራሲን ለማምጣት በ2003 የጀመረው ‘የአረብ ስፕሪንግ’ የሚል ሥያሜ በምዕራባዊያን ብዙኀን መገናኛዎች የተቸረው እና በቱኒዚያ ተለኩሶ፣ ግብፅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ፣ ወዘተ. ያደራሰው አብዮት የታለመለትን የዴሞክራሲ ሕልም ከማሳካት ይልቅ ወደ እርስ በርስ ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ውድቀት እና በአንዳንዶቹ የአገር መፍረስንም ጭምር አስከተሏል። ፍራንሲስ ፉኩያማ ‘ፖለቲካል ኦርደር ኤንድ ፖለቲካል ዲኬይ’ በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ዓይነቱ ችግር የሚፈጠረው ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት በመገንባት መንግሥት ኀይልን ለብቻው መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ ታጣቂዎች እና የጎበዝ አለቆች በመጠናከራቸው ነው ይላሉ። ይህንን ክርክራቸውን ሲያስረዱም እ.ኤ.አ በ2013 የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አሊ ዘይዳን ክፍያ በሚጠይቁ አማፂዎች ታግተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በተመሣሣይም ሌላ የታጣቂዎች ቡድን የአገሪቱን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን የነዳጅ ምንጭ በመቆጣጠር ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመውም ነበር።

ፉኩያማ እንደሚሉት የኀይል የበላይነትን የተቆጣጠሩ አምባገነን መንግሥታት ዴሞክራሲን ፍለጋ ሕዝባቸውን ወደማያባራ የግጭት አዙሪት ከከተቱ፣ የተሻሉ ቢመስሉም እውነቱ ግን ከዛ የራቀ ነው። እንደ ኒጀር፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ ያሉት መንግሥታት አሁን የአክራሪዎች መነኻሪያ ከመሆናቸውም አልፎ ለጎረቤቶቻቸው የሥጋት ምንጭ ሆነዋል። በአንፃሩ ዓለምን በጠንካራ ኢኮኖሚዋ የምትመራው አሜሪካ በ2008 ያጋጠማትን የፋይናናስ ቀውስ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ከመፈታተን ባለፈ የኢኮኖሚውን ኅልውና የተፈታተነም ነበር ይላሉ። በተመሣሣይ ቱርክ እና ብራዚልም በአብዮት ከተናወጡት አገራት መካከል ናቸው።

እነዚህ ክስተቶች መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሕዝቦች የተነሱ አብዮቶች ናቸው ብለው የሚያመሣሥሏቸው ፉኩዩማ አዲስ የሚፈጠረው ወጣት ትውልድ ከወለጆቹ የተለየ አዳዲስ ጥያቄዎችም አሉት ይላሉ። እነዚህ አቢዮቶች የተነሱበትን ዓላማ አሳክተው አገራቱ ወደ ነበሩበት ወይም ከነበሩበት ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማስገባት የተቋማቶቻቸው ጥንካሬ ይወስነዋል። በተለይም ጠንካራ እና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ፣ ለፓርቲ ወይም ለስርዓት ያልቆመ የደኅንነት መሥሪያ ቤት፣ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤቶች፣ የመከላከያ ሠራዊት እና ጠንክሮ የቆመ ቢሮክራሲ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ታዲያ አብዛኛዎቹ አምባገነን ስርዓቶች ገዢ ፓርቲውን ወይም የስርዓቱን እጅ ወደ እነዚህ ተቋማት ስለሚሰዱ ከስርዓቱ መገርሰስ ጋር አብረው መገርሰሳቸው የማይቀር ይሆናል።

የብሔረ-መንግሥት ግንባታም በዋናነት ማተኮር ያለበት በዚህ ዙሪያ ነው ካልን አንድ መንግሥት ከዕለት ተዕለት የቤት ሥራዎች በመውጣት ለእነዚህ ተቋማት መሠረት የመጣል ኀላፊነቱ ለነገ የሚባል አይሆንም። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየተደረገ ያለው ለውጥም ከተጋረጡበት ዋና ዋና ችግሮች አንዱ የእነዚህ የጀርባ አጥንት የሚባሉ ተቋማት ሕወሓት መራሹ መንግሥት ከሥልጣን መገለል ጋራ አብሮ የመጣ መታወክ መሆኑን መንግሥት በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ ያምናል።
ታዲያ ጠንካራ መንግሥትን ለመገንባት አስኳል የሆኑትን እነዚህን ተቋማት የመገንባቱ ሥራ በየዕለቱ በሚከሰቱ ግጭቶች እና የተለያዩ ቀውሶች ውስጥ ሆኖ የማሳከቱ ነገር ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀርም። የተለያዩ መሠረታዊ መሻሻሎች ተደርገውለት ከዚህ ቀደሙ በበለጠ ቴክኖሎጂ እና አቅም ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው መከላከያም፣ ፖሊስ በዕለት ተዕለት ሥራው ማስጠበቅ በሚገባው የውስጥ ሰላም የማስከበር ተውጦ ይውላል።

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ለሕዝብ ቃል ከገቧቸው ነገሮች አንዱ በሥራ ቀን ስብሰባን ማስቀረት ቢሆንም የስረኛው የቢሮክራሲ መዋቅር ግን ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል። የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ካቢኔ ግን በዚህ ደንብ ተገዝቶ ምሳሌ ለመሆን ቢሞክርም በፓርቲ መዋቅር የተሸበበው ሲቪል ሰርቫንት ግን ለውጡን መሸከም መቻሉ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ማንኛውም የአገር ግንባታ ሥራ የመንግሥት አገልግሎትን ማቀላጠፍ እንዲሁም በሥነ ምግባር የሚመራ ማድረግ ዋና አላማው መሆን አለበት ከተባለም ከፓረቲ ጫና ወይም መጠቀሚያነት ወጥቶ ዘመን የሚሸገር የተቋም ግንባታ ከሚያሰፈልጋቸው ዘርፎች አንዱ ይህ ነው።

ምንም እንኳን እንደ ፕሮፌሰር ክርስቶፈር ክላፋም ያሉ ፀሃፊዎች ኢትዮጵያ በቢሮክራሲ ደረጃ ጠንካራ የሚባል መሰረት አላት ብለው ይከራከራሉ። “ስቴት ፎርሜሽን ኤንድ ዲኬይ ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ” በሚለው መጽሐፋቸው ክርስቶፈር ኢትዮጵያ በ1966ቱ አብዮት እንዲሁም በ1983ቱ የስርዓት ለውጥ ወቅት የመንግሥት ሥራ አለመቋረጡን እንዲሁም የደመወዝ ክፍያም ያለመዘግየቱ ብረቱ መሰረት ላይ የቆመ ቢሮክራሲ እንዳለ ይናገራሉ። ይህ ባይሆን ግን መልሶ ለማንሰራራት የሚያስቸግር የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ሊገባ ይችላል ይላሉ።

እንደማጠቃለያ
መንግሥት የአገር ግንባታ ላይ ትኩረቱን እንዳያደርግ ያደረጉትን የውስጥ ቀውሶች ክልሎችም ሆኑ የፌደራሉ መንግሥት ጊዜ ሳይሰጡ ማቆም ይገባቸዋል። ይህንን በማድረግ ወቅት የፌደራል ስርዓቱን ተከትሎ በሕገ መንግሥት የተሰጧቸውን መብቶችም ያለከልካይ መጠቀም አለባቸው።

እነዚህን ሥራዎች ለማከናወን የሕግ ማዕቀፎችን በማዘጋጀትም ጭምር መሆን እንደለበት ማርሸት ይከራከራሉ። ለምሳሌ በክልሎች መካከል የወንጀለኛ ልውውጥ ለማደረግ ቢያስፈልግም እንኳን የሚስችል ሕግ እንደሌለ ይናገራሉ። የፍርድ ቤት ማዘዣ በየትኛውም ክልል ተፈፃሚ የሚሆን ቢሆንም ትዛዙን ለመፈፀም ግን የክልል የፀጥታ ኀይሎች በቀላል ምክንያት ሊያፈገፍጉ ይችላሉ።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአገር ግንባታ የሚጀመረው ከሕዝብ ውክልና ያገኘ መንግሥትን በመምረጥ ነው ካልን መንግሥት የሕግ የበላይነትን ባስቸኳይ አስከብሮ የምርጫ ዝግጅት በማድረግ አገርን ከመምራት ባሻገር የኅልውናዋን ጥያቄ መመለስ አለበት። ለዚህም እንደማሳያ መጋቢት 20 ሊደረግ የነበረውን አገር ዐቀፍ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ እንኳን ማካሔድ ያለመቻሉ የሕግ የበላይነት ካልተከበረ የፖለቲካ ሥልጣን ለውጥ ውጤት የሚያመጣውን ብሎም በጠነከሩት አገራትም ግርግር የማያጣውን ምርጫ ማካሔድ ዘበት ይሆናል።

ምርጫን ከማካሔድም ባለፈ ብሔራዊ ጥቅምን ቅድሚያ በመስጠት ሕዝቦችን የሚያስማሙ አጀንዳዎችን መቅረፅ እና የጠንካራ አገር መገለጫ ተቋማትን በማጠንከር ጉዞውን መጀመር አለበት። ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት፣ ኀያላን አገሮች እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዳከም ጥቅም የሚያገኙ አካላትን በማቋቋም ሕዝብን መምራት አማራጭ አይኖረውም።
መንግሥት በግለሰቦች፣ በቡድኖች አንዳንዴም በክልል ደረጃ ያሉ ያለአግባባ የተያዙ የኅይል ምንጮችን ወደ ሕጋዊው መሰረት በመሰብሰብ የሕግ የበላይነትን ከማስከበርም ባለፈ የዜጎችን እልቂት ማቆም አለበት።

በተጨማሪም ዜጎች እና ሕዝቦች የግንኙነት መንገዳቸውን ግልፅ በማድረግ በጋራ እኩልነት ላይ መመስረት አለበት።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here