የሥልጣን ክፍፍል ነገር

0
803

የፌዴራሊዝም ዋነኛ መርሕ የመንግሥት ሥልጣንን ያልተማከለ ማድረግ ነው። ይህም “የወል እና የተናጠል አመራር” (‘ሰልፍ ኤንድ ሼርድ ሩል’) በተባለ መንገድ ይፈፀማል። የጋራ አመራሩ በፌዴራል መንግሥቱ አማካይነት የሚከናወን ሲሆን፥ የተናጠል አመራሩ ደግሞ በክልል መንግሥታቱ አማካይነት የሚፈፀም ነው። የሥልጣን ክፍፍሉ እና ኢ-ማዕከላዊነት ወደታችኛው እርከንም መውረድ ስለሚኖርበት፥ እያንዳንዱ ወረዳ ድረስ የየራሳቸው ሥልጣን ይኖራቸዋል።

በሌላ በኩል የዴሞክራሲ አንዱ መርሕ ሥልጣን በአንድ አካል ብቻ ተከማችቶ እንዳይኖር ማድረግ ነው። በዴሞክራሲያዊ አመራር ውስጥ የመንግሥት ተቋማት እርስ በርስ ቁጥጥር የሚያደርጉበት እና ሚዛን የሚጠብቁበት አሠራር የሚፈጠረው የሥልጣን ክፍፍል ሲኖር ነው።

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ማንነትን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ምክንያት በርካታ ትችቶች ቢኖሩበትም፥ ለዚህ የሥልጣን ክፍፍል ተገዢ መሆን ግን ይችላል። ይሁን እንጂ የአውራ ፓርቲ ስርዓት በፈጠረው አስተዳደር ውስጥ መሬት ላይ የወረደ የሥልጣን ክፍፍል ሳይኖር ቀርቷል። ራሱን “አውራ” ፓርቲ ብሎ የሰየመው ኢሕአዴግ የሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና “የተማከለ ዴሞክራሲ” የሚል መርሕ ያለው መሆኑ በላይኛው የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የተወሰነውን በሙሉ በታችኛው የሥልጣን እርከን ያሉ ሰዎች ሁሉ ያለምንም ማንገራገር የሚፈፅሙበት አሠራር ተዘርግቶ ከርሟል። ይህ የፌደራል ስርዓቱን የይስሙላ አድርጎት ከርሟል።

በመሆኑም ባለፉት ዓመታት የነበረው አሠራር የፌዴራል መንግሥቱ አለቃ፣ የክልል መንግሥታቱ ደግሞ ምንዝር የነበሩበት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ የሥልጣን ክፍፍል እንዳይኖር እና እንዳይተገበር ማድረጉ አልቀረም። አሁን የፖለቲካ ተሐድሶ ሲካሔድ ደግሞ ክልሎች ሥልጣናቸው አላግባብ ተለጥጦ አዲስ ፈተና ሆኖ የመጣው ክልሎች ለፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣን አናጋራም ማለታቸው ነው።

ሥልጣን በቀዳሚ ስርዓቶች የተማከለ በመሆኑ ምክንያት ክልሎች እና የአካባቢ አስተዳደሮች ሥልጣን መጋራት አልተቻላቸውም ነበር። አሁን ደግሞ በተቃራኒው ክልሎች ለማዕከላዊው መንግሥት ሥልጣን አናጋራም በማለት ላይ ናቸው። ኹለቱም ፅንፍ የነኩ አካሔዶች ሲሆኑ ከዴሞክራሲም ይሁን ከፌዴራሊዝም ስርዓታት አንፃር የማያስኬዱ አሠራሮች ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here