በሶማሌ ክልል በየቀኑ ከ1600 በላይ የቁም እንስሳት በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር ይወጣሉ

0
788

በሶማሌ ክልል በየቀኑ 1 ሺሕ ግመሎችና 600 ፍየሎች በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት አገራት እንደሚሻገሩ ተገለፀ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ ክልሉን ተዘዋውሮ በጎበኘበት ወቅት እንደታዘበው የተጠቀሰው ቁጥር ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ውስጥ በተወሰኑ ከተማዎች ብቻ የተገኘ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ተናገሯል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጌታቸው መለሰ እንዳስታወቁት ቋሚ ኮሚቴው በሶማሌ ክልል በጅግጅጋና ቶጎ ጫሌ ባደረገው ምልከታ የሕገ ወጥ ንግዱ በጣም ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑንም አስታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የአማደሌ የቁም እንስሳት ማቆያ ጣቢያ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተገንብቶ ባለመጠናቀቁ ለሕገ ወጥ ንግዱ መባባስ እንደምክንያት ተነስቷል።
ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ የሕገ ወጥ ንግዱ መባባስ ኢትዮጵያ የቁም እንስሳትን ወደ ውጭ በመላክ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረትም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ በዘርፉ ሊሰማሩ በዝግጅት ላይ ያሉ ባለሃብቶችንም የሚያዳክም በመሆኑ በአፋጣኝ መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ጨምረው ተናግረዋል።

ሰብሳቢው እንደገለጹት የቁም እንስሳትን በሕገ ወጥ መንገድ ማስወጣቱ ብቻ ሳይሆን በሕገ ወጥ መንገድ ደግሞ ወደ አገር ውስጥ ምን ሊገባ እንደሚችል ማሰብ ይኖርብናል ብለዋል። አያይዘውም የሕገ ወጥ ንግዱ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቁም እንስሳት እጥረት እንሚያስከትልም ሳይጠቁሙ አላለፉም።

ከቁም እንስሳት እጥረት ጋር በተያያዘ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ2011 ዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸምም ወቅት እንደተገለፀው በስድስት ወራት ብቻ ሰባት የውጭ ንግድ ቄራዎች 1 ሽሕ 180 ነጥብ 5 ቶን የሥጋ ትዕዛዝ የዕርድ እንስሳት እጥረት በማጋጠሙ ሳይልኩ መቅረታቸውን ገልጿል። በዚህም ሳቢያ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር በአማካኝ ሳይገኝ ቀርቷል። የዘርፉ የወጪ ንግድ 98 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው ሥጋ ምርት በመሆኑ ጉዳቱን ከፍተኛ ያደርገዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቀዳሚ ተረካቢ ከሆኑት አገራት ሳኡዲ አረቢያ እና ዱባይ በተጨማሪ ወደ ሌሎች አገራት ከተላከው 1 ሽሕ 750 ቶን የሥጋ እርድና ተረፈ ምርቶች 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን ይህም አፈጻጸሙም ከጠቅላላ ገቢ 11 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here