ምነው በሴቶች ላይ “መቀነስ” በዛ?

0
719

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ያደረጉትን ውይይት መነሻ በማድረግ በተለይ ለሴት ሐኪሞች ጥያቄዎችና የሥራ ላይ ተግዳሮትን በተመለከተ የተሰጡትን ምላሾች በመተቸት ቤተልሔም ነጋሽ ይህንን ጽሁፍ አዘጋጅተዋል።

 

 

በሥራ ላይ ከቆየሁባቸው ዓመታት አንጻር ምናልባት በሕይወቴ ካገኘኋቸው ዕድሎች ሁሉ ወርቃማ የምለው ገና በጠዋት ሌላ አገር ሔዶ ለመሥራት ያገኘሁት ዕድል ነው። በሉሳካ ዛምቢያ የአንድ ዓመት ቆይታ በኹለት ዕለታዊ ጋዜጦች ላይ የመሥራት ልምድና በባለሙያ ልውውጡ ተሳታፊ የነበረው ተቀባዬ የዛምቢያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያ ሴቶች ማሕበር ያካሒዳቸው በነበረው መርሃ ግብሮች ላይ መሳተፍን ያካተተ ነበር።

የዛሬ ዐሥራ ሦስት ዓመት ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓስፖርት አውጥቼ ከአገሬ ልወጣ ስነሳ ለአንድ ዓመት የሥራ ቆይታ ነበር። የዛምቢያ ቆይታዬ ገጠመኝ ይቆይና ለዛሬ ጽሁፌ ማጣቀሻ የሚሆነውን የዛምቢያ ልምዴን ልጥቀስ። በጠቀስኩት ወቅት ዛምቢያ በለጋ ታዳጊ ሴቶች እርግዝና ምጣኔ ከደቡባዊ አፍሪካ አገሮች ተጠቃሽ ነበረች። ምናልባት ከኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀር የሰውነት ዕድገታቸው በጣም ፈጣን የሚባል ሆኖ፣ በሌሎችም ውስብስብ ባሕላዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የ13 እና 14 ዓመት ታዳጊ ተማሪዎች የሚያረግዙበት አጋጣሚ ከፍ ያለ ነበር። ታዳጊዎቹ እርግዝናው ሲገፋና መውለድም ሲመጣ ትምህርታቸውን ማቋረጥ ከዚያም አልፎ ምናልባት ደጋፊ ተቀባይ ቤተሰብ ከሌለ ወጥቶ መቅረት ቢኖርም ተመልሶ ወደ ትምህርት ለመመለስ ሌላ ዓመት ማጣት ወዘተ ነበር። ከዚያ ምናልባት እንደኛ አገር ቢሆን “ባሕል ጠፋ፣ ተበላሽ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ ይፈቀድልን መድኀኒቱ እሱ ነው” ተብሎ የመታለፍ ዕድል ያለው ጉዳይ ብሔራዊ አጀንዳ ሆነ። እንደ ታንዛንያው ማጉፉሊ በቃ የራሳቸው ጉዳይ ሕይወታቸውን በገዛ ራሳቸው አበላሹ እንዳውም ወይ ያግቡ አልያ ትምህርት ቤት መመለስ እንዳያስቡት አልተባሉም። ከዚያ ተማሪዎቹ ልጅ ከወለዱ በኋላ ተመልሰው ትምህርት ቀጥለው ውጤታማ ዜጋ የመሆን ዕድላቸውን እንዲያሰፉ የሚያስችል ልዩ ድጋፍና ፈተና የማካካሻ ክፍለ ጊዜ የሚደራጅበትን የሚዘረዝር ፖሊሲ ወጣ። ምናልባት በጋዜጠንነት ሥራዬ ዛምቢያ ላይ ካጋጠሙኝ በጎ ልምዶች ይሔ አንዱ ነው።

ይህን ጉዳይ ምን አስታውሰኝ – ሰሞኑን ሴት ሐኪሞች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት ያሰሙት ጆሮ ያጣ ብሶት። መቼም በዚሁ ጋዜጣ የተዘገበውን ጨምሮ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተለማማጅ (ኢንተርን) ሐኪሞች ቀጥሎም ሌሎች በየጤና ፋኩልቲው በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ ያሉ ሐኪሞችን ጨምሮ የተካሔደው የሐኪሞች ሰላማዊ ተቃውሞና ዘመቻ የሚዲያውን ትኩረት ስቦ ሰንብቷል። ማኅበራዊ ሚዲያን ጨምሮ በብዙ መድረኮች የተነሰው የሐኪሞች ለመስማት የሚከብድ ችግርና መዋቅራዊ እንዲሁም የፖሊሲ መልስ የሚሻ ለዘመናት የቆየ ብሶትና አለመመቸት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ያልተጠበቀና ብዙዎችን ያሳዘነ ምላሽ ጋር እየተነፃፀረ በስፋት ሲቀርብ ከርሟል። በቴሌቪዥን የተላለፈው የጥያቄና መልስ ሁኔታ ከሌሎች ሙያተኞች ሳይቀር ተቃውሞ ሲገጥመው ሐኪሞችን “ከጎናችሁ ነን” እያለ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻውን እንዲቀላቀል መነሻ ሆኗል። ሐኪሞችም በተቃውሞ ዘመቻው እንዲገፉ ሆኗል። በማኅበራዊ ሚዲ ከቀረቡ መካከል ሐኪም በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ የቀረበውን ለምሳሌ ብናይ፤ ዶ/ር ሰምሀል ብርሃነ መስቀል የተባሉ ሐኪም እንዲህ ብለዋል።

“ጥያቄዎቻችን ሕመምተኞቼን መሬት ላይ፣ ወንበር ላይ፣ ሳጥን ላይ፣ ጠረጴዛ ላይ እና የተሰበረ አልጋ ላይ ከማክም የተመቸ አልጋ ላይ ተኝተው ላክም ነው።

ድምጻችን በምጥ ላይ ያለች እናት በፈረስ ላይ ተጭና እየተንገላታች ራሷንም ልጇንም አደጋ ውስጥ ከታ ከምትመጣ በአንቡላንስ ከጤና ባለሙያ ጋር ወደ ሆስፒታል ትምጣ የሚል ነው።

እንባችን በሳምንት 2 ሕፃናት ብቻ በልብ ቀዶ ሕክምና ታክመው ከሚድኑ 7 ሕፃናት ይዳኑልን የሚል ጭምር ነው።
ድካማችን የተለያዩ ለሕክምናው አገልግሎት የሚጠቅሙን የምርመራና የሕክምና መሣሪያዎች ወደ ሆስፒታል ይግቡና ታካሚው ከዚህ እዛ ከሚንገላታ ጊዜና ገንዘቡን በመቆጠብ የሚያስፈልገውን ግልጋሎት ያግኝ የሚል ነው።
ይህ ከሐኪም አንደበት ወጣ እንጂ የብዙዎች ኢትዮጵያውያን መልስና መፍትሔን የሚሻ ጥያቄ ነው!”
እውነት ብለዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው መልስ አበሳጭነትና ጨርሶ የማይገናኝ መሆኑን የሚያሳዩ ደግሞ የሚከተሉት ናቸው ።

“የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች ውስጥ አልጋ ጠፍቶ በሽተኛው መሬት ላይ እየተኛ በሚታከምበት ሁኔታ ስለ ጤና ቱሪዝም ይጠየቃል? እንግዳ ከውጭ አገር ሲመጣብን የምናሳክምበት ቦታ የለንም ይባላል?” – ዶ/ር ሮዳስ ካሳሁን
“ሐኪሞች ፖለቲካውን ተውትና ሥራችሁን ሥሩ ደሞዛችሁም የሕሊና እርካታ ነው የምትል የሽንገላ አስተያየት ሰለቸችኝ!” – ዶ/ር ካሳው ጥጋቡ ከጎንደር
ሌሎችም አሳዛኝ መልሶች ነበሩ። ዛሬ ላተኩርበት የፈለኩት ግን ሴት ተለማማጅ (ኢንተርን) እና ስፔሻላይዜሽን የሚማሩ (ሬዚደንትስ) በሕግ የተፈቀደውን የወሊድ ዕረፍት የሚከለከሉበት አግበብ እና በሥራ ላይ የሚደርስባቸው ተደጋጋሚ ያነሱት የፆታዊ ጥቃት ጉዳይ ነው።

በነገራችን ላይ አንዷ ሐኪም ሲቃ እየተናነቃት ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ገና ባንድ ወሬ ልጅሽን ትተሸ ሥራ ግቢ ተባልኩ” ብላ አስተዛዝና ብትጠይቅ “ጉዳይሽ የግል ነው፥ ከአሚር ጋር ጨርሺ” ብለዋታል። ይሔ ግን የፖሊሲ ጉዳይ እንጂ የግል ጉዳይ አይደለም። ብዙ ሴት ሐኪሞች የሚያልፉበትም መከራ እንጂ።

ስድስት ወር ጡት አጥቡ እያለ በእርዳታ ብር ማስታወቂያ ሲያስነግር የሚውል ሚኒስቴር፥ የገዛ ሠራተኞቹንና በጤናው ዘርፍ የእናቶችን ሕይወት ለማዳን የሚሠሩ ሴት ሐኪሞችን የሕፃናት ማቆያ (ለሌላ መንግሥት ሠራተኞች የተደነገገ መብት) በሌለበት የአንድ ወር ልጅ ትታችሁ ሳታገግሙ ሥራ ግቡ ማለት ትንሽ ተቃርኖ የለውም?

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሠራተኛ ሕግ መሠረት ለማንኛውም መደበኛ ሥራ ተቀጣሪ ሴት ሠራተኞች 12 ሳምንት ወይንም ሦስት ወር የወሊድ ዕረፍት (4 ሳምንት ወይም አንድ ወር ከወሊድ በፊትና 8 ሳምንት ወይም ኹለት ወር ከወሊድ በኋላ) ዕረፍት ማግኘት መብት አለ። በተሻሻለው የመንግሥት ሠራተኞች ሕግ ደግሞ ይኸው ረፍት ወደ አራት ወር ከፍ እንዲል ሆኗል። ተለማማጅ ሐኪሞችና ሪዚደንቶች በዚህ ሕግ እንዲዳኙ ማድረግ ከሥራቸው ባሕሪ አንፃር ቀላል ነው ባይባል እንኳን የተለየ ሁኔታውን የሚያስተናግድ ከላይ እንደገለጽኩት ያለ ፖሊሲ ሊወጣ ግድ ነው። የኢትዮጵያ ሴት ሐኪሞች ማኅበር እንደሚለው የሴት ሐኪም አባላቱ ቁጥር 2000 ደርሷል። ይህ ደግሞ ቀላል ቁጥር አይደለም። ወደ ሙያው ብዙ ሴቶች እንዲገቡና ሥራ ላይ እንዲቆዩ ከማበረታታትም አንፃር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

የሴት ሐኪሞች የወሊድ ዕረፍት ዕጦና በሕግ የተደነገገ መብትን የመከልከል ጉዳይ ካለፈው ቅዳሜ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አመፅና ዘመቻ የወለደው ጥያቄና መልስ በፊትም ይነሳ የነበረ ነው። ለአብነት ከዚህ በታች ያሉትን ኹለት ምሳሌዎች አሳያለሁ።
“በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ሕግ መሰረት አንዲት እናት ከመውለድዋ በፊት አንድ ወር ከመውለድዋ በኋላ ሦስት ወር የወሊድ ዕረፍት እንዲሰጣት ተደንግጎ ይገኛል። በሕክምና ትምህርት ቤቶቻችን ላይ ግን ይሔ አይስራም! በተለይም በሬዚደንሲ መርሃ ገብር ላይ ያሉ ሴት ሐኪሞች ወልደው በአንድ ወር ውስጥ ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ይደረጋል። ወደ ሚሠሩበት ተቋም ተመልስውም ሕፃን ልጆቻቸውን በቅርበት የሚክታተሉበት የሕፃናት ማቆያ የላቸውም። ስለዚህ ሴት ሐኪሞቻችን ፈታኝ በሆነ ሁኔታ እንዲያልፉ፣ አልያም ለልጃቸው ሲሉ ትምህርታቸው ያቋርጣሉ። አንድ ሕፃን ልጅ የእናት ጡት ብቻ መጥባት ያለበት እስክ 6 ወር ነው። ታድያ እነዚህ ሐኪም እናቶች እንዴት እና በምን ሁኔታ ሆነው ነው ይሔንን ማድረግ የሚችሉት? ሊታስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው!” -ዶ/ር ሄለን ቴዎድሮስ

ሐኪም ባለቤት የያለችውና በነፍሰጡርነት ጊዜዋ አብሯት የተነሳውን ፎቶ አብሮ ለጥፎ ዘመቻውን ሐኪም በተሰኘው ሶሻል ሚዲያ ገጽ ያጋራው ፍፁም ደመላሽ የተባለ ግለሰብ በበኩሉ እንዲህ ብሏል።

“ሥሜ ፍፁም ደመላሽ ይባላል። መሐንዲስ ነኝ። ዶክተር ሔመን ከተባለች ሐኪም ጋር ትዳር መስርቻለሁ። የሥርዓቱን ስቃይ ያየሁት ባለቤቴ ስታረግዝና ከጥቂት ጊዜ በፊት የመጀመሪያ ልጃችንን ወልዳ ወዲያውኑ ወደ ሥራ ስትመለስ ነው። ይታያችሁ እስከ መውለጃዋ ቀን ድረስ ሥራ ላይ ነበረች። ጨቅላ ልጇን ትታ ሥራ መጀመሯ ሞራሏን ጎድቶታል። ይሔ በምንም መልኩ ተቀባይነት ያለው አሠራር አይደለም። የትኛውም አሠራር ሴትን ከልጇና ከሥራ እንድትመርጥ ሊያስገድዳት አይገባም። በየዕለቱ ሕይወት ለማዳን የሚጥሩ ሐኪሞችን እደግፋለሁ። ሴት ሐኪሞች የራሳቸው ቤተሰብ እንዳይኖራቸው የማይፈቅድን አሠራር ግን አልደግፍም”

ሌላ የሐሳባቸው ደጋፊ በበኩሉ “እኛን ለማከም እነሱ መታመም የለባቸውም። ሐኪሞችና የሕክምና ትምህርት ተማሪዎች ከሁሉ የተሻለ የወሊድ ዕረፍት ያስፈልጋቸዋል” ብሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ “ፌሚኒስት ነኝ” ብላ ወደ ጥያቄዋ ያለፈችን ሴት ሐኪም “ፌሚኒስትነት ይቅርብሽ ሐኪምነቱ ይበቃሻል እናቶችን ካከምሽ ወዘተ” ማለት 50 በመቶ ውክልናውን እኛ እንሠራበታለን ማለት የሚያስተዛዝብ መሆኑን ሳልጠቅስ አላልፍም። እኛ እናውቅላችኋለን ማለት በአገሪቱ የሴቶች ጥያቄ ሙሉ እንደተመለሰ አድርጎ ማጣጣል ከዚህ በፊት እዚህም እዚያም የሰማናቸው ትናንሽ የሚመስሉ አግባብ ያልሆኑ ስለሴቶች የሚነገሩ ነገሮች ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ለሴቶች ያለውን ቦታ እንድንጠይቅና እስከዛሬም ተወሰዱ ብለን በትንሹ ስንደሰትባቸው የነበሩ እርምጃዎችን እውነተኛ ምክንያት እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው።

በተረፈ “የሴት ኢንተርኖች ሥራ በአዳር ጊዜ ወንድ ሬዝዳንቶችን ማስደሰት ነው” የሚባለውን ጉድ በሌላ ቀን ብንመለስ የተሻለ እንደሆነ በማመን ጉዳዬን ሳበቃ ርዕሴን የወሰድኩበትን የአንድ ሐኪም አባባል ጠቅሼ ላብቃ።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕክምናው ጉዳይ ተቀነሱ”። እኔም ምነው በሴቶች ላይ “መቀነስ” በዛ!

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here