ሴትነትና የሙዚቃ ቪዲዮ

0
614

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

እስቲ እንወቃቀስ! በፊልሞቻቸን ላይ የሚሳሉ ሴት ገጸ ባሕርያት ትክክል እንዳይደሉ ታዘበን ተቃውመናል። በአገራችን ፊልሞች ሴት ልጅ ገንዘብ ወዳድ፣ አልቃሻ፣ ጥገኛ፣ በአቋራጭ የምትጠቀምና ተንኮለኛ ወዘተ ተደርጋ ብቻ ትሳላለች፤ የዚህም ተጽእኖ በየኑሯችን ገብቶ ታይቷል።

እንግዲያው በሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ ያሉትስ ሴቶች ምን መልክ አላቸው? አኳኋናቸው ምንን ይገልጻል? ማንን እንዴት ነው ያጀቡት? እውነት የምናየው ውዝዋዜ ነው ወይስ ሌላ? የፊልሙን የምንቃወም ከሆነ ይህን “ተዉ!” የማንልበት ምክንያትስ አለ?
በሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ በተራቆተ ልብስ ገላዋን ለማጀቢያነት ያቀረበችው ሴት ለእኔም እህቴ ናት። እርሷ ያንን ያደረገችው ፈልጋ፣ ሰውነቷ ልከኛ ስለሆነ እንዲታይላት፣ ውበት ስለሆነ እንዲደነቅና ሙዚቃውን እንዲያደምቅ ወይም የራስ መተማመን መገለጫ አድርጋው! አላውቅም። ነገር ግን ይሄ የሴቶችን ውበትና ገላ፣ እርቃንና አማላይ እንቅስቃሴ እንደሸቀጥ ማድመቂያ ጌጥ መደረጉ እየተለመደ መምጣቱ ያስቀይማል።

ይሔ ሥልጣኔ ሆኖና እኔን ሳይገባኝ ቀርቶ ይሆን? ይህንንም አላውቅም። ግን ልንወቃቀስበት ይገባል ባይ ነኝ። በእኔ እምነት ከፊልሞቻችን የጎደለው በሴት ላይ የሚደረገው ጥፋት ሁሉ በሙዚቃው ተክሷል¡ ፊልሞች ሊያሳዩት ያልቻሉትንና ሊያደርጉ ያልደፈሩትን የሙዚቃው ቪዲዮ አድርጎታል፤ አራቁቶናል። “ከኋላዋ!” ብለው እየዘፈኑ “የኢትዮጵያን ታሪክ ማለታችን ነው” ብለው ቀልደዋልም።

ነገሩ ሴት ልጅ ይህንን ትልበስ አትልበስ አይደለም። ያሻትን ትልበስ ብለው የሚከራከሩ፣ እንደፈለገች እርቃኗን እንድታሳይ የሚያደፋፍሩት፤ አለባበስን የክብር መገለጫ አድረገው የሚቆጥሩና ስለአለባበሳቸው የሚጠነቀቁት ናቸው። ስለዚህ የአለባበስን ነገር ለለባሹና ለቻይና እንተወዋለን። በቪዲዮዎቹ የሚታዩ ውዝዋዜ ለማለት የሚቸግሩ እንቅስቃሴዎች ግን ሴትን የምትወርድና የምትሰቀል ጌጥ አድርጓታል፤ ይህ ደግሞ ደስ አይልም።

ማንኛውም ዓይነት የቪድዮ ሥራ ላይ ማንኛውም ሰው ሊሳተፍ ይችላል። ሙዚቃም ከሆነ እንደ መልዕክቱና እንደሚተላለፍበት ዓውድ፤ ጥበባዊ ውበትን /aesthetics value/ ጠብቆ ሊሠራ ይችላል። ደግሞም ብዙና ውብ ባሕል በታደለች አገር ነገሩ አይጠፋንም። የዳሌ ውዝዋዜና የደረት ምት ለአገራችን አዲስና ልዩ የጭፈራ ዓይነት ባለመሆኑም “ከየት የመጣ ጭፈራ ነው?” አንልም።

ይሁንና ግን ልዩነቱ ምን እንደሆነ የሴቶቹ አኳኋን በሚገባ ይነግረናል። ሰውነታቸው ስለመታየቱ ብቻ ሳይሆን በገጻቸው ላይ ስለሚተላለፈው መልዕክት ነው። ውበትን አናይም፤ መጠቀሚያነትን እንጂ። ምንአልባት እንደፊልሙ ሁሉ የሙዚቃ ቪዲዮም በወንዶች ቁጥጥር ሥር ስለሆነ ይሆን? እነዛ ሴቶች ግን ምን ያህል ቢከፈላቸው ነው? የት ነው የሚኖሩት? ዘመድ የላቸውም ወይ? እላለሁ። ምክንያቱም እኛ አውሮፓውያን ወይም አሜሪካውያን ወይም ሌላ ሳንሆን ኢትዮጵያውያን ነን፤ ማለትም አንጠቀመው እንጂ ለሰው ልጅ ክብር ያለው ባሕል አለንና!

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here