ኢዜማ የተባለ ፓርቲ ተቋቋመ

0
512

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተባለ አዲስ ፓርቲ ሐሙስ፣ ግንቦት 1 በደማቅ ሥነ ስርዓት በአዲስ አበባ ስብሰባ ማዕከል ተመሠረተ፡፡ ኢዜማ ማኅበራዊ ፍትሕና የዜግነት ፖለቲካ መብቶችን በማስከበር ላይ የሚያተኩር መሆኑን አሳውቋል፡፡
የኢዜማ አደራጅ ግብረ ኀይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ማለዳ እንደስታወቁት በምሥረታ ጉባዔው ላይ ከመላው ኢትዮጵያ 312 የምርጫ ወረዳዎች የተውጣጡ 1467 ወኪሎች ለምሥረታው መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲያቸው ያልተማከለ የአስተዳደር ስርዓትን ለመገንባትና የግለሰቦችን መብት ለማስከበር የማዕዘን ድንጋይ ያደረገና በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጥ ፕሬዘዳንታዊ ስርዓት ለመመሥረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

ኢኮኖሚን በተመለከተ ኢዜማ የሚመሠርተው መንግሥት ከግለሰቦች ጋር ሳይወዳደር በእርሻና በኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ የተናገሩት ናትናኤል፣ ኢትዮጵያ በዓለም ዋነኛው የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ በቅድመ ምሥረታ ወቅት ፓርቲው ዝርዝር የፖሊሲ ዝግጅት መቅረፁንም ገልጸዋል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ በማደረግ የሚታወቁት አንጋፋ ፖለቲከኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ የንግግራቸው ማጠንጠኛም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ዴሞክራሲያዊ የሆነ ፓርቲ የመኖርን አስፈላጊነትን አፅንዕት ሰጥተው መናገራቸውን እንዲሁም ከእስከ ዛሬው የፖለቲካ ፓርቲ አካሔድ ተመክሮ መውሰድ እንደሚገባ ለጉባዔተኛው ተናግረዋል።

ጉባዔው በሐሙሱ ውሎው የፓርቲውን ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብ እና ዓርማ ማፅደቁ የታወቀ ሲሆን በአርቡ ውሎው ደግሞ የሥራ አስፈፃሚውንና የፓርቲውን ሊቀ መንበር መምረጡ ቢታወቅም አዲስ ማለዳ ለኅትመት እስከገባችበት ድረስ የተመረጡት ሊቀመንበር ማን እንደሆኑ አላቀወችም።

ኢዜማ የተመሠረተው የቀድሞ አንድነት ለዴሞክራሲና ፍትሕ አመራሮች፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ሰማያዊ ፓርቲ፣ አርበኞች ግንቦት 7 መላው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ እና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ከስመው ውሕደት መሆኑ ይታወቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here