አሜሪካዊው የደሃ ደንብ መብት ጥያቄ ማንሳታቸውን የመንግሥት የልማት ድርጅት ተቃወመ

0
677

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ የፍትሓ ብሔር ችሎት በብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የባለቤትነት ክርክር አመልካች ብርሃኔ ገብረመድህን በዜግነት አሜሪካዊ በትውልድ ኤርትራዊ በመሆናቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በነፃ ሊያስተናግዳቸው እንደማይገባ የመንግሥት ልማት ድርጅት ኤጀንሲ ገልፆ ተከራከረ።

ኤጀንሲው በቀደሞ ቀጠሮ ለችሎቱ ሀብታቸው ተጣርቶ እስከሚታወቅ በደሃ ደንብ መስተናገድ የለባቸውም ብሎ የተከራከረ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30/2011 በነበረው ቀጠሮ ግን ሀብት ቢኖራቸውም ባይኖራቸውም የደሀ ደንብ መብት ሊጠበቅላቸው አይገባም ብሎ ተከራክሯል።

ፍርድ ቤቱም በችሎት የሀሳብ ለውጥ በማድረግ ክርክር እያደረጉ እንደሆነ ለድርጅቱ ነገረ ፈጅ ቢያስታውስም ተጠሪ ግን ቀድሞውንም የተከራከሩት አመልካች የውጪ ዜጋ በመሆናቸው ብቻ ጉዳያቸው በደሃ ደንብ ሊታይላቸው አይገባም በማለት አንደነበረ አስረድቷል።

በትውልድ ኤርትራዊ ዜግነታቸው ደግሞ አሜሪካዊ የሆኑት ብርሃኔ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት ከሆነ በውጪ አገር የሚገኝ ምንም ዓይነት ንብረት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አስረድተዋል።

“በዚህ ጉዳይ ላይ ምስክሮችን ማሰማቴ ይታወሳል፤ ነገር ግን የመንግሥት ልማት ድርጅት ንብረት አላቸው በሚል ማስረጃ የሌለው ሐሳብ በማምጣት እያስተጓጎሉኝ ስለሆነ ፍርድ ቤቱ ይህን ታሳቢ በማድረግ ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ ይሰጥልኝ” በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ አሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጰያ ኢምባሲ ጉዳዩን አጣርቶ እንዲያቀርብለት በተደጋጋሚ ትዕዛዝ አስተላልፎ ምላሽ ካለማግኘቱም ባለፈ ኢምባሲው ለተጠየቀው ማስረጃ ምላሽ ያልሰጠበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ አስተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።

መንግሥት ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ካዘዋወራቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ሽያጭ ዙርያ ከሳሽ ብርሃኔ በፋብሪካው ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳታቸውን ተከትሎ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሽያጭ ሒደቱ እንዳይቀጥል የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።

ለረጅም ዓመታት ሳይሳካ የቆየውን ፋብሪካውን የመሽጥ ሙከራ በመጨረሻ ሎሚናት መጠጥ ፋብሪካ በ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በጨረታ በማቅረቡ ፋብሪካውን እንዲጠቀልለው ተወስኖለት የነበረ ቢሆንም የረጅም ጊዜ የባለቤትነት ጥያቄ ባቀረቡት አመልካች ጥያቄ በመታገዱ ዝውውሩ መጠናቀቅ አልቻለም።

በቀድሞ ሥሙ ኤልያስ ፓፓሲኖስ መጠጥ ፋብሪካ የአሁኑ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ከዛሬ 106 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ሲሆን እስከ 1969 ድረስ በብርሃኔ ሥር ይተዳደር የነበረ ፋብሪካ ነበር። ይሁንና በቀድሞ የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ዋና ጸሐፊ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ትዕዛዝ 1969 በመንግሥት እንዲወረስ ተደርጎ ነበር።

በአዋጅ የተወረሱ ንብረቶች ወደ ባለቤቶቻቸው እንዲመለሱ በ1983 በፀደቀው መሰረት በኃላ ብርሃኔም ድርጅታቸው እንዲመለስላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር። በ1990 በቀድሞው የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ቦርድ ሊቀ መንበር በነበሩት አሰፋ አብርሀ እና ሌሎች የቦርዱ አባላት ትዕዛዝ የአልኮል ፋብሪካው በወቅቱ የወጣበትን ወጪ 26 ሚሊዮን ብር ከፍለው አልያም አቅሙ ከሌላቸው ካሳ እንዲከፈላቸው አዞ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጂ በ1991 በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግሥታት የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ የቀድሞ ባለቤት ብርሃኔ ከአገር እንዲወጡ በመደረጋቸው ኹለቱንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። ይሁንና በ2001 ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከተፈቀደላቸው በኋላ ድርጅቴ ይመለስልኝ የሚል ጥያቄ አቅርበው፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ካሳ እንዲከፍላቸው ቢወሰንም ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 27 ግንቦት 3 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here