ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት ያስፈልጋታል?

0
1098

የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ በሴራ፣ በመግደል እና መገዳደል ላይ የተመሠረተ ነበር የሚሉት ሙሐመድ ሐሰን (ዶ/ር)፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ግን “መግደል መሸነፍ ነው” በሚል መፈክር ይህንን ሒደት የሰበረ ነው በማለት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያራምድ መንግሥት ነው ይላሉ።

“ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት ያስፈልጋታል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት ነበራት የሚለውን በአጭሩ መዳሰስ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከሳባ – ሰለሞን – ቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ዛሬው ኢሕአዴግ ድረስ የተለያዩ መንግሥታት መጥተው አልፈዋል። እነዚህ መንግሥታት ለአገራቸው ያደረጉት አስተዋፅዖ በዝርዝር ለመቃኘት መጽሐፍ ሊወጣው የሚችል ጉዳይ ስለሆነ የቅርቡን የኢትዮጵያ መንግሥታት ታሪክ ላይ በማተኮር እንወሰናለን።

የፖለቲካ ታሪክ ሒደቱ
የቅርቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ሲባል ደግሞ ከዳግማዊ ቴዎድሮስ እስካሁን ያለውን ማለት እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ እንዲሆን ያስፈልጋል። ታዲያ እነዚህ መንግሥታት ጥለውት የሔዱትን አሻራ ስንመረምር ዛሬ ለምንገኝበት የመንግሥትና የአስተዳደር ሁኔታ ተፅዕኖ በማድረግ ለበጎም ሆነ ለክፉ ያበረከቱት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ መመርመር ያስፈልጋል። ዐፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያው የብሔራዊ መንግሥት ምሥረታ ጠንሳሽ እንደነበሩ ይታወቃል። ከዚያ በፊት የነበሩ መንግሥታት አገራዊ መንግሥትን ሲያስቀጥሉ ኖሩ እንጂ ወደ ብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ገና አልተሸጋገሩም ነበር።

የዐፄ ቴዎድሮስ አጀማመር ምን ያህል ችግር እንደነበረበትና ፍፃሜውም ከራሳቸው ሕይወት ማለፍ ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ግልጽ ነው። የዐፄ ዮሐንስ (አራተኛ) ዘመነ መንግሥትም የተጀመረውን ዓላማ በመቀጠል ውጣ ውረዶችን ካለፈ በኋላ ወደ ግብ ሳይጠጋ እንደዚሁ ከራሳቸው ሕይወት ጋር አብሮ ተጠናቋል። የኢትዮጵያን ብሔራዊ አገረ መንግሥት ግንባታ ለየት ያለ መልክ ያስያዙት ዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ ነበሩ። የአድዋን ድል መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያ በዓለም ውስጥ ነጻነቷን አስከብራ ራሷን የቻለች ብሔራዊ መንግሥት መሆኗን ያስመሰከሩ ብቸኛ መሪ ነበሩ። ከዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ በኋላ ይህንን የተጀመረውን የብሔራዊ አገር መንግሥት ግንባታ አስቀጥለው ለከፍተኛ ደረጃ ያበቁታል ተብሎ የተጠበቀው በልጅ እያሱ ዘመን ነበር። ይሁንና ልጅ እያሱ ለዚህ ለብሔራዊ መንግሥት ግንባታ የሚያስፈልጉ ጠቃሚ ቁምነገሮችን ለማሳካት ጅምር ላይ እንደሉ በአጭር ተቀጩ። የልጅ እያሱን በአጭር መቀጨት ኢትዮጵያን ከአዙሪት ፖለቲካ አውጥቶ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነባት አገር እንድትሆን ያደረጉት ሙከራ በአጭር ስለተቀጨ ዛሬም ከዚሁ አዙሪት መውጣት አቅቶን በመንገዳገድ ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ ስትጠቀምበት ያመለጣት የመጀመሪያው ዕድል ይህ እንደነበር ታሪክ ያስታውሰዋል።

መፍታት ያቃቱን ችግሮች
ዐፄ ኃይለሥላሴ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ መንግሥት ግንባታ ያደረጉት አስተዋፅዎ እንዳለ ሆኖ ከገዙበት ረጅም ዕድሜ ጋር ሲወዳደር በጣም ያነሰና ዛሬ ለምንገኝበት የፖለቲካና የብሔር ችግር ራሱን የቻለ አስተዋፅዎም አበርክቷል። አገሪቱ ከነበረችበት የመጋደልና የሴራ ፖለቲካ አውጥተው ሕዝቡን ለፍትሕና እኩልነት ማብቃት አልቻሉም። በመሆኑም የብሔራዊ መንግሥት ግንባታውን ወደኋላ ጎተተው እንጂ በሚጠበቅ መልኩ ወደፊት ሊያራምደው አልቻለም። ስለሆነም የዚህ ሁሉ ችግር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቋዳሽ ከመሆን አልቀረለትም። ይህን ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ወስዶ በመጠኑም ቢሆን ለማሻሻል የሞከረው ደግሞ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ነበር። ደርግ መጠናዊ ማሻሻል ቢያደርግም ከዚያው ከመግደል መጋደል አዙሪት ፖለቲካው መውጣት ስላቃተው የራሱን መውደቅ አመቻቻቶ አልፏል። ደርግን የተካው ኢሕአዴግ ደግሞ ሕወሓት ደደቢት ላይ የነደፈውን አጀንዳ ሲያራምድ ቆይቶ እንኳን ለብሔራዊ መንግሥት ግንባታ አስተዋፅዎ ማበርከት ይቅርና መገንጠልን ለመቀበል መሪ ተዋንያን ሆኖ አረፈው። በኋላም ምርጫ ዘጠና ሰባት የከፈተለትን በር ጭራሽ ቅርቅር አድርጎ በመዝጋት እዚያው መግደል መገዳደል ውስጥ ተዘፍቆ አረፈው። እንኳን ኢትዮጵያን የመሠለ አገር መምራት ይቅርና አቅሙም ችሎታውም ክፉኛ ስለአጋለጠው መጨረሻው መቀሌ ሔዶ መመሸግ ሆነበት።

የዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ
የሕወሓትን መውደቅ ተከትሎ የመጣው ሌላው ኢሕአዴግ ደግሞ መንበረ ሥልጣኑን ተቆናጠጠና ኢትዮጵያን መምራት ጀመረ። በዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው ኢሕአዴግ እስካሁን የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀያይሮ አዲስ አስተሳሰብና አመለካከትን በኢትዮጵያ ጮራውን እየፈነጠቀ ይገኛል። ይህ አዲስ አስተሳሰብ ከበፊቱ የሚለየው በምንድን ነው? የበፊቶቹ መንግሥታት ከዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ እና ልጅ እያሱ በስተቀር ሥልጣን የመጡት አንድም በኃይል ወይንም መግደልና መገዳደልን መሠረት ባደረገ የሴራ ፖለቲካ ነበር። ስለሆነም ፍትሕና እኩልነትን መሠረት ያደረገ ስርዓት መገንባት አልቻሉም። የብሔራዊ መንግሥት ግንባታውም ሒደት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ሊደርስ ያልቻለው በዚህ ምክንያት ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሥልጣን ሒደቱ በመግደል መገዳደል ወይንም በሴራ ሳይሆን በሰላም እንዲሸጋገር የተሞከረው ዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክ ልጅ እያሱን አልጋወራሽ ሲያደርጉ ነበር።

ከዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክና ከልጅ እያሱ በጎ ጅምር በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመሳሳይ ሐሳብ አንግበው የተነሱት መሪ ከራሱ ከኢሕአዴግ አብራክ የወጡት ዐቢይ ሆነው ብቅ አሉ። መግደል መሸነፍ መሆኑን በአደባባይ ለሕዝብ ያበሰሩት የመጀመሪው የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው። አገራችን በታሪክ ያጋጠማትን አንዳንድ ጥሩ አጋጣሚዎች ሳትጠቀምበት በመቅረቷ ምን ያህል እንደጎዳንና ወደ ኋላ እንዳስቀረን እና አሁንም ይህ በእጃችን የገባውን ጥሩ ዕድል ሳንጠቀምበት በከንቱ እንዳያልፈን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአደባባይ ነግረውናል። እርሳቸው ኢትዮጵያን ፍትሕና እኩልነት የሰፈነባት እንዲሁም በዴሞክራሲ ጎዳና መርቶ አገሪቱ ያጣችውን ክብሯን እንደገና ለማጎናፀፍ የሚጥሩ መሪ መሆናቸውንም በማያሻሙ ቃላቶች ነግረውናል። ይህን ሁሉ ከተረዳን ታዲያ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግሥት ነው የሚያስፈልጋት የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ መመለስ ግድ ይለናል። ለመሆኑ እኛ ኢትዮጵያውያኖች ምን ዓይነት መንግሥት እንደሚያስፈልገን በግልጽ እናውቃለን?
ማን ነው የተሻለ አማራጭ ያለው?

አዲሱ የዐቢይ መንግሥት ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ዕድገት እንድትራመድ ለማድረግ ቆርጦ የተነሳ መሆኑን አገሩን የሚወድ ሁሉ የሚጠራጠር አይመስለኝም። ጥያቄው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዓላማቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉት ማንን ይዘው ነው? በተለይ ደግሞ ሊጋረጥባቸው የሚችለውን እንቅፋት ለማስወገድ አቅማቸው ምን ያህል ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በቂ መልስ ማግኘት አለባቸው። ከላይ እንደተጠቀሰው ዐቢይ የወጡት ከኢሕአዴግ አብራክ ነው ተብሏል። ማንም እንደሚያውቀው ኢሕአዴግ የሚባለው ደግሞ ተጠፍጥፎ የተሰራው በሕወሓት ነው። ዐቢይ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲመረጡ ሕወሓቶች አኩርፈው ጓዛቸውን ጠቅልለው መቀሌ ሄደው መሸገዋል። ሌሎች ሦስቱ የኢሕአዴግ አባል ድረጅቶች ቢያንስ የበላይ አመራሩ የለውጡ አካል መሆኑን ሲያበስር ሕወሓት በይፋ የለውጡ ደጋፊም ተቃዋሚም ነኝ ሳይል የያዘውን ይዞ መቀሌ ላይ ሔዶ መመሸግን መረጠ። ለመሆኑ ሕወሓት ምንድን ነው ይዞ የሔደው?

የሕዝብ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ለአንድ መንግሥት ዋልታና ማገር ነው። ሕወሓት ያዋቀረው የሕዝብ ደኅንነት ከዋና መሪውና ተከታዮቹ ጋር ሆኖ ያለውን ጠቅላላ መረጃ ይዞ አብሮ መቀሌ መሸገ። ቀሪው የሕዝብ ደኅንነት አባሎች ባሉበት አድፍጠው እንዲጠብቁ ተደረገ። ስለሆነም አዲሱ መንግሥት የሕዝብ ደኅንነት የሌለው ወና ቤት ብቻ ወረሰ ማለት ነው። ይህ የተባለው የሕዝብ ደኅንነት ኻያ ሰባት ዓመት ሙሉ ሰው በማሰር፣ በመግደልና በማሰቃየት የታወቀ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ደኅና አድርጎ ሲቀለብና የተንደላቀቀ ኑሮ ሲመራ የኖረ ነበር። ይህ መቸም በምንም ተአምር የለውጡ አካል ሊሆን አይችልም። በተፈፀመው ወንጀል ደግሞ አንድ ቀን መጠየቃቸው አይቀርም።

በምን ዓይነት የዘር ስብጥር የተዋቀረው የመከላከያ ሠራዊት ደግሞ ሌላው የሕወሓት ቀኝ እጅና መከታ እንደሆነ ይታወቃል። ለውጡን የሚደግፍ ሌላ የመከላከያ ሠራዊት ማቋቋም ደግሞ ጊዜ ከመውሰዱም ባሻገር እንደዚህ ለአፍ የሚቀል ጉዳይ አይደለም። በዚያ ላይ በዘርፈ ብዙ የሙስና ሰንሰለት የተዋቀረው የመከላከያ ሠራዊት የአገሪቱ ሀብት በእጁ ነበር። የት ደረሰ? ስለዚህ አዲሱ መንግሥት ሊንቀሳቀስ የሚያስችለው ገንዘብም የለውም ነበር ማለት ነው። በሕወሓት አስተሳሰብ ይሔ አዲሱ መንግሥት በእግሩ ሊቆም ስለማይችል በቅርብ ጊዜ እንደሚወድቅ ይተማመኑ ስለነበር በዲፕሎማቶች አካባቢና በየኮክቴሉ ሲናፈስ የነበረ የአንድ ሰሞን ወሬ ነበር።

ሕወሓት የራሱን ጥቅም እንዲያስጠብቁለት የፈጠራቸው ሦስቱ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ቅድሚያ ሰጥተው ሲሠሩ የነበሩት የሕወሓትን የሥልጣን የበላይነት ለማስፈፀም እንጂ የወከሉትን ሕዝብ ጥቅም ሲያስጠብቁ እንዳልነበር ለማንም ግልጽ ነው። ይህም እውነት እወክልሃለሁ የሚሉት ሕዝብ ተለጣፊ የሚል ሥም ከማውጣት ባሻገር በአገኘው ሁሉ አጋጣሚ ተቃዋሚነቱን ሲገልጽ እንደነበር ይታወቃል። እንደዚህ ዓይነቱን ድርጅቶች ነው እንግዲህ አዲሱ አመራር የለውጡ አካል ናቸው ተብለው የተነሳበትን በጎ ዓላማ ተግባራዊ ለማድረግ የተነሳው። በሌላ ወገን ደግሞ የእነዚህ ሦስት ድርጅቶች ካድሬዎች ለውጡ አስካሁን የለመዱትን ቅምጥል ኑሮ የተጀመረው ለውጥ ሊያቆምባቸው እንደሚችል ስለሚገምቱ ለውጡን በበጎ ያዩታል ብሎ መገመት የዋህነት ነው። ዐቢይ ከዚህ ድርጅት ውስጥ የመጡ ስለሆኑ ይህ ሁሉ ችግር ለእርሳቸው ግልጽ እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ሁሉ ተደምሮ ነው እንግዲህ የለውጡ ተቃዋሚ ኃይሎች አዲሱ መንግሥት በእግሩ ሊቆም ስለማይችል እኛም በየጊዜው አንዳንድ መሰናክል እየወረወርን ፋታ አሳጥተን በአጭር ጊዜ መውደቅ አለበት ብለው ባለሙሉ ተስፋ እንደሚሆኑ ይገመታል። አዲስ የተመረጡት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ማንን ይዘው ወይም በምን ተማምነው ነው ይህንን የመሰለ ኻያ ሰባት ዓመት ችግር ያልፈታ ድርጅት ይዘው ለውጥ አመጣለሁ ብለው የተነሱት?

የለውጡ ዋና ዋና ዓላማዎች
ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ፓርላማ ቀርበው ያደረጉት የመጀመሪ ንግግራቸው በጣም ግልጽ፣ ማንም በቀላሉ ሊገባው በሚችል አነጋገርና እና ትህትና በተሞላው አንደበት የተነሱበት ዓላማ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲደግፈውና ከጎኑ ሲቆም መሆኑን አሠመሩበት። ስለሆነም ዐቢይ ሙሉ በሙሉ እምነታቸውን የጣሉት በኢሕአዴግ ሳይሆን በፈጣሪና በኢትዮጵያ ሕዝብ መሆኑን አስረግጠው ተናገሩ። ያለፈው 27 ዓመት የኢሕአዴግ ዘመን ያለፈና የተቀበረ መሆኑን ለማረጋገጥ በፖለቲካ፣ በጋዜጠኝነት፣ ከሃይማኖት ጋር በተሳሰረ ጉዳይና ሙሉ የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ አደረጉ። በሃይማኖት፣ በዘርና በፖለቲካ ሆነ ተብሎ እንዲለያይ እንዲጠላላ ሲደረግ የነበረው የ27 ዓመት ጥረት አክሽፈው አገር ውስጥና ውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ እንዲታረቅና ለጋራ አገር ግንባታ እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲጓዝ ድልድዩን መሠረቱለት። የመለያየትና የመጠላላት መንፈስ ተቀብሮ አብሮ በመደመር በጋራ አገራችንን እንገንባ ብለው ጥሪ አቀረቡ። ጊዜ ከረሳውና አውቆ እንዲድበሰበስ ከተደረገው የዳግማዊ ዐፄ ምኒሊክና የልጅ እያሱ ለአገር በጎ አሳቢነት ወዲህ ዐቢይ የመጀመሪያው ለኢትዮጵያ በጎ አሳቢ መሪ መሆናቸውን ታሪክ መዝግቦላቸዋል ብዬ አምናለሁ። ይህንን እውነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ በትክክል ይረዳዋል?

ሁላችንም እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመጋቢት ወር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆንና በፓርላማ ያደረጉትን አስደማሚ ንግግር በመደገፍ በሰኔ ወር መስቀል አደባባይ በነቂስ ወጥቶ ድጋፉን አሳየ። ይህ በሕዝብ መንፈስ የተሰረፀው ሁለገብ ድጋፍ ያስደነገጠው ኃይል የመግደል ሙከራ ማካሔዱ ሊገርም አይገባም። መላው የኢሕአዴግ አመራር እኮ አሁንም ከፍተኛ ሥልጣን ላይ አለ። ታዲያ የመግደል ሙከራው ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም የሚል እንደምታ ያለው ይመስላል። ያኮረፈውና አውቆ የመሸገው ኃይል እንዲህ በቀላሉ ተሸናፊነቱን ተቀብሎ አደብ ይገዛል ብሎ መገመት የዋህነትና የኢትዮጵያ ፖለቲካና ታሪካዊ ሒደት ያልገባው ብቻ ነው። ስለሆነም ያደፈጠው ኃይል ፈራተባ እያለ በአገኘው አጋጣሚ እንቅፋት ከመሆን አይመለስም። የዐቢይ አሕመድ የሕዝብ ድጋፍ የሌለውና በእግሩ ሊቆም የማይችል መሆኑን ከፕሮፓጋንዳ ባሻገር በተግባር ተሠማርቶ አገሪቱ ያልተረጋጋች እንድትመስል በሰፊው ተሰማራ። የሕግ የበላይነት ሊያስከብር የማይችል መንግሥት መሆኑን ደጋፊም እስከሚጠራጠር ድረስ ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ያስረዳል።

መረጋጋት እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት?
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ የሚያስረዳው እስካሁን የነበሩት መንግሥታት በሙሉ በአጭር ጊዜ ተረጋግተው አያውቁም። ሌላውን ሁሉ ትተን ደርግ እንኳ መረጋጋት የጀመረው ኹለቱ የመጀመሪያ መሪዎች ጄኔራል አማን አንዶምና ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ከተገደሉ በኋላ፣ ነጭና ቀይ ሽብር እንዲሁም የሱማሌ ወረራ አክትሞ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የአምባገነን መንበረ ሥልጣናቸውን ካረጋገጡ በኋላ ነው። ይህ ደግሞ ቢያንስ ከኹለት እስከ ሦስት ዓመት ፈጅቷል። ኢሕኣዴግ በቀላሉ የተረጋጋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነት ሰልችቶት ስለነበር፣ ጎረቤት ሱማልያ የደረሰው የእርስ በእርስ ግጭት ኢትዮጵያ እንዳይደርሰ አሜሪካኖቹ ከፍተኛ ግፊት በማድረጋቸውና የቀድሞው የደኅንነቱ ኀላፊ አቶ ክንፈ ገ/መድኅን፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴን ከእስር ቤት ወደ ቢሮው እያስመጣ የደርጉ ሕዝብ ደኅንነት ችግር እንዳይፈጥርና የራሳቸውን ሕዝብ ደኅንነት በማዋቀር ስለረዷቸው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። እስካሁን ከነበሩት ሁሉ የዐቢይን መንግሥት ልዩ የሚያደርገው ባዶ ቤት ወርሶ ዋና መተማመኛውን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ማድረጉ ነው። ሕዝብን የተማማነ መንግሥት ደግሞ ለጊዜው ይንገራገጭ ይሆናል እንጂ እንዲህ በቀላሉ አይወድቅም። የዐቢይ መንግሥት እንዲወድቅላቸው የሚፈልጉ ኃይሎች ያልገባቸው ነገር ቢኖር እነርሱም በሕዝብ ቢተማመኑ ኖሮ ከመውደቅ ይድኑ እንደነበር ነው። የዐቢይ መንግሥት የሚወድቀው ሕዝብ በማያምናቸው ተንኮለኞች ሴራ ሳይሆን የኢትዮጵያን ሕዝብ ድጋፍ ሲያጣ ብቻ ነው። መሪው ለሕዝብ ያደረግውን ንግግር ማጠፍ ሲጀምርና ማስመሰል ሲሞክር ሕዝብ የሰጠውን አመኔታ ያነሳል። ይህ ደግሞ የውድቀት መጀመሪያ ይሆናል ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ሕዝብ በትንሹ፣ በሆነ ባለሆነው፣ በአሉባልታ መፍራትና መደናገጥ የለበትም። የሚነዛው ውዥንብር ቀላል አይደለም። እንኳን ብዙ ዓይነት ችግር ያለበትን ሕዝብ ይቅርና ተምሬአለሁ አውቃለሁ የሚለውም በቀላሉ ሲዋዥቅና ሲንሸራተት ይታያል። በእርግጥ ወቅቱ አስቸጋሪ ነው። ለሁሉም ትግስትና ጥንቃቄ ማድረጉ አይከፋም። የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ሲባል ይሰማል አይደል!

ማጠቃለያ
ወደተነሳንበት ጥያቄ ለመመለስ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት መንግስት ያሰፈልጋታል ለሚለው እስካሁን የነበሩትን መርምረን እስከዛሬው የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ደርሰናል። የት ነበርን ወዴት ነው የምንሄደው የሚለውንም ጥያቄ ለመመለስ አቅሙም፣ ችሎታውም እንዲሁም በቂ ግንዛቤ አግኝተናል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ (በጥንስሱ የተቀጨው ምርጫ ዘጠና ሰባት እንዳለ ሆኖ) ዛሬ ይህን ዓይነት መንግስት እፈልጋለሁ ብሎ ቢነሳ ሕዝቡ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይደርስበት ያውቃል። ዶ/ር አብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያጎናፀፉት ነፃነት ከዚህ በፊት ኖሮት አያውቅም።ይኸ የዛሬው የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት ቢወድቅ ምን ዓይነት መንግስት ሊመጣ እንደሚችል ሁላችንም በቅጡ ተረድተናል የሚል ግምት የለኝም። ይኸ ዛሬ ያገኘነው በእጃችን ያለው ነፃነት አስከብረን፣ተንከባክበን፣ ተቋማዊ ሆኖ መሰረት እንዲጥል መርዳት አቅቶን ችግር ውስጥ ቢገባ በዶ/ር አብይ አህመድ ወይም በቲም ለማ ማሳበብ ተገቢ አይሆንም። ሕዝብ ደግፎና ተንከባክቦ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻግር የተነሳውን መሪና ወደኋላ ጎትቶ በማስቀረት ገደል ሊከተው በተነሳው አስመሳይ መካከል ያለውን ልዩነት በግልፅ መረዳት ይኖርበታል። ከተረዳ ደግሞ አቋሙን ማስተካከል አለበት። ሐገሪቱን ለጭቆናና ለስቃይ ዳርጎ ሲቀማጠል የኖረው ኃይል ጥቅሙ ሲቋረጥበት ወደ አሸብሪነት ሲሰማራ ሕዝቡ ተው ይብቃህ በማለት ወደ እርቅና ወደ ሰላም እንዲመጣ ተገቢውን ተፅእኖ እንዲያደርግ ይጠበቅበታል። ሐገሪቱ እኮ የሁላችንም ነች። አንዱ እየገነባ ሌለው እያፈረሰ ሐገር አታድግም። መሪው እንታረቅ እንደመር ሲል አኩራፊው አሻፈረኝ በጭራሽ ሲል ሕዝብም አቋሙን ለይቶ አዎ ትክክለኛው መንገድ ይህ ነው በማለት ድጋፉን ማሳየት አለበት። በሽብር የተሰማራው ኃይልም የሕዝብን ድጋፍ ሲመለከት ከጥፋት ሥራው እንዲርቅና ወደ ሰላምና መረጋገት እንዲመጣ ይገደዳል። ጥፋትና ግጭት በማንኛውም መንገድ መፍትሄ ሆነው አያውቅም።

ሙሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የኦርየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም መምህር ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው selammhd@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here