“ኢዜማ የመከፋፈል ዕድል ይገጥመዋል ብለን አናስብም”

0
979

ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) መሪ ናቸው።
ብርሃኑ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በንቃት በማሳተፍ በሰፊው ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ ቀስተ ዳመና እና ቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ (ቅንጅት) ፓርቲዎች ውስጥ እስከ አመራርነት የደረሰ ተሳትፎ ነበራቸው። የ1997ቱን አገር ዐቀፍ ምርጫ ውጤት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉት ብርሃኑ፣ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት “የነፃነት ጎሕ ሲቀድ” የተባለ ዳጎስ ያለ መጽሐፋቸው በድብቅ ታትሞ ተሰራጭቷል። በመጽሐፋቸው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር የሰላማዊ ትግል አማራጭ የለሽነትን በሰፊው አትተዋል፤ የፖለቲካ ተሳፏቸውንም አስነብበዋል።

ይሁንና ከእስር እንደተፈቱ በኢትዮጵያ ሰላማዊ ትግል ብቻ ሳይሆን ሁለገብ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ግንቦት 7 የነፃነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄን (በኋላ አርበኞች ግንቦት 7) በመመስረት ትጥቅ ትግል አካሒደዋል፤ ድርጅቱንም በሊቀ መንበርነት መርተዋል።

የ2007 አገር ዐቀፍ ምርጫ በተካሔደ ማግስት ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ሕዝባዊ ተቃውሞ የበረታበት ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ‘ጥልቅ ተሐድሶ’ በማድረግ የአዳዲስ አመራሮች ወደ ሥልጣንን መምጣት ተከትሎ በተፈጠረው የፖለቲካ ምኅደር መስፋት በ2010 የመጨረሻ ሳምንት÷ በብርሃኑ የሚመራው ታጣቂ ቡድን ትጥቁን በይፋ በመፍታት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል።

ላለፉት 7 ወራት ዜግነትን መሰረት ያደረገ ፓርቲ ለመመሥርት በከፍተኛ የሥራ ጫና ውስጥ እንደነበሩ የሚናገሩት ብርሃኑ÷ ግንቦት 1 እና 2 በአዲስ አበባ ስብሰባ ማዕከል ከመላው ኢትዮጵያ 312 ወረዳዎችን የወከሉ 1467 ሰዎች በተሳተፉበት የመመስረቻ ጉባኤ በ912 ድምጽ የፓርቲው መሪ ሆነው ተመርጠዋል።

ብርሃኑ በሙያቸው ታዋቂ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሲሆኑ፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ኒው ዮርክ ከሚገኘው ‘New School for Social Research’ ከተባለ ተቋም አግኝተዋል፤ እዛው ሰሜን አሜሪካ በሚገኘው በክኔል ዩኒቨርሲቲ ለዓመታት አስተምረዋል። የኹለት ልጆች አባት የሆኑት ብርሃኑ÷ ከአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ጋር ስለአዲሱ ኢዜማ ፓርቲ እና ወቅታዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታን በተመለከተ ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ማለዳ፡ ባልተለመደ መልኩ ኢዜማ ኹለት ዓይነት የፓርቲ አወቃቀር በማድረግ በመሪና በሊቀመንበር ይመራል። ለፓርቲው የእነዚህ ኹለት መዋቅሮች መኖር ፋይዳው ምንድን ነው?
ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፡ በዋናነት ለመለየት የፈለግነው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ አሰራር የተለመደው ግራ ዘመም፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጋር የሚያያዘው አንድ መሪ የፓርቲውን ሁሉን ነገር ጠቅልሎ የመያዝ ነገር ለማስቀረት ነው። በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ልዩነት የለም። ይሔ በአብዛኛው አምባገነን ስርዓቶች የሚጠቀሙበት፣ ብዙ ተሞክሮ ብዙ ማኅበረሰብን ችግር ውስጥ የከተተ እንደሆነ እናውቃለን። ከምንም በላይ መንግሥትና ፓርቲ መካከል ትልቅ ልዩነት ሊደረግ ይገባል። ፓርቲ በአንድ አመለካከት የተሰባሰቡ ዜጎች አንድ ዓይነት ፖሊሲና ዓላማ ይዘው ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱበት ነው።

ፓርቲ መንግሥት ሲሆን የሚያስተዳድረው የፓርቲውን ሰዎች ብቻ አይደለም። ከድርጅት ውጪ ያሉ ፓርቲውን የማይደግፉ፣ ሌላ አመለካከት ያላቸውን ዜጎች ጭምር ነው። እንደዜጋ በእኩልነት ሊተዳደሩ ይገባል።

የፓርላማ ተወዳዳሪዎችንና በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚሠሩ ሰዎችን ከፓርቲው የዕለት ተዕለት ሥራ መለየት አለብን። የፓርቲ የዕለት ተዕለት ሥራ ከመንግሥት ጋር በተቻለ መጠን ምንም ንክኪ እንዳይኖረው በማድረግ ነው ፓርቲውን ያደራጀነው። በመንግሥት ዙሪያ የሚሠሩ እንደ ፓርላማ ተመራጭ ወይም ሌላ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዙ በአጠቃላይ የፓርቲውን ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር፣ ማወቅና መረዳት ያለባቸው የምርጫ ወረዳቸውን ጥቅም ማስከበር ነው። የምርጫ ወረዳ ጥቅም ደግሞ ፓርቲውን የማይደግፉትን ጭምር ሊያካትት ይችላል። ይሔ በግልጽ መለየት አለበት፤ መንግሥት በፓርቲው መዋጥ የለበትም የሚል አመለካከት ይዘን ነው የተነሳነው። ፓርቲው በምርጫ ወረዳ ላይ የተመሰረተ ነው ስንል ይህንን ማለታችን ነው።

ፓርቲው ወይም በፓርቲው ውስጥ የአንድ ምርጫ ወረዳ ተወካዮች በዋናነት ያላቸው ኀላፊነት የወረዳቸውን ሕዝብ መወከል ነው። አንዳንድ ጊዜ ከፓርቲው አቋም ጋር የሚለያይ ነገር ቢኖር እንኳን መወከል ያለባቸው ሕዝባቸውን ነው።

የኢዜማ ዋና ዋና የፖሊሲ አማራጮች ምንድን ናቸው?
አንድ ያደረግነው ነገር ጥቅል የሆነ ፕሮግራም ከማዘጋጀት ባሻገር በእያንዳንዱ መሰረታዊ ጉዳይ የፖሊሲ ጥናት ማስጠናት ነው። አርባ ምሁራን የሚሳተፉበት የፖሊሲ አጥኚ ቡድን ነበረን፤ ቡድኑ 12 ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ጥናት እንዲያደርግ አድርገናል።

ማዕቀፉ ማኅበረሰባዊ ፍትሕ አንድ ኅብረተሰብ በሰላም አብሮ እንዲኖር ካስፈለገ ለተወሰኑና ለተመቻቸው ሰዎች ብቻ ሊሆን አይችልም። ሁል ጊዜ ይሔ ችግር ሲፈጠር ታይቷል። ስለዚህ ነፃ ገበያ እየተባለ የሚወጣው ነገር÷ ነፃ ገበያን የሚከተሉ አገሮችን ጭምር ችግር ውስጥ እየከተተ ነው።

በሀብታምና በደሃ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ ሲሔድ ሰዎች መሰረታዊ የሆነ ለኑሮ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ምግብ፣ መጠለያ፣ ጤና ማግኘት የማይችሉ ከሆኑ ዘላቂ የተረጋጋ ማኅበረሰብ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ እኛ የምንለው ገበያው ሀብት ሲያቀርብ በመንግሥት ከፍተኛ ተጽዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ማድረግ ነው። ገበያ ሰዎች የሚፈጥሩት ተቋም ነው። ዝም ብለህ ከለቀቅከው ማኅበረሰብን ሊጎዳ ይችላል። ስለዚህ በተወሰነ ደረጃ ሚዛናዊ የሆነ ገበያ እንዲሆን በማድረግ መንግሥት ኅብረተሰብን የተሸለ ሕይወት እንዲኖር ማድረግ ኀላፊነት አለበት።

በታክስ ፖሊሲ አማካኝነት በደሃና ሀብታም መካከል ያለውን ክፍተት የሚሸፈንበት መንገድ መኖር አለበት። ይሔ ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በፖሊሲ ደረጃ የምታደርገው፣ “አሁን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? ወደፊት ሊመጣ የሚችለው ምንድን ነው? የተጠራቀሙት ችግሮች ምንድን ናቸው?” ብለህ ማስጠናት ይጠይቃል። ጥናቶቹ በእነዚህ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፤ አሁን አልቀዋል። የቀረን ነገር ቢኖር ሰፊ ውይይት ከአጥኚዎቹ ጋር በማድረግ ወደ ማጽደቅ እንሔዳለን።

ከማኅበራዊ ፍትሕ አንጻር የፆታ ዕኩልነት ማስከበር ጉዳይ አንዱ ነው። በኢዜማ ውስጥ የሴቶች ተሳትፎና የአመራሮች ውክልና ምን ይመስላል?
እያንዳንዱ ወረዳ ወደ ጉባኤ የሚሔዱ ሦስት ሰዎች ወክሏል። ነገር ግን ሴት ተወካይ ከመረጡ አራት፣ የአካል ጉዳተኛ ካካተቱ አምስት ሰው መላክ እንዲችሉ ተደርጓል። ስለዚህ እያንዳንዱ ወረዳ ከሦስት እስከ አምስት ተወካዮች ልኳል ማለት ነው። ይህንን ያደረግነው ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን እንዲሳተፉ ለማበረታታት ነው። ይህ ማለት ግን እንደዚህ በቀላሉ ታገኘዋለህ ማለት አይደለም።

በፕሮግራማችን ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥነው የሴቶች ተሳትፎ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል የለበትም፤ ማብቃት አለብን የሚል ነው። ብቃት ያላቸው ሴቶች ከታች ጀምሮ ራሳቸውን ችለው በደንብ በፓርቲ ወይም በመንግሥት አመራር ላይ እንዲመጡ መሥራት አለብን። ይሄን ያክል በመቶ ግን መባል የለበትም። ሥራ ይጠይቃል በደንብ መሥራት አለብን።

በወረዳ ምርጫ ላይ ሴቶች ተሳትፈዋል፤ ጉባኤው ላይም እንዲሁ። ይህንን የምንሠራው ግን አንድ ቡድን ለማስደሰት ወይም የበለጠ ድምጽ አገኛለሁ በሚል አይደለም። ምክንያቱም ግማሽ የሚያክልን የኅብረተሰብ ክፍል ካልወከልክ ትልቁን የሰው ኀይልህን ታጣለህ። ስለዚህ ከታች ጀምሮ የሚሠሩ ብቃት ያላቸው ሴቶችን ወደ ላይ ለማምጣት መላ መፈለግ አለብን። ብቃት ያላቸው ሴቶችን ማምጣት አለብን። ስለሆነም ከታች ጀምሮ ሥልጠናዎች መስጠት እንጀምራልን። የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከቱ ተከታታይነት ያለው ሥልጠና የሚሰጥ የሆነ አካል ይቋቋማል። በዛ መልክ የበለጠ ማብቃት እንችላለን ብለን እናስባለን።

የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ተልዕኮ በምርጫ ተወዳድሮ የመንግሥት ሥልጣን በመያዝ ፕሮግራሙን ተፈፃሚ ማድረግ ነው።

በኢዜማ ምሥረታ ቀን ንግግሮት “ምርጫ ቅድሚያ የምንሰጥው ጉዳይ አይደለም” ማለትዎ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
የፖለቲካ ፓርቲ ዋና ተልዕኮ ምርጫ ላይ መሳተፍ ነው የተባለው ጥበብ (‘ዊዝደም’) ከየት የመጣ ነው? ፖለቲካ ማለት ሕዝብ ማለት ነው። በመጀመሪያ ሕዝብ ሰላም መሆን አለበት። የፖለቲካ ፓርቲ ተልዕኮ የሕዝብ ጉዳይ ፍላጎት የሚፈጥርብህ ከሆነ ከሰላም በላይ ምንም የለም።

ስለዚህ እንደፖለቲካ በምርጫ ማሸነፍ ብቻ አይደለም። በንግግሬ ውስጥ የተጠቀምኩት በዋናነት አሁን ቅድሚያ የምንሰጠው ሰላም እንዲመጣ፣ ኅብረተሰባችን እንዲረጋጋ፣ ምክንያቱም ያለ እነዚህ ምርጫ ማካሔድ ትርጉም የለውም። አሁን ባለንበት ሁኔታ በየቦታው ምርጫ ይደረግ ቢባልስ ይደረጋል? እንኳን ምርጫ ሊካሔድ እንዲሁም ሰው መኖር አልቻለም።

ምርጫ የፖለቲካ ኃይሎችንና የሕዝቡን ስሜት የበለጠ የሚያነሳሳ ነገር ነው። መረጋጋት ሳትፈጥር ስለምርጫ ማሰብ ወይም ቅድሚያ የምሰጠው ምርጫ ነው ብለህ ሁሉን ነገር ትተህ የምታስብ ከሆነ ፖለቲካ ምን እንደሆነ አልገባህም ማለት ነው።
ፖለቲካ ምርጫ የሚሆነው እኮ በተደላደሉ አገሮች ነው። ምርጫ አሸንፈህ ፕሮግራሜን ተግባራዊ አደርገዋለሁ የምትለው እኮ የተረጋጋ ማኅበረሰብ፣ በፖለቲካ ምክንያት የማይናወጥ ማኅበረሰብ ሲኖር ነው። በየጊዜው የሚናወጥ ማኅበረሰብ ካለ መጀመሪያ ያንን ማረጋጋት ይጠበቃል። አሁን እኛ ቅድሚያ የምንሰጠው ብቻ ሳንሆን መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ይህንን አገር አረጋግቶ ትርጉም ያለው እውነተኛ ምርጫ ማድረግ የሚያስችል ሰላም መፈጠር አለበት። አለበለዚያ ምርጫ ማካሔድ ትርጉም የለውም።

ብሔርተኝነት ጠርዝ ረግጧል በሚባልበት በዚህ ወቅት እናንተ ዜግነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ ይዛችሁ መምጣታችሁ ወደፊት እንዴት ያራምዳችኋል?
መጀመሪያ አገር ማረጋጋት ሥራ ላይ እናተኩር የምንለው ለዚህ ነው። ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ትርጉም የለውም። ነፃ ምርጫ ማለት ለኅብረተሰቡ የተለያዩ አማራጮችን ሰጥቶ፣ ያለምንም ፍርሃት ለእኔ የሚበጀኝ፣ ለቤተሰቤ የሚበጀው ብሎ ሲመርጥ ነው። ይንን ለማድረግ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በነፃነት ሔደው ማስተማር አለባቸው። ይህንን ማካሔድ ካልቻሉ ስለምርጫ ማውራት አይቻልም። በአንድ ወይም በሌላ መልኩ [ኅብረተሰቡ] እንዳይሰማ ተደርጎ “አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያለህ” ተብሎ ከሆነ የሚመረጠው፣ ይሔ በምንም መልኩ ምርጫ አይደለም። ስለዚህ ነው ሰላምና መረጋጋት አስፈላጊነቱ፤ የፖለቲካ ጨዋታው መሰረታዊ ሕግ ምን መሆን ይገባዋል በሚለው ላይ ስምምነት ያስፈልጋል።
ለዚህ ነው ባለፈው ጊዜ የፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ የተፈረመው። እኔ ሰፈር፣ መንደር፣ ክልል አትምጡ የሚባለው ነገር በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ቦታ የለውም። ከየትም ይምጣ ከየት፣ ማንም የፈለገበት ቦታ ቢሮ ከፍቶ ማስተማር፣ አባል መመልመልና ማደራጀት መቻል አለበት። ይሔንን ሲደረግ ነው እውነተኛ ምርጫ የሚካሔደው። ሕዝቡ ብሔርተኛውንም ከብሔርተኛ ውጪ ያለውን ይሰማል፤ ሁሉንም ሰምቶ የሚሻለውን ይመርጣል።

ከዚህ ባሻገር እኛ ለአገር የሚያዋጣው የዜግነት ፖለቲካ ነው ስንል በዚህ ምክንያት ድምጽ እናገኛለን ወይም አናገኝም በሚል ስሌት አይደለም። በመሰረታዊነት ፖለቲካን ከዘር ወይም ከሌላ ማንነት ጋር ባያያዝከው ቁጥር ግጭት ከመፍጠር ውጪ የተረጋጋ ማኅበረሰብ መፍጠር አትችልም።

ፖለቲካው ከብያኔው ጀምሮ የመንግሥት ጉዳይ ከሆነ መንግሥት ደግሞ የሚመለከተው ሁሉንም ሰው ነው። አንዱን ለይቶ ለአንዱ ብቻ መንግሥት ሊሆን አይችልም። መንግሥት ሕግ ሲያወጣ ለኦሮሞ ለብቻው፣ ለትግሬ ለብቻው፣ ለአማራው ለብቻ ብሎ አይደለም። የወጣ ሕግ ሁላችንንም በአገሪቱ ውስጥ የምንኖር ዜጎችን መከተል ያለብን ነው። ፖሊሲም ሲያወጣ ተግባራዊ የሚሆነው ለሁሉም ነው። የአንድ ዘር ተጠቃሚነትን ነው የምፈልገው ብለህ ድርጅት አቋቁመህ የመንግሥት ሥልጣን ስትይዝ እንዴት ነው ሁሉንም ማኅበረሰብ በእኩልነት የምታስተዳድረው።

በብሔር መደራጃት ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያለው ጉዳይ አይደለም እንዴ?
[በብሔር መደራጀት] የሕገ መንግሥቱን ዕውቅና አገኘ ማለት ትክክል ነው ማለት አይደለም። በትክክልም በሕገ መንግሥቱ ተፈቅዷል፤ ነገር ግን ችግሩን እየፈጠረ ያለው ይሔ ሕገ መንግሥት ነው እያልን ነው። ለዚህ ነው ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል፣ እንወያይ፣ ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለውን ማየት አለብን የምንለው።

ሕገ መንግሥቱ ላይ ተጽፏል ማለት ይሔ ጉዳይ መነሳት የለበትም ማለት አይደለም። ሕገ መንግሥቱ ጥሩ የሆኑ ነገሮች አሉት፤ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮችም አሉት። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ እንደዚህ ይላል ማለት ትርጉም የለውም።

ከዚህ በመነሳት ኢዜማ በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
[ሕገ መንግሥቱ] መሻሻል አለበት። የሕገ መንግሥት ማሻሻሉ ምናልባት ዛሬ መሆን የለበት ይሆናል። ተቀባይነት ያለው ምርጫ ተካሒዶ ኅብረተሰቡ የፈለገውን ከመረጠ በኋላ [የሕዝቡ ወኪሎች] ቁጭ ብለው ስለ ሕገ መንግሥቱ በራሳቸው መካከልና ከኅብረተሰቡ ጋር በመወያየት በየትኛው መንገድ ብንሔድ ይሻላል የሚለውን መወሰን አለባቸው ብለን እናምናለን።

እውነተኛ ምርጫ ለማካሔድ የመጀመሪያው ጉዳይ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር ነው። ከዛ በኋላ ተቋማትን ማጠናከር፣ ሕጎችን ማሻሻል በመጨረሻም እውነተኛ ምርጫ ማካሔድ ይቻላል። የሕዝብ ውክልና ያገኙ ሰዎች ሲመጡ ብዙ ነገሮች ለክርክር መቅረብ አለባቸው፤ “ሕገ መንግሥቱን እንቀጥልበት ወይስ እናሻሽለው? ስርዓቱ ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዘዳንታዊ ይሁን? ክልሎች ዘርን መሰረት አድርገው መቋቋም አለባቸው ወይስ ሌላ መንገድ ይፈለግ?” በሚሉትንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክንያታዊነት የተላበሱ ውይይቶችና መመቻመቾች ያስፈልጋል። በመጨረሻም ሕዝብ የወሰነውን መቀበል ነው። ይህ ሒደት መካሔድ ያለበት።

ኢዜማ በኢትዮጵያ ማንነትን መሰረት ያደረገ አድሎና ጭቆና ነበረ ብሎ ዕውቅና ይሰጣል? ዕውቅና ከሰጠ፣ የብሔር ጭቆና በምን መልኩ መፈታት አለበት ብሎ ያምናል?
ነፃነት በሌለበት አገር ውስጥ ሁሉም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ተጨቁኗል። መንግሥት ከፈቀደልህና ከፈጠረልህ ማዕቀፍ ውጪ ማሰብ፣ መናገር አትችልም። በዛ በኩል ነበረብኝ ቢል በእርግጥ ሁላችንም ተበድለናል። ለዚህ ነው እኮ አዲስ ስርዓት እንዲፈጠር የምንፈልገው። በፊት ተበድያለሁ [ይላሉ] ስለዚህ አሁን ምን ይሁን? ማድረግ የሚገባን በጋራ በደል የማይኖርበት ስርዓት መፍጠር ነው።

ኢዜማ በንጽጽር ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘባቸውና ጠንካራ መዋቅር የገነባባቸው ክልሎች የትኞቹ ናቸው? በንጽጽር ዝቅተኛ ተቀባይነት ያገኘባቸውስ? ለምን?
እዚህ አገር ከመጣን ወደ ሰባት ወር ገደማ ሆኗል። በሰባት ወር ውስጥ 312 ወረዳዎች አደራጅተህ እዛ ወረዳ ያሉ ሰዎች የራሳቸውን ሰዎች መርጠው፣ ወኪሎቻቸውን መላካቸው መቼም ተአምር ነው፤ ዝም ብሎም የመጣ አይደለም። በዚህ ሒደት ውስጥ ያልተወከለ ክልል የለም።

ሁሉም ክልሎች ላይ የድርጅት መዋቅር ተዘርግቷል። በርግጥ አንዳንዶች ከሌሎች ብዙ ናቸው። አዲስ አበባ መቶ በመቶ ወረዳዎችን አደራጅተናል። በአማራ ወይም በደቡብ ክልል ደግሞ መቶ በመቶ አደራጅተናል ማለት አይደለም። ምርጫው እስከሚቃረብ በ547ቱም ወረዳዎች የድርጅት መዋቅር ይኖረናል፤ ተወዳዳሪዎችም ይኖሩናል። ያንን ለማሳካት እየሠራን ነው።
የዜግነት ፖለቲካ የበለጠ የት ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለውን አላውቅም። ምርጫ ካልተካሔደ እንዴት ነው የሚታወቀው? የሕዝብ አስተያየት የሚሰበሰብበት ሁኔታ የለም። ከዚህ ውጪ የሚኖረው ግምት ነው። እውነተኛ ምርጫ ሲደረግ የኅብረተሰቡን ስሜትና ፍላጎት የት ላይ እንደሆነ ማየት ይቻላል።

በምርጫ ‘97 ጊዜ አንድ ወንበር አታሸንፉም ተብለን ነበር። [በተግባር ግን] ተቃዋሚዎች የቻሉበት ሁኔታ ነበር። ለዛ ነው መንግሥት ያፈነው፤ መንግሥት እስካላፈረ ድረስ እና ነፃ ምርጫ እስካለ ድረስ የሚሆነውን እናያለን።

በተለያዩ ወቅቶች የተቃውሞው ጎራ በውኅደት፣ ቅንጅትና ኅብረት በመፍጠር በአጭር የሚቀጩ ወይም ደካማ ሆነው የሚዘልቁ ስብስቦችን አስተናግዷል። ዘላቂነት ያለው ተገዳዳሪ ፓርቲ በመሆን የመንግሥት ሥልጣን ሊይዙ አልቻሉም። በዚህ ረገድ የ1997ቱ ቅንጅት ተጠቃሽ ነው። ከዚህ አንጻር ኢዜማ ላለመከፋፈሉና ላለመፍረሱ ምን ዋስትና አላችሁ?

የተነሳህበት መንደርደሪያ ሐሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ አልቻሉም የሚል ነው። ይሔ ማለት የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ የሚያስችል የፖለቲካ ስርዓት እንዳለ አድርገህ ነው የምታወራው።

የኢሕአዴግ ጥንካሬ ወይም አንባገነንነት ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎች ደካማነት ይነሳል። እንደ ምርጫ ‘97ቱ ቅንጅት ጠንክሮ በመውጣት ተገዳዳሪ መሆን አይቻልም ወይ?
በዛን ወቅት ተቃዋሚዎች ያሸነፉት እኮ በኢሕአዴግ ግብዝነት ነው። በተለይ የመለስ [ዜናዊ] ግብዝነት ነው። እሱ የመሰለው ሕዝባዊ ስለሆንን ማንም አይነቀንቀንም፣ ማንም አያሸንፈንም የሚል ነበር። አምባገነኖች ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት ግብዝነት አላቸው። ሁል ጊዜ የራሳቸውን ሐሳብ ብቻ ስለሚሰሙ እውነቱ የእነሱ ብቻ ይመስላቸዋል። እሱ [መለስ] አሸንፋለሁ ብሎ አስቦ በንጽጽር የተሻለ ምርጫ እንዲካሔድ አደረገ፤ ተሸነፈ። ከዛ በኋላ በየፓርቲው የደኅንነት ሰዎች እያስገባ ፓርቲዎቹን መከፋፈል መደበኛ ሥራ አድርጎ ተያያዘው። መንግሥት በሙሉ ኀይሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ እየገባ እንደዚህ ዓይነት ነገር የሚሠራ ከሆነ ሁል ጊዜ የፖለቲካ ድርጅቶችን ማፍረስ ይቻላል።

ይህንን የምልህ በተቃዋሚዎች በኩል ግን ድክመት የለም ለማለት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ግን የምትሳሳቱት [መገናኛ ብዙኀን?] ትልቁን ጉዳይ ትረሱትና በትናንሽ ጉዳይ ላይ ታተኩራላችሁ።

ይሔ አሁን ወደ ፊት የሚካሔደው ምርጫ የማሸነፍና ያለማሸነፍ ጉዳይ የሚወስነው ትርጉም ያለው ‘ነፃ ምርጫ ይካሔዳል አይካሔድም’ በሚለው ነው። ይሔ በሌለበት ሁኔታ ምንም መናገር አትችልም።

ከዛ ውጪ አንተ ላነሳኸው የፖለቲካ ድርጅትቶች መሰነጣጠቅ ያልከው በከፊል የመንግሥት ግፊት፣ በከፊል ደግሞ በፖለቲካ አመራሮች ውስጥ ያለው ድክመት ነው። ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሉበት አገር በአንድ ይሁን በሌላ ምክንያት ደስተኛ ያልሆነ ሰው በቃ እኔ የራሴን ፓርቲ ይዤ እሔዳለው ይላል። ይሔ [በኢዜማ እንዳይደገም] ውሕደት፣ ግንባር የሚል ነገር የለም፤ አንድ ዓይነት አመለካከት ካለህ ተዋሕደህ መቅለጥ ነው።

በኹለተኛ ደረጃ ውሕደቱን ያደረግነው በወረዳ ደረጃ ነው። በከፍተኛው መዋቅር ደረጃ አይደለም። እያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ ያሉ የድርጅት አባላት በጋራ ሥልጣና ወስደዋል፣ ምርጫም አካሒደዋል። ምርጫው በተካሔደበት ቅጽበት ፓቲዎቹ ፈርሰዋል።
ሁላችንም አባሎቻችንን በአዲሱ መዋቅር ውስጥ አሳትፈናል። በላይኛው የፓርቲው መዋቅር ምንም የሆነ ነገር የለም። ውሕደቱ የተፈጸመው እዛው ወረዳ ላይ ነው። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከድርጅቱ ልውጣ ቢል ራሱን ይዞ ይወጣ ይሆናል፤ መብቱ ነው። ድርጅት ይዞ የሚወጣው ነገር የለም። ለዚህ ነው ቀድሞ ሁሉም ፓርቲ መክሰም አለበት ብለን ሁሉም ራሱን ያፈረሰው። በተወሰነ መልኩ ከቀድሞው ልምድ ለመለየት ነው። ስለዚህ [ኢዜማ] የመከፋፈል ወይም የመፍረስ ዕድል ይገጥመዋል ብለን አናስብም። ግለሰቦች ላይመቻቸው ይችል ይሆናል፤ ቢወጡም ራሳቸውን ብቻ ይዘው ነው የሚወጡት።

እንደትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ወይም ግለሰብ አገሪቱ በሰላም እጦት፣ በደቦ ፍርድ፣ ጠርዝ በረገጠ ብሔርተኝነት፣ በማፈናቀል በምትናጥበት ጊዜ ድምጾት ጎላ ብሎ አልተሰማም ለሚለው ትችት ምን ምላሽ አለዎት?
የፖለቲካ ድርጅት ነህ። እንደፖለቲካ ድርጅት ቅድሚያ ሰጥተን የወሰድነው ኹለት ነገር ነው። አንደኛው አገሩ እንዲረጋጋ ማገዝ ነው። ኹለተኛው ጠንካራ፣ ሥር የሰደደ በጣም ሰፊ ድንኳን ያለው የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም ነው።

እኛ ወደዚህ ስንመጣ ምንም ዓይነት መዋቅር አልነበረም። አብዛኛው ሥራችን የነበረው መዋቅር መፍጠር ላይ ነበር። ለምርጫ ብቻ ሳይሆን የአምባገነንነት ግርሻ መልሶ ልምጣ ቢል እንኳን መቋቋም የምትችለው ጠንካራ ድርጅት ሲኖርህ ነው። ዝም ብሎ በመጮኽ አይሆንም።

ኹለተኛ መግለጫ የምታውጣው በከፊል የሚሰማህ ስታገኝ ነው። የሆነ ነገር ተፈጠረ፣ ይሔ ነገር ትክክል አይደለም ብለህ ታምናለህ። ትክክል አይደለም ብለህ ያመንከውን ነገር ለመለወጥና ለሕዝብ ለመግለጽ መግለጫ ታወጣለህ።

በአጠቃላይ አገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩትን ግጭቶች፣ በተመለከተ “ምክንያቱ ምንድን ነው? ምን ቢደረግስ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል?” የሚለውን በቃል ብቻ አይደለም በጽሁፍ ለሚመለከታቸው አካላት ሰጥተናል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላችሁ ብዙ ጊዜ ይወራል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ አጋጣሚ በሕዝብ በቀጥታ የሚመረጥ መሪ እንዲኖር እንደሚፈልጉ የተናገሩበት አጋጣሚም አለ። በዚህ ዓይነት አብሮ በአንድ ፓርቲ ውስጥ የመሥራት አጋጣሚው ይኖረናል ብለው ያስባሉ?
የእኛ ፍላጎት ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊ አገር እንዲኖር ነው። ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አገር በአንድ ፓርቲ ላይ ተመስርቶ አይሆንም። ኹለት ሦስት ጠንካራ፣ መወዳደር የሚችሉ፣ የተለያየ አመለካከት ያላቸው፣ አማራጭ ማቅረብ የሚችሉ ፓርቲዎች መኖር አለባቸው ብለን እናምናለን። ጠንካራ የተቃዋቀሚ ድርጅቶች ያስፈልጋሉ።

ከነዐቢይ ጋር ለዘለቄታው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ አብረን እንሰራለን። ምክንያቱም የጋራ አገር ነው ያለን፣ አገር በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከተበጠበጠ ሁላችንም ነው የሚጎድልብን። ይህንን የለውጥ ሒደት ትክክለኛው ቦታ ላይ አድርሶ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር ካልቻልን አማራጩ ሌላ አንባገነን ማምጣት ሳይሆን የአገር መፍረስ ሊያጋጥም ይችላል፤ ጉዳዩ ቀላል አይደለም።

እኛ የምናየው በረጅም ጊዜ ጠንካራ መደላድል ላይ የሚቆም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዴት እንፍጠር የሚለውን ነው። ይሄን ከሚያስቡ ኃይሎች ጋር በመመካከር የጋራ ስርዓት የማቆም ኀላፊነት አለብን።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መፍጠር የነዐቢይ ብቻ ኀላፊነት ሳይሆን የእኛም ጭምር መሆኑን እንዲረዱም፣ እንዲያምኑም እንፈልጋለን።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ውስጥ አባል በመሆንዎት በግለሰብ ደረጃ ምን እያበረከቱ ነው? ኮሚሽኑስ በተጨባጭ ምን እየሠራ ነው?
ኮሚሽኑ በቅርቡ ነው ሥራ የጀመረው፤ ከኹለት ሦስት ሳምንት በፊት ስብሰባ አድርገን ነበር። አገር ለማረጋጋት ስለሚጠቅም ኮሚሽኑ ሥራውን ቶሎ መጀመር አለበት ተብሎ የተለያዩ ኮሚቴዎች እየተዋቀሩ ነው። እኔም እዛ ላይ እየተሳተፍኩ እገኛለሁ። በቅርቡ ሊቀ መንበሩና ምክትል ሊቀ መንበሯ መግለጫ ሰጥተዋል። በቶሎ ሥራ ይጀመራል ብለን እናስባለን።

በአጠቃላይ ግን ዴሞክራሲዊ ስርዓት ፍትሕና እርቅን ያጣመረ አካሔድ ካልሔደበት በቀር ሁሌም በቁርሾ፣ ሁሌም በጸብ፣ ሁሌም ጠላት የምትለውን በማጥፋት ማቆም አትችልም።

ይህንን የሰላምና እርቅ ሥራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመፍጠሩ ሒደት አንድ አካል አድርጌ ነው የማየው። በታሪክ የተበደለ፣ በግለሰብ ደረጃ የተበደለ፣ ሰብኣዊ መብቱ የተገፈፈበት ሁሉ በተወሰነ ደረጃ የምታጥብበት ነገር ከሌለህ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት አስቸጋሪ ይሆናል።

ብርሃኑ በፖለቲካው ውስጥ በመዳከራቸው፣ አገራቸውን በተሻለ መልኩ በሙያቸው ማገልገል አልቻሉም የሚሉ ተቺዎች አሉ። ከተጠቃሽ ጥንካሬዎት ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ባለሙያዎች ማኅበር ጠንካራ እንዲሆን የሠሩት ሥራ ነው። የእስካሁኑ የፖለቲካ ተሳትፎዎት ፀፀት አሳድሮቦታል?
እኔ በመጣሁበት ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስት ባለሙያዎች ማኅበር ያን ያክል ጠንካራ አልነበረም። በጋራ ሰርተን ጠንካራ የሙያ ማኅበር እንዲሆን አድርገነዋል። ይሔ የሆነበት ዋናው ምክንያት ግን በኢሕአዴግ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተወሰነ ለቀቅ ያለ፣ በተወሰነ ደረጃ መብትን የማካሔድ ነገር ነበር። ከምርጫ ’97 በኋላ ግን አጠፏቸው። ማኀበሩ በአሁን ወቅት የራሱ ሕንፃ ባለቤት ከመሆን ውጪ በጣም ተዳክሟል፤ አሁን ለማጠናከር ግን ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አውቃለሁ።

ስለዚህ ነፃነት በሌለበት የምትሠራቸው ሥራዎች አንተን በተወሰነ ደረጃ የሚጠቅም፣ ገንዘብ የምታገኝበት ሊሆን ይቻላል። ነገር ግን እንደ ኅብረተሰብ አካል የፖለቲካው ሁኔታ ተስተካክሎ እንደዜጋ ማበርከት የሚችለውን በሚመስለውና በሚፈልገው ማድረግ ይችላል። ነገር ግን ምንም ነገር ከፖለቲካ ውጪ የሆነ የለም።

እኔ ሙያዊ ሥራ እሰራለሁ ለሚሉት በግለሰብ ደረጃ ጥሩ ነው ግን የምትሠራበት ከባቢ ወሳኝነት አለው። ነፃነት በሌለበት ከባቢ የምትሠራው ሥራ በጣም ውሱን ነው የሚሆነው።

ዋናው ጉዳይ የተረጋጋ ማኅበረሰብ መፍጠር፣ የተረጋጋ የፖለቲካ ማኅበር መኖር ለማንኛውም ነገር ወሳኝ ነው። እነዚህ እስከሌሉ ድረስ ባለሙያ ነኝ ብለህ ስትጮኽ ብትውል ትርጉም የለውም። ስለዚህ ትችቱ ትክክል አይመስለኝም።

ከፖለቲካ ጡረታ የመውጣት ሐሳብ አለዎት?
አዎ!

መቼ?
ለእኔ በጣም ትልቁ ነገር የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፈጥረን ሁላችንም በየፍላጎታችን መሔድ የምንችልበት ሰላማዊ የሆነ፣ ሰዎች በነፃነት የሚኖሩበት፣ የሚያስቡበት፣ [ሐሳብ] የሚያፈልቁበት ዓይነት የፖለቲካ ስርዓት መፈጥር ከተቻለ በኋላ ችሎታና ፍቅሩ ያላቸው ወጣቶች መጥተው [የፖለቲካ አመራሩን] ሊጋልቡት ይችላሉ። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካለ ማነው መሪው የሚባለው ነገር ኹለተኛ ጉዳይ ይሆናል።

ተቃዋሚ ፓርቲዎች በብዛት የሚተቹት አዳዲስ ወጣት አመራሮችን ወደፊት ማምጣት ላይ ነው። ኢዜማ በዚህ በኩል ምን የተለየ ነገር ይዞ መጣ?
ወጣቶች [ወደ አመራር] እየመጡ ነው። አሁን የተመረጡትን ብዙዎቹን አመራሮች አላውቃቸውም። ዛሬ [ሰኞ፣ ግንቦት 5] ለመጀመሪያ ጊዜ ቁጭ ብለን እንነጋገራለን። እነዚህ አመራሮች የመጡት ከ300 በላይ ወረዳዎች ነው። በጣም ብዙ የሚገርም ችሎታ ያላቸው ወጣቶች እያየን ነው። ይሔ ደግሞ ተስፋ ይሰጥሃል። በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደው መጓተት፣ መሳሳብ፣ ምቀኝነት የሌላቸው በመሆኑ በፍቅር ሥራቸውን የሚሠሩት ወደ ፊት ሲመጡ እያየናቸው ነው። ይሔ ነገር በጥሩ መደላድል ላይ ከተቀመጠ ወደ ፊት መውሰድ የሚችሉ በቂ ሰዎች አሉ ብዬ አምናለው።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here