ሲቪል ማኅበራት ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ

0
613

ቀጣዩ ምርጫ በመደበኛ ሰሌዳው በግንቦት ወር 2012 ይካሔዳል ተብሎ ይጠበቃል። ሳምሶን ኃይሉ ለዚህ ምርጫ ጊዜያዊ አጀንዳዎችን እየመረጡ ከማስጮህ በስተቀር ዘላቂ አማራጭ የሚያቀርቡ የፖለቲካ ድርጅቶች አይስተዋሉም በማለት፣ እንደ መፍትሔ የሲቪል ማኅበራት ሚናን ይጠቅሳሉ።

 

በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ጤናማ የሆነ ውድድር በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት ውስጥ ትልቅ ሚና አለው። ፓርቲዎች አካባቢያዊ፣ ክልላዊ እና አገር ዐቀፋዊ የሆኑ የዜጎችንና የኅብረተሰብ ፍላጎቶችን ከማንፀባረቅም አልፈው ከሌሎች ሐሳቦች ጋር በማስታረቅና በመደመር ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማረጋገጥም ሆነ ዴሞክራሲን እውን ማድረግ ይችላሉ። ለዚህ ነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዴሞክራሲ ዋልታ ናቸው የሚባለው።

በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በለውጥ ሒደት ውስጥ ላሉ አገሮች ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለማምጣትም ሆነ ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የትየለሌ ነው። ነገር ግን ይህ የፓርቲዎች ሚና የሚወሰነው በአገሪቱ ባለው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ጥንካሬና በፓርቲዎች አደረጃጀት ነው።

የመድበለ ፓርቲ ስርዓት ጥንካሬ የሚለካው በአንድ አገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ፖርቲዎች ብዛት ሳይሆን እያንዳንዱ ፖርቲዎች ባላቸው ተቀራራቢ የሆነ አቅምና ለማሸነፍ በሚኖራቸው እኩል ዕድል ነው። ብዙ መገለጫዎች ቢኖሩትም የአባሎችና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ብዛት የፓርቲዎችን አቅም ከሚወስኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች ቢኖሩም አንዳቸውም እንኳን ከገዢው ኢሕአዴግ ጋር በትንሹም እንኳን የተቀራረበ አቅም የላቸውም።
የፓርቲዎችንም አደረጃጀት ስናየው በርዕዮተ ዓለምና ፖሊሲ ቀመስ አስተሳሰቦች ዙሪያ ከመታቀፍ ይልቅ ብዙዎቹ በብሔር ጉያ ውስጥ መሸሸግን መርጠዋል። የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማኅረሰብ ዐቀፍ ችግሮችን የሚፈቱ ሐሳቦችን ከማንሸራሸር ይልቅ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ደርዝ የሌላቸው አጨቃጫቂ የሆኑ ጉዳዮችን በማራገብ ተጠምደዋል።

ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 39፣ የፌደራል ስርዓቱ አወቃቀር እና የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ በፓርቲዎች በስፋት ከሚራገቡ ጉዳዮች መካከል ዋነኛዎቹ ናቸው። ለእነዚህ ጉዳዮች በአጭር ጊዜ እልባት ማግኘት እንደማይቻል እያወቁም ቢሆን ጉዳዮቹን በማጮህ ፓርቲዎቹ ጊዜያዊ ተቀባይነት ለማግኘት እየተውተረተሩ ነው። ዋና ዓላማቸው በሚቀጥለው ምርጫ የተቻላቸውን ያህል ወንበር ማግኘት ስለሆነ ከደጋፊዎቻቸው ዝንባሌ ጋር ይሔዳል ብለው ያሰቧቸውን ሐሳቦች ማራገብ ሥራዬ ብለው ይዘውታል።

እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ሆኖ በእነዚህ ደርዝ አልባ ጉዳዮችና የፖለቲካ ጥያቄዎች አለመጠለፍም አይቻልም።በሊቀ መንበሩ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኩል ከፀሐይ በታች በሁሉም ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ዝግጁ ነን ሲል የነበረው የኦሮሞ ዲሞክራሲራዊ ፓርቲ እንኳን በሌሎች ፓርቲዎች ለተነሳው ሐሳብ ምላሽ ለመስጠት ከጥቂት ወራቶች በፊት በፌደራሉ ስርዓት ላይ አልደራደርም ብሎ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው።

የፌደራል ስርዓቱ የሚፈርሰው ወይንም የሚቀጥለው ፓርቲዎች ስላሉ አይደለም። ለእንደዚ ዓይነት ጉዳዮች እልባት ለማግኘት ረጅም ጊዜና ጠለቅ ያለ ውይይት ከማስፈለጉም በላይ የአብዛኛውን ድጋፍ ይሻል። በመሆኑም ጉዳዩን በማጦዝ ሊገኝ የሚችለው ለአጭር ጊዜ የሚቆይ የፖለቲካ ቅቡልነት እንጂ ዘለቄታ ያለው መፍትሔ አይደለም። እንደውም በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ምክንያት እርስ በርስ ግጭትና መፈናቀል በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ነገር እየሆነ መቷል።

ስለዚህም ነው ቅደም ተከተላቸውን የጠበቁ የመወያያና የመወዳደሪያ ሐሳቦችን አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታና የሚቀጥለውን አገር ዐቀፍ ምርጫ ባገናዘበ መልኩ ማመንጨት የሚገባው። እዚህ ላይ የመወዳደሪያ ሐሳቦችና ሕዝባዊ ጥያቄዎች በቅደም ተከተል እንዴት ማደራጀት ይቻላል የሚለውን ማብራራት ያስፈልጋል። ይህ ሥራ በመጀመሪያ ሁሉንም የተለያዩ የኅብራተሰብ ክፍሎች የሚነሱትን ሐሳቦች በዝርዝር ማስቀመጥን ይጠይቃል። በመቀጠልም በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸውን ጉዳዮች መለየት ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላ አንኳር እና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ በዋነኝነት ትኩረት ሰጥቶ በሙሉ አቅም እልባት ለመስጠት መንቀሳቀስ ነው።

ለምሳሌ በአሁኑ ሰዓት በዞንና በክልል የመደራጀት፣ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻልና የመቀየር እና ከፌደራል መዋቅሩ ጋር የሚነሱ ሐሳቦች ብቻ ሳይሆኑ ሰላማዊ ሥልጣን ሽግግር ማሳካት፣ የሥራ ዕድል እጦት፣ የሸቀጦች ዋጋ መጨመር እና አንፃራዊ ሰላም በአገሪቱ ውስጥ ማስፈን የመሳሰሉ ጉዳዮች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይነሳሉ። ለእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች እልባት ለማግኘት ግን በመጀመሪያ አንኳር የሆኑትንና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚገባቸውን በመለየት በቶሎ ወደ ሥራ መግባት ያስፈልጋል። በኔ አመለካከት ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ማረጋገጥ እና የሥራ አጡን ችግር መቅረፍ የመሳሰሉ ጉዳዮች አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ የሚያስማሙና ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆኑ የሚገባቸው ናቸው። ይህ ማለት ለሌሎች ጉዳዮች እልባት መስጠት አይገባም ማለት አይደለም። ከላይ የዘረዘርኳቸውንም ሆነ ሌሎች አንኳር የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት ግን በመጀመሪያ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የሆነ ሥልጣን ሽግግር ማረጋገጥ ይጠይቃል። የዚህ ግብ መሳካት አብላጫውን ድምፅ ያገኘው ፓርቲ ወይንም የፓርቲዎች ጥምረት ሁሉንም ባሳተፈና ሰጥቶ መቀበል መርሕ ላይ በተመሠረተ አካሔድ በመካከለኛና ረጅም ዕቅድ አካቶ ሁሉንም ጉዳዮች እንዲመልስ ያስችለዋል።

እዚህ ላይ በዋነኛነት መነሳት የሚኖርበት ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚነሱትን ጥያቄዎች በቅደም ተከተል አደራጅተውና በነሱ ላይ ተከራክረው ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ማረጋገጥ ይችላሉ ወይ የሚለው ነው። በኔ እምነት በተልፈሰፈሰ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እና ባልተገባ የፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ ሆኖ ይህን ማምጣት ይቻላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

ለዴሞክራሲ አዲስና የተሳካ ሥልጣን ሽግግር በቅርቡ ማረጋገጥ የቻሉ እንደ በርማ ያሉ አገራት ተሞክሮ የሚያሳየው የሲቪል ማኅበራት ሚና በዚህ በኩል ወሳኝ መሆኑን ነው። በእነዚህ አገራት እንደታየው የሲቪል ማኅበራት በፓርቲዎች መካከል ለሚደረግ ክርክር የሚያስፈልገውን እንደ ቦታና የመከራከሪያ ሐሳቦች ገለልተኛ በሆነ መንገድ በማዘጋጀት ለመራጩ ሕዝብ ትክክለኛ ነው የሚለውን ፓርቲ እንዲያማርጥ ከፍተኛ እገዛ ከማድረግም በዘለለ ጤናማ ውድድር እንዲኖር የማስቻል አቅም አላቸው። በዋነኝነት በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማኅበራትን ተመራጭ የሚያደርጋቸው ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለማምጣትና ዴሞክራሲን ለማስፈን በመቻላቸው ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ፍላጎት የሌላቸው በመሆናቸው ጭምር ነው። ይህም ሒደቱ ለሚጠይቀው ገለልተኛ የሆነና የሁሉንም ፍላጎት ሊያካትት የሚችል ተቋም በቂ ምላሽ ይሰጣል።

ከመደበኛው አደረጃጀት ባሻገር ግን የሲቪል ማኅበራት ገለልተኛ የሆኑ ምሁራንን ሊያሳትፉ ይገባል። የእነዚህ ምሁራን ሚና የሚሆነው ከዘርና ጎጥ ፖለቲካ እራሳቸውን አላቀው ፓርቲዎች የሚከራከሩበትን ሐሳብ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማደራጀት አጀንዳ ማሰናዳት ነው።ይህ ምሁራንን የማሳተፍ እንቅስቃሴ ግን ጥንቃቄ የሚያሻው ጉዳይ ነው።

የሲቪል ማኅበራት ለሚያሳድሩት በጎ ተፅዕኖ ኢትዮጵያዊያን አዲስ አይደለንም። በ97 ምርጫ መባቻ እንዳየነው በጥቂት የሲቪል ማኅበራት በተዘጋጁ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዲግ እንኳን አላመነታም ነበር። ምክንያቱም ገለልተኛ በሆኑና በዘርፉ ዳጎስ ያለ ዕውቀት ባላቸው ምሁራን ድጋፍ በሲቪል ማኅበራት በተዘጋጀ መድረክ ላይ አለማሳተፍ የሚያስከፍለውን ኪሳራ ሁሉም ፓርቲዎች ኢሕአዴግን ጨምሮ በመገንዘባቸው ነበር።

በ97 ምርጫ የሲቪል ማኅበራት ያሳደሩት ተፅዕኖ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና መንግሥታት እያወገዙትም ቢሆን ኢሕአዴግ አዲስ አዋጅ አውጥቶ የሲቪል ማኅበራት ለማዳከምና ቀስ በቀስ ለማክሰም በቅቷል። በዚህ አዋጅ መሠረት ከ10 ፐርሰንት በላይ በጀታቸውን ከውጭ የሚያገኙ የሲቪል ማኅበራት እንደውጭ አገር ተቋም በመቆጠራቸው ዴሞክራሲ ማስፋፋትና ሰብኣዊ መብቶችን ማስከበር ከመሳሰሉት እንቅስቃሴዎች እንዲገለሉ ተደርገዋል። እንደ “The Observatory for the Protection of Human Rights Defenders” ዘገባ፥ 17 የሚሆኑ የሲቪል ማኅበራት በዚህ ምክንያት ዘርፍ እንዲቀይሩ ወይንም ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ተገደዋል። ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ እንቅስቃሴያቸውን ቀንሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ ቡኋላ አንደኛው ሥራቸው ያደረጉት ይህን አዋጅ ማሻሻል ነበር። ከወራቶች በፊትም አዋጁ ማሻሻያ ተደርጎበት በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትም ሆኑ መንግሥታት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። አሁን የሚቀረው በተቻለ ፍጥነት የተዘጉትን የሲቪል ማኅበራት ወደ ሥራ እንዲገቡና ያሉትንም ማጠናከር ነው። ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ማረጋገጥ ይገባል።

ሳምሶን ኃይሉ የአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት የሆነችው ʻኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪውʼ ምክትል መራሔ አሰናጅ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው ebr.magazine1@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here