ኹለቱ ጎራዎች የዜግነት እና የማንነት ፖለቲካ ተመጋጋቢ ወይስ ተቀናቃኝ?

0
743

ስመኝ ታደሰ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጫወታ ማንነታችሁን ቀምቼ ሌላ ማንነት ካልሰጠኋችሁ እያለ ከሚታገላቸው ሰዎች አንዷ ናት። ተወልዳ ያደገችው ቡሌ ሆራ ነው። ቡሌ ሆራ በቀድሞው አስተዳደር የሲዳማ ክፍለ ሀገር ውስጥ የሚገኘው ሀገረ ማርያም ወረዳ አካል ነበር። ስመኝ በወቅቱ ለሥራ ጉዳይ ከኮሬ ወደ ሀገረ ማርያም የሔዱት አባቷ የጉጂ ኦሮሞ ተወላጅ ከሆኑት እናቷ ጋር ትዳር መሥርተው ካፈሯቸው ልጆች አንዷ ናት።

ስመኝ “እንደ የሀገረ ማርያም ልጅነቴ ከአካባቢው ተወላጆች ሥነ ሕዝብ፣ ሥነ ቃልና የልጅነት ጫወታዎች በተጨማሪ ከከተሜው (በአብዛኛው በአማርኛ) ከነበሩን የልጅነት ጨዋታዎች እና ሥነ ቃላዊ ሁነቶች እኩል እየተጠቀምኩ አድጌያለሁ፡፡ ይህንን ውሕድ ማንነቴን ግን በዚያ መልኩ በአዋቂነቴ ዘመን ለማስቀጠል እስኪፈታተነኝ ድረስ ወይም ደግሞ ቋንቋ መምረጥ እስኪኖርብኝ ድረስ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖብኛል – የፖለቲካው ስርዓት።”

የጉጂ ኦሮሞን ባሕል አንስታ “ሁሉንም ነገር እወደዋለሁ። ቋንቋው፣ የገዳ ስርዓቱ፣ ሁሉም ነገሮች የኔ ናቸው” የምትለው ስመኝ፣ የሆነው ሆኖ ራሷን የየትኛውም ነጠላ ጎሳ አባል አድርጋ ለመግለጽ ባትገደድ ኖሮ እንደማትመርጥ ትናገራለች። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልማድ ማንነት የሚወረሰው ከአባት በመሆኑና አባቷ የኮሬ ተወላጅ በመሆናቸው ምክንያት ከዚህ በፊት ለአጭር ጊዜ በሠራችበት የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ወገን ለማድረግ ሲሞክሩ እንደገጠሟት ትናገራለች።
ኮሬ አሁን በደቡብ ክልል ውስጥ ነው የተካለለችው። የጉጂ ኦሮሞ ነዋሪዎች ግጭት ውስጥ ከገቡባቸው አካባቢዎች አንዱ ኮሬ ነው። ስመኝ “ይሄ ማለት በቀጥታ ግለሰቦቹ በግጭቱ ባይሳተፉበትም የአባቴ ቤተሰቦች እና የእናቴ ቤተሰቦች ግጭት ውስጥ ናቸው እንደማለት ነው” ትላለች። የስመኝ ታሪክ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የገባበት የማንነት እና አረዳዱ እንዲሁም ማዕከላዊ የአስተዳደር አስኳል መሆኑ የፈጠረው ውስብስብነት አንድ ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም እንኳን በርካታ ተዋናዮች ቢኖሩትም፥ በኹለት ዋነኛ የፖለቲካ ኀይሎች ፍጥጫ ተወጥሯል። እነዚህ ኀይሎች መሠረታዊ ልዩነታቸው የሚወሰነው በመሰባሰቢያ መሥፈርታቸው ነው። አንደኛው ኀይል የመሰባሰቢያ መሥፈርቱን የዘውግ ማንነት ያደረገው እና የዘውግ ብሔርተኛ (ethnonationalism) በሚለው ማዕቀፍ የሚጠራው ነው። ሌላኛው ኀይል የመሰባሰቢያ መሥፈርቱን ዜግነት ላይ ያደረገው እና በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ የሚል መጠሪያ እተጠራ ያለ ስብስብ ነው፤ ከዚህ ቀደም ኅብረ ብሔራዊ እና ዘውግ ዘለል የሚሉ መጠሪያዎች ለተመሳሳይ የፖለቲካ ቡድኖች ይሰጥ ነበር። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔርተኛ የሚሉትም አሉ።

የመጀመሪያው ቡድን በጥቅሉ ‘የማንነት ጥያቄዎች የሚፈቱት በብሔርተኝነት ነው’ የሚል መሠረታዊ ፍልስፍና ያለው ሲሆን፥ ሌላኛው ደግሞ ‘የማንነት ጥያቄዎች የአንድ ቡድን ችግር ብቻ ስላልሆኑ መልስ የሚያገኙትም ዜጎችን በሙሉ በአንድ ማዕቀፍ ባሰባሰበ ስርዓት ነው’ ይላል።

ለመሆኑ በኹለቱ የፖለቲካ ስብስቦች እና የመሰባሰቢያ መሥፈርቶች መካከል ያለው አንድነት እና ልዩነት ምንድን ነው? የዜግነት ፖለቲካ ለማንነት ጥያቄዎች አደጋ ፈጣሪ ወይስ የመፍትሔው አካል?

የማንነት ፖለቲካ ማንሰራራት
የማንነት ፖለቲካ በዓለም ዙሪያ እያንሰራራ ነው። ብሔርተኝነትም እንደዚሁ። የእንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት መውጣት እና የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ፣ አልፎ ተርፎም በአውሮፓ ውስጥ አክራሪ ብሔርተኞች ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘታቸው ምዕራባውያን ልኂቃንን ያስደነገጠ ገጠመኝ ሆኗል። የምዕራባውያን ማንነት ፖለቲካ በምዕራባውያን አረዳድ በተለይ ከዘር (በቆዳ ቀለም እና የፊት ቅርፅ)፣ የስርዓተ ፆታ፣ እና የፆታ ግንኙነት ምርጫ ላይ የተመሠረተ ነው።

ብሔርተኝነታቸው ደግሞ በአመዛኙ አገረ መንግሥታቱ (the states) ከተመሠረቱባቸው መሠረታዊ ፍልስፍናዎች – ማለትም ነጮችን የበላይ ያደረገ መሠረት ያደረገ እና ስደተኞችን በመጠየፍ ላይ የቆመ ነው።

የአገረ መንግሥታት ምሥረታ የጀመረው በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ሲሆን፣ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ተጧጡፏል። የአገረ መንግሥት ምሥረታው መሣሪያ ያደረገው ብሔርተኝነትን ነበር። በመሆኑም በተለይ ማንነት ጭፍለቃ (assimilation) ዋነኛ ስልቱ ነበር። በዚህ መንገድ የተመሠረቱት አውሮጳ አገራት ባብዛኛው ሕዝባቸውን ወጥ ማንነት ያለው ለማድረግ በቋንቋ እና ሃይማኖት ረገድ በርካታ ጭፍለቃዎችን አከናውነዋል። በዚህም ብዙዎቹ ብሔረ መንሥት (Nation State) የሚል መለያ አግኝተዋል። ሆኖም የማንነት ፖለቲካ እስከ ዛሬም ድረስ አልተለያቸውም።

ዊሊያም ሳፍራን የዓለም ዐቀፉ የፖለቲካል ሳይንስ ጆርናል ላይ ‘State, Nation, National Identity, and Citizenship: France as a Test Case” በሚል ባሳተሙት ጥናታቸው ላይ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ በጃኮቢኖች የተፀነሰው ጠንካራ እና ማዕከላዊ የፈረንሳይ ብሔረ መንግሥት የመገንባት ሥራ እስካሁንም አወዛጋቢ ሆኖ መቀጠሉን የገለጹት በአግራሞት ነው፦ “ከኹለት ክፍለ ዘመናት በላይ በፖለቲካ የተዋሐደችው እና ይህንኑ ለሚያህል ጊዜ የረጋ ዳር ድንበር የነበራት ፈረንሳይ እስከዛሬ ድረስ ብሔራዊ ማንነትን በተመለከተ ችግር ያለባት መሆኑ እንግዳ ነገር ሊሆን ይችላል።” ከሞላ ጎደል ወጥ ማንነት ያላት የምትመሥለው ፈረንሳይ ዛሬም የማንነት ፖለቲካ የሚንጣት መሆኑ፥ የማንነት ፖለቲካን እና ብሔርተኝነትን የማያቋርጥ፣ እንዲያውም አንዳንዴ እየገነፈለ የሚያስቸግር ዥረት ያስመሥለዋል።

የኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት፣ የማንነት ፖለቲካን “የአንድ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ማኅበራዊ ስብስብ፣ ወዘተ. አባላት ከተለመደው መሠረተ ሰፊ የፖለቲካ ፓርቲ ያፈነገጠ የጋራ የፖለቲካ ስብስብ የመፍጠር ዝንባሌ ነው” በሚል ይፈታዋል። ብሔርተኝነትን ሲተረጉመው ደግሞ “ራስን ከብሔር ጋር አቆራኝቶ መግለጽ እና በተለይም ደግሞ በሌሎች መገለል እና መጎዳት የሚገኝ የዚያ ብሔርን ተጠቃሚነት መደገፍ ነው” ሲል ይፈታዋል።

ነገር ግን ይህ ብያኔ በትክክል ገላጭ እንዳልሆነ የሚከራከሩ አሉ። የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ምርምር ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) “የብሔርተኝነት ርዕዮተ ዓለም ሌሎችን በማጥቃት ላይ የተመሠረተ አይደለም” ይላሉ። “ይልቁንም የሰው ልጅ በተፈጥሮው የተከፋፈለ ነው ብሎ የሚያምን እና ይህም እንዲከበር የሚታገል ርዕዮተ ዓለም ነው። ብሔርተኝነት ሰዎች በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በጋራ አመጣጥ ታሪክ፣ በእውነተኛ ወይም ምናባዊ ግዛት እና ወዘተ. ተከፋፍለዋል ብሎ የሚያምን ርዕዮተ ዓለም ነው።” ብርሃኑ አክለውም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ የማያስገባ ርዕዮተ ዓለም ከፈተና እንደማያመልጥ ጠቁመዋል።

ክብር እና ዕውቅና
የማንነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ዐውድ ከቋንቋ እና ባሕል ጋር ብቻ ተቆራኝቶ የተሳለ ቢሆንም ከዚህ የሰፋ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በአጭር አገላለጽ የማንነት ፖለቲካ የእኩል ክብር እና የእኩል ዕውቅና (dignity and recognition) ጥያቄ ነው። እነዚህ ማንነቶች በዘር፣ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በስርዓተ ፆታ፣ በፆታዊ ግንኙነት ምርጫ ወይም ወዘተ. ሊለያዩ ይችላሉ። ሆኖም የኢትዮጵያ ፖለቲካ የተቃኘበት ቅኝት ቋንቋን እና ባሕልን መሠረት ያደረገ የማንነት ፖለቲካ መሆኑ ሌሎቹን የማንነት ጥያቄዎች ወይም ማንነቶችን ሳይቀር የሚደፈጥጥ የማንነት ፖለቲካ ሆኗል። ቀድሞ በተማከሉት የዘውዳዊው እና የደርግ አስተዳደሮች ወቅት የበለጠ ዕውቅና ተሰጥቶት የነበረው ኢትዮጵያዊ ማንነት በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ለብሔር ማንነቶች ከተሰጠው ፖለቲካዊ ዕውቅና ያነሰ ዕውቅና ተሰጥቶት ነው የከረመው።

ከዚህም በከፋ የማንነት ፖለቲካው በዘር ግንድ የሚቆጠር መሆኑና የአባት ውርስ ተደርጎ መበየኑ እንደ ስመኝ ያሉትን ሰዎች ‘አለን’ የሚሉትን ሌላ ማንነት ‘የላችሁም’፣ ‘ይህም የኔ፣ ያንኛውም የኔ’ የሚሉትንም ‘አይ አንዱን ምረጡ’ ማለት የሚዳዳው ሆኗል። የስመኝ የሕይወት ተሞክሮ የሚያሳየን አንድ ነገር ቢኖር፥ ማንነት ተለዋዋጭ መሆኑንና ያንን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ምኅዳር የሚፈልግ መሆኑን ነው። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ፖለቲካ የዜጎችን ማንነት ራሳቸው እንዲመርጡ ወይም እንዲወስኑ ከማድረግ ይልቅ ሌሎች ሰጪ እና ነሺ ሆነው መገኘታቸው ሌላኛው አስቸጋሪ ሁኔታ ነው።

የአርበኞች ግንቦት ሰባት የውጭ ግንኙነት ኀላፊ የነበሩት አዚዝ መሐመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ነባራዊ ፖለቲካ ራሳቸውን የት ቦታ ማስቀመጥ እንዳለባቸው እንደሚቸግራቸው ይናገራሉ። “እኔ ለምሳሌ ተወልጄ ያደግኩት ወሎ ነው፤ በተለምዶው አተረጓጎም ምናልባት ‘አማራ’ ነው እባል ይሆናል። ሆኖም ሉላዊ ዜግነት (‘ግሎባል ሲቲዝንሺፕ’) እንኳን አይበቃኝም። እናም ሁሉም ሰው የዘውግ ማንነት ይኖረዋል ብሎ ማሰብ አሊያም ማንነቱ በአንድ አተረጓጎም ውስጥ ነው የሚለው አስተሳሰብ በራሱ የተሳሳተ ነው” በማለት የአረዳዱን ችግር ለመለየት ይሞክራሉ።

በሌላ በኩል የስርዓተ ፆታ ጉዳይ እንደ ማንነት ጥያቄ አይቆጠርም፤ የአንድ ሰው ማንነት ከአባት ማንነት በቀጥታ የሚወረስበት ያልተጻፈ ሕግ አለ። ቅይጥ ማንነት ከግምት ውስጥ አይገባም። ከሁለት አንዱ መምረጥ ብዙ ጊዜ የግድ ይመስላል።
በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሕግ እና የፖሊሲ ጆርናል ላይ ‘አምስት የማንነት ፖለቲካ አንብሮዎች (theses)’ በሚል ርዕስ ትንታኔያቸውን ያስነበቡት ሪቻርድ ፓርከር በአንደኝነት ደረጃ ያስቀመጡት “ሁሉም ፖለቲካ የማንነት ፖለቲካ ነው” የሚለውን ነው። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የራስን ወይም የሌሎችን ምንነት እና ማንነት በመበየን እና መከላከል (define and defend) ላይ የተመሠረተ ነው።

ፓርከር የማንነት ፖለቲካ አንብሮዎችን ሲዘረዝሩ ሁሉም ፖለቲካ የማንነት ነው ከሚለው አንድ ጠርዝ፥ የማንነት ፖለቲካ ለፖለቲካዊ ነጻነት ጠንቅ ነው እስከሚለው ድረስ አንብሮዎች አሉ። ሆኖም ፓርከር ልዩነት ራስን ለመረዳት እና ለመግለጽ ጠቃሚ ሲሆን፣ ብሶትም ቢሆን ፖለቲካዊ ነጻነትን ለማምጣት የሚያነሳሳ ነዳጅ በመሆኑ ልንፈራው አይገባም ባይ ናቸው።

የዜጎች አገር
የዜግነት ፖለቲካ ‘ሲቪክ ፖለቲክስ’ ከሚለው የእንግሊዝኛ አገላለጽ የተወረሰ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ከተፈቀደ ወዲህ በሰፊው ተግባራዊ ከሆነው ማንነትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት በተቃራኒ፣ ቢያንስ በሐሳብ ደረጃ የትኛውንም ዓይነት ማንነት ያላቸውን ሰዎች ለማስተናገድ የተዘጋጀ አደረጃጀትን የሚወክል ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነው።

አና ትሪያንዳፊላይዶ የተባሉ አጥኚ እ.ኤአ. በ2002 “Italy: Nation Formation, the Southern Question and Europe” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታቸው ሁሉም ዓይነት ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ የብሔርም፣ የዜግነትም መልክ እንዳለው አበክረው ይናገራሉ። የዜጎች አገር (‘ሲቪክ ኔሽንስ’) ግን ከብሔረ አገር ያለውን ልዩነት ሲያስቀምጡ እንዲህ በማለት ነው። “የዜጎች አገር – በአንፃሩ – በጋራ የፖለቲካ ባሕል መሠረት ላይ የቆመ እና ለሁሉም አባላቱ እኩል መብቶችን አጎናፅፎ እኩል ግዴታዎችን የሚጥል ሕጋዊ ስርዓት ያለው፣ በነጠላ የሥራ ክፍፍል የቆመ የጋራ ኢኮኖሚ እና በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ እና ፖለቲካዊ መሥመር የተለየ ማኅበራዊ ስብስብ ነው።”

ነገር ግን በኢትዮጵያ በዜግነት መደራጀትን ለማንነት ጥያቄዎች ማፈኛ ወይም የማንነት መጨፍለቂያ መንገድ አድርገው የሚወስዱት በርካቶች ናቸው። ብርሃኑ የዜግነት ፖለቲካ ለማንነት ፖለቲካ እንቅፋት ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ቢገልጹም፣ ዜግነትም በራሱ ማንነት መሆኑን ተከራክረዋል። “ማንነት ሰዎች ራሳቸውን የሚገልጹበት መንገድ ነው። አንድ ሰው በዜግነቱ ራሱን መግለጽ ከጀመረ ዜግነቱ ማንነቱ ይሆናል ማለት ነው” በማለት የክርክራቸውን ፍሬ ሐሳብ ለማስጨበጥ ይሞክራሉ።
ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ሲመጣ፥ የዜግነት ማንነት ሁሉንም አሰባሳቢ እንዳልሆነ ብርሃኑ ይገልጻሉ። እንደርሳቸው አባባል “በኢትዮጵያ የአገር ምሥረታው በተሳካ ሁኔታ ነው የተጠናቀቀው፤ ነገር ግን እንደማንነት የሚቆጠር ዜግነት ለሁሉም በሚሥማማ መልኩ አልተገነባም። ይህንን ለማየት በዜግነት ለማደራጀት ጥሪ የሚያደርጉትን የፖለቲካ ቡድኖች የሚቀላቀሏቸውን ሰዎች ማንነት ማየት በቂ ነው። ባብዛኛው የተማሩ አማርኛ ተናጋሪዎች ብቻ ናቸው። በዚህም ምክንያት ‘ኢትዮጵያዊነት’ እስካሁንም ድረስ ዘውግ ዘለል (‘ነን ኤትኒክ’) አልሆነም” በማለት በዜግነት ጥላ ሥር የሚሰባሰቡት ባብዛኛው ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አዚዝ በአገር አመሠራረቱ ጉዳይ ከብርሃኑ ጋር ይሥማማሉ። “በኢትዮጵያ የተካሔደው አገር ምሥረታ ልክ እንደ ብዙ አገራት በማስገበር ነው” ይሉና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ግን ኢትዮጵያውያን መዘናጋታቸውን ያስታውሳሉ። “ሌሎች አገራት ምሥረታቸውን ሲያጠናቅቁ በቀጥታ የገቡት ወደ ልማት እና ዴሞክራሲ ግንባታ ነው። የኛ ግን ሳይለማ እና ዴሞክራታይዝ ሳያደርግ፣ የእኩልነት ጥያቄን ሳይመልስ ቆመ” ይላሉ።

አዚዝ “አሁን ለቀሩት ጥያቄዎች መልስ መስጠት የምንችለው ወደ ኋላ በመመለስ ሳይሆን ‘ዴሞክራታይዝ’ በማድረግ እና ኢኮኖሚው ላይ በመሥራት እንዲሁም ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ነው” ይላሉ። “አለበለዚያ አንድ ችግር ፈታን ብለን ሌሎች ብዙ ችግሮችን እንፈጥራለን።”

የስርዓተ ፆታ ጉዳይ
የስርዓተ ፆታ እና እኩልነት ተሟጋቿ መምህር ሕሊና ብርሃኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እምብዛም ያልተነሳ የማንነት ጥያቄ ያነሳሉ። የማንነት ፖለቲካው የሴቶችን ጥያቄ እንደማንነት ጥያቄ እንደማያየው አስታውሰው፣ ሁሉም አደረጃጀቶች የሴቶችን ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ ያልተሳካላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በርግጥም በቅርቡ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ምሥረታ ይህንኑ ያስረዳል፤ መሥራች ጉባዔው ላይ ድምፅ ለመስጠት የተገኙት 1170 ወንዶች ሲሆኑ፥ ሴቶቹ ደግሞ 144 ናቸው። 10 ነጥብ 9 በመቶ ማለት ነው። ለዚህ ዓይነቱ ቅሬታ የፓርቲው መሥራቾች መልስ ሲሰጡ ሴቶችን ለማበረታታት ጥረት ማድረጋቸውን ይናገራሉ። እያንዳንዱ የምርጫ ወረዳ ወደ ጠቅላላ ጉባዔው መላክ የተፈቀደለት ትንሹ ቁጥር 3 ቢሆንም፥ ሴት እና አካል ጉዳተኛ መርጠው የሚልኩ ወረዳዎች አምስት (ሴት ወይም አካል ጉዳተኛ የሚልኩ ወረዳዎች አራት) ሰዎች መላክ እንደተፈቀደላቸው ይናገራሉ።
ብርሃኑ ግን “ኢዜማ ርዕዮተ ዓለሜ ማኅበራዊ ፍትሕ ነው ካለ በተለይ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞችን ማኅበራዊ መሠረቱ ማድረግ መቻል አለበት” ብለው ይከራከራሉ።

ሕሊና ሴቶች ወደ ፖለቲካ ድርጅቶች ለመግባት ከወንዶች የበለጠ እንደሚያመነቱ አብራርተዋል። “በመጀመሪያ ደረጃ ወንዶች ያሉባቸው ችግሮች ሁሉ አሉባቸው። ከዚያ በተጨማሪም ግን ሴቶች ቤተሰብ ማማከር ሳይሆን ማስፈቀድ ጭምር የሚጠበቅባቸው አጋጣሚ አለ። የፖለቲካው ከባቢ በራሱ ለወንዶች በወንዶች የተሠራ፣ አርማ የሌለው የወንዶች ማኅበር ስለሆነ ለሴቶች ጋባዥ አይደለም። በዚያ ላይ ሴቶች የሚፈ፡ለጉት ለተሳትፎ ያክል እና ለ‘ሶፍት ፖለቲክስ’ ስለሚመስላቸው፣ ለቁምነገር አለመጠራታቸው ደስ አይልም። በተጨማሪም፣ ሴቶች ብቃታቸውን ለማሳመን ከወንዶች የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ የሚጠበቅባቸው መሆኑ ገፊ ሌላ ምክንያት ነው። ሌላው ወደ ፖለቲካው ሲገቡ ባለው አጨዋወት ነው እንዲቀጥሉ የሚጠበቅባቸው እንጂ እነሱ በሚሥማማቸው መልኩ እንዲሳተፉ አይደረግም” በማለት ለመጨረሻው ሐሳባቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ፕሬስ ሴክሬተሪያቷ ቢልለኔ ሥዩም “ወ/ሪት” ወይም “ወ/ሮ” የሚል ቅጥያ አልፈልግም በማለታቸው ብቻ የደረሰባቸውን ተቃውሞ ይጠቅሳሉ።

የስርዓተ ፆታ እና የአካል ጉዳተኞች ጥያቄን የመሳሰሉት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ቤት አልባ ይመስላሉ። የመሰባሰቢያ መሥፈርቱ ዜግነት የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ለማሰባሰብ ከሌሎች የበለጠ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ዴሞክራሲያዊነት
ብሔርተኞች ብሔርተኝነትን “ሰዎችን በቀላሉ ለማሰባሰቢያ ይጠቀሙበታል እንጂ የሚመሠርቱት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ያለው ቡድን ነው” የሚሉት ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር)፥ እንደሚባለው ‘በማንነታቸው ብቻ ሌሎችን ለማግለል ዓላማ አይሰባሰቡም’ ይላሉ። “በዜግነት ነው የምንደራጀው የሚሉትም ቢሆኑ” በማለት ኢዜማን ይጠቅሱና “የዜጎች ፓርቲ ነው ይበሉት እንጂ የርዕዮተ ዓለም ፓርቲ ነው። ዜጎች 100 ሚሊዮን ናቸው። የእነሱን ፓርቲ የተቀላቀሉት ደግሞ ‘ሶሻል ዴሞክራሲን’ እንደ ርዕዮተ ዓለም የተቀበሉ ዜጎች ናቸው” በማለት አገላለጹ ዜጎች የሚባሉት የፓርቲው አባላት ብቻ እንደሆኑ ያስመሥላል ይላሉ።
ብርሃኑ ለወደፊቱ በማንነቶች መካከል ፉክክር መፍጠር አያስፈልግም፣ “ኢትዮጵያዊነት ከኦሮሞነት ጋር መፎካከር የለበትም” በማለት ይመክራሉ። “አንድ ማንነት የመፍጠሩ ሒደት ያልተሳካ ስለሆነ ቀላሉ መፍትሔ ያለፉትን ኢፍትሓዊ ድርጊቶች በማመን፣ የኢትዮጵያን ኅብረ-ብሔራዊ ማንነት በመቀበል ሁሉንም ዐቃፊ ዜግነት መገንባት ነው” ይላሉ።
አዚዝ መሐመድ (ዶ/ር) በሌላ በኩል “ኢትዮጵያ አሁን ታማ አልጋ ይዛለች” ይላሉ። ስለዚህ መድኅኗ ነው የሚሉት ዜግነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ አሁኑኑ ባያድናትም ቀስ በቀስ እንድታገግም ያደርጋታል ይላሉ። “በኢትዮጵያ የማንነት ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚም ችግር አለ፣ የትምህርት ችግር አለ፣ የጤና አጠባበቅ ችግር አለ፤ ሁሉም መልስ ማግኘት አለባቸው” ይላሉ። ሆኖም በዜግነት መሥፈርት ዜጎችን ማሰባሰብ ባለፉት ዓመታት ከተሠራው ሥራ አንፃር “ሥልጣን እና ሀብት የሚገኝበት መንገድ በመሆኑ፥ የዜግነት ፖለቲካ ሥራ ይጠይቃል” ይላሉ።

አዚዝ እንደሚሉት “በፊት በኢትዮጵያ አለ የተባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ማግለል አሁን ወደ ክልሎቹ ነው የተዘዋወረው። የትኞቹም ክልሎች አንድ ዓይነት ቋንቋ እና ባሕል ያላቸው ሰዎች መኖሪያ አይደሉም። ክልሎቹ በውስጣቸው ላሉት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎች እኩል ዕድል አልሰጡም። በዜግነት ፖለቲካ ግን እነዚህን ችግሮች መቅረፍ ይቻላል፤ የቱም ዜጋ የትኛውም አካባቢ ሔዶ መኖር፣ መሥራት፣ መምረጥ እና መመረጥ መቻል አለበት” በማለት የዜግነት ፖለቲካ የማንነት ጥያቄዎችን እንደማይጨፈልቅ አስረግጠው ይናገራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here