የራስን ዕድል በራስ መወሰን

0
1021

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአንቀጽ 39ን ያህል አወዛጋቢ አንቀጽ የለም። “የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል”። አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋስኦ ውስጥ የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለውን ብዙ ሰዎች የሚረዱት የአስተዳደር ጉዳይ ሳይሆን የመገንጠል ጉዳይ አድርገው ነው። “እስከ መገንጠል” የሚለው ቃል የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚለውን ተጭኖታል።
በመሠረቱ “የራስን ዕድል በራስ መወሰን” (self-determination) የሕግ ቋንቋ ነው። ብዙ፣ በተለይም በፌዴራል የአወቃቀር ስርዓት የሚተዳደሩ አገራት የራስን ዕድል በራስ መወሰን የሚል ሐረግ ሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ቢያስገቡም እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ግን ግልጽ አያደርጉትም።

ናሽናሊያ የተባለ የካናዳ ጋዜጣ “መገንጠልን” መብት ያደረጉ ዐሥር አገራትን ሲዘረዝር የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት “የመገንጠል መብትን እና የብዙኀን አገርነቷን በተመለከተ ምናልባትም የዓለማችን የመጨረሻ ግልጹ ሕገ መንግሥት ነው” ይለዋል። (“This is probably the world’s explicit constitution regarding secession and plurinationality”)
ይሁንና ሌሎቹ አገሮች በመገንጠል ላይ ያላቸው አቋም በብዛት ግልጽ አይደለም። በካናዳ የኩዩቤክ መገንጠል ጥያቄ ላይ ለመወሰን የተካሔደው ሕዝበ ውሳኔ በአንድ በመቶ ተቃውሞ ተበልጦ ውድቅ ከተደረገ በኋላ የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግልጽ ያደረጋቸው ነጥቦች ነበሩ። አንደኛው ኪዩቤክ ብቻዋን የመገንጠል መብቷን መወሰን ትችላለችም፣ አትችልምም አይልም፤ ኹለተኛው ኩዩቤክ ብዙኀን ነዋሪዎቿ ለመገንጠል እስከወሰኑ ድረስ ካናዳ እምቢ ማለት የምትችልበት የሕግ ማዕቀፍ የለም፤ ኹለተኛው ውሳኔ በሚተላለፍበት አጋጣሚ ካናዳ እና ኪዩቤክ በአተገባበሩ ላይ መደራደር ይኖርባቸዋል።

በኢትዮጵያ በርካታ የዞን እና ክልል እንሁን ጥያቄዎች አሉ። ለዚህ የተለጠጠ ፈቃድ ሕገ መንግሥቱ ቢሰጥም አፈፃፀሙ ላይ በርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አሉ። ለምሳሌ ያክል ሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ እንኳን ብንመለከት በጣም አወዛጋቢ ነገሮች ካሁኑ እየተከሰቱ ነው። የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔን ሳይውል ሳያድር እንዲፈፀም እያለ የሚወተውተው “ኤጄቶ” የተባለ ኅቡዕ ቡድን በፌስቡክ ገጹ፣ “ከሕዝበ ውሳኔው በፊት ምንም ድርድር የለም” የሚል መግለጫ አውጥቷል። በተለይም የአስተዳደር ወሰኑ እምብዛም ግልጽ ባልሆነበት እና የደቡብ ዋና ከተማ ሆና ስትገነባ የከረመችው ሐዋሳ ከተማ ዕጣ ፈንታ ላይ ምንም ዓይነት ቅድመ ድርድር ሳያደርጉ የራስን ዕድል በራስ መወሰን አንድ ጥያቄን ለመመለስ ሌላ ጥያቄን መፍጠር ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here