ከማመን መጠየቅ፣ ከማድረግ ማሰብ እንዲቀድም

0
724

የኡጋንዳ ተሞክሯቸውን መነሻ በማድረግ ቤተልሔም ነጋሽ÷ ስለ ሒሳዊ ትችት ወይም ራሳቸው በተጠቀሙበት ሐረግ አጠንክሮ ማሰብና መጠየቅን በተመለከተ ከማመን በፊት መጠየቅ እንደሚቀድም ከድርጊት ደግሞ ውጤትና ዓላማን የመመርመርን ጠቀሚነት አስምረውበታል’ እንዴት የአጠንክሮ ማሰብና መጠየቅን ክህሎት ማደበር እንደሚቻልም መንገዶችን ጠቁመዋል ።

 

“በዓለማችን ላይ ያለ ሁሉም ሰው ሊኖረው የሚገባው አንድ ክህሎት ቢኖር ያለወገንተኝነት፣ ያላድልዎ አጠንክሮ የማሰብ ችሎታ ነው”

ጆሽ ላንየን
“የአገራችንን ገዥዎችና የትምህርት ሥራ ኀላፊዎች የምጠይቀው ተማሪዎች የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን ችግርን የመፍታትና አጠንክሮ የማሰብን ክህሎቶች እንዳላቸው የሚመዝኑ ፈተናዎችና መመዘኛዎች እንዲያወጡ ነው”

ባራክ ኦባማ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት
ለስብሰባ በመጣሁበት ካምፓላ ኡጋንዳ ያገኘኀኋቸውና ኡጋንዳ መኖር ከጀመሩ 20 ዓመት ማስቆጠራቸውን የነገሩኝ አሁንም በምህንድስና ሥራ ላይ ያሉ አዛውንት አባት ስለኢትዮጵያ ብዙም መረጃ የሌላቸው ሆኖ ብዙ ጥያቄ አከታትለው ሲጠይቁኝ የማውቀውን ስመልስ፣ የማላውቀውን መረጃ ወዳለበት ሳመላክት ቆየሁና ወሬው ስለኢትዮጵያውያን ማንነትና ስብዕና ሆነ’ በተለይም ስለኡጋንዳውያን መልካምነት ጠቅሰውልኝ በርዕሱ ላይ የመሰለንን ሐሳብ ከሰነዘርን በኋላ የተስማማንበት መደምደሚያ አገር ቤት ያለው ኢትዮጵያዊ ወጣ ብሎ ሌላው ቀርቶ በባሕልም በዕድገት ደረጃም የሚቀራረቡንን አገራት የማየት ዕድል ቢኖረውና ተመልሶ አገሩ መሥራት ቢችል ምናልባት የተሻለ ሕዝብ ሊኖረን ይችላል የሚል ነው።

በነገራችን ላይ ሕዝብ እንደሕዝብ ተጠቅሎ እንዲህ ነው ባይባልም በተለይ የተማረው፣ በከተሞች የሚኖረው በዕውቀትም በትምህርትም የተሸለ ቦታ ላይ ያለውና አገሩን የመለወጥ ዕድል ያለው ከተሜው ግን በአብዛኛው በሚያሳየው ባሕሪይ እንዲህ ነው ወይም አይደለም ብሎ ለመናገር ይቻል ይመስለኛል። ከምንኖርበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ማኅበረሰባችን ዋጋ ከሚሰጣቸው ጉዳዩችና ዕሴቶች አንፃር በተጨማሪም በዓለም በተለያዩ መስፈርቶች መሠረት ካለን ደረጃ አንፃር የሆነውንና ያልሆነውን፣ የጎደለንንና ያለንን ማወቅ ከባድ አይሆንም።

ለዛሬ ምናልባት በግሌ አስተያየት ይጎድለናል ብዬ የማስበውና በሌሎች ሰዎችም ሲጠቀስ የምሰማው ጠቃሚ ነገር አጠንክሮ ማሰብና መጠየቅን critical thinking የሚመለከት ነው። ምናልባት እንደአገር ካለንበት ሁለንተናዊ ለውጥ፣ ፊታችን ከተጋረጠው ብዙ ችግር፣ አለመስማማትና የጋራ ሐሳብ ማጣት እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ላለው መቃቃርና በዚህም ምክንያት ለሚፈጠረው መፈናቀልና ሰላም እጦት የመፍትሔ መጀመሪያ አጠንክሮ በትኩረት ማሰላሰል ነው። በፖለቲካ ሥልጣን ላይ በተዋረድ ላሉት፣ በየቦታው ወጣቱን በማኅበራዊ ሚዲያና በሌላውም መንገድ እየቀሰቀሱ ለጥፋት ለሚነዱት ለራሱ ለወጣቱም የሚባለውን ከማመን በፊት መጠየቅ፣ ከድርጊት በፊት የድርጊቱን ውጤትና ዓላማ መመርመር እጅግ ጠቃሚ ነው።
አጠንክሮ ማሰብና መጠየቅ (critical thinking) ምናልባት ተጋኗል ሊባል በሚችል መልኩ በአንድ ወቅት የሁሉም በተለይ የምዕራባዉያኑ ዘይቤ ፣ ለሁሉ መፍትሔ ነው እየተባለ የሚነገርለት ጠቃሚ ክህሎት ነው። በርካታ መጻሕፍት በርዕሱ ላይ ተጽፈዋል፤ ሥልጠናዎች ተሰጥዋል። ምናልባት በአገራችን ይህ በስፋት ተካሒዶ ቢሆን የተሻለ ቁጥር ያለው ጠያቂ፣ ምክንያታዊ፣ አሰላሳይ ትውልድ መፍጠር በቻልን ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ግን በርካታ ሕዝባችን ወጣት በሆነበት የወጣቱን ዝንባሌና የማሰላሰል አቅም ለማየት ማኅበራዊ ሚዲያን ማየት ይበቃል፣ ይሄ በቂ ነው ባይባል በየቦታው ያለው መልካም አስተዳደር እጦት፣ ለአገር ኅልውና አለማሰብ ከአገር ይልቅ የራስን ስሜትና ፍላጎት ማራመድ የመሳሰሉትን ጠንቆች ማየት ይቻላል።

በአንክሮ ማሰብ ከተለመደው ወጣ ባለ ሁኔታ በጥልቀትና በብልጠት ማሰብ ነው። በአንክሮ ማሰብና መጠየቅ አዳዲስ ዘመን አመጣሽ ተግዳሮቶችን ለመሻገር ይረዳል።

አጠንክሮ የማሰብ፣ የመጠየቅ፣ የመመርመር ክህሎት የለንም ስንል ለችግሩ እንደምንጭ የሚታየው ጉዳይ ለመፍትሔውም የሚረዳ ነውና ያንን መጥቀስ ተገቢ ነው። በበኩሌ አንዱና ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ሥርዓታችን ይመስለኛል። ከጥንትም ጀምሮ አንዴ የሶሻሊስት ሌላ ጊዜ የፈርንሳይና የአሜሪካ እየተባለ የተለያየ ፖሊሲ መሞከሪያ ሆነን እንደነበር የሚታወስ ነው። ትምህርት ዜጎች የሚሠሩበት ቁልፍ መሣሪያ ሳይሆን የፖለቲካ መጠቀሚያ እንደነበር በመንግሥትም ጭምር የታመነ ጉዳይ ነው።

ፖሊሲያችንና አስፈፃሚ መምህራኖቻችን ምሥጋና ይግባቸውና እኛ ከተማርንበት ዘመን ጀምሮ እስካሁን ሸምድዶ መመለስና መድፈንን እንጂ ለምን ብሎ የሚጠይቅን ትውልድ አያበረታቱም።

ተማሪዎች በ10 ወይም 12 ዓመታት ከኮሌጅ በፊት ትምህርት ዓለምና ከዚያም እንደየትምህርቱ እስከ አምስት ዓመት በሚቆዩቤ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ ሁሉንም የሕይወት ልምድ ያገኛሉ ማለት ዘበት ነው። ማሰብ፣ ማሰላሰል፣ መጠየቅን ግን ቢያንስ እንደ ፍልስፍና ባሉ ትምህርቶች እንኳን አጠንክረው ግንዛቤ እንዲያገኙባቸው ማድረግ ይገባል። ሌላው ትምህርት ከዚህ ክህሎት ውጪ ባዶ ነውና።

የቀድሞ የብሪታንያ የትምህርት ሚኒስትር ቻርለስ ክላርክ ይህንኑ በሚመለከት እንዲህ ብለው ነበር።
“ትምህርት ለእያንዳንዱ ሰው ሊሰጠው የሚችለው ነገር አጠንክሮ ማሰብ ዋነኛው ነው። መረጀና ዕውቀት እንደ ልብ በሚፈስበት ዘመን መረጃ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ያገኙትን መረጃ ማጠናከር፣ ማሰላሰልና መመዘን ዋናው ልዩነት የሚያመጣ ድርጊት – ይህም አጠንክሮ ማሰብ ነውና አጠንክሮ የማሰብን ጥቅም ወይም ዓላማ ከገለፁ ጸሐፍት መካከል ደግሞ ጆን ስትራተን “አጠንክሮ የማሰብ ጥቅም ደጋግሞ ማሰብ ነው። ይኸውም እንደገና መከለስ፣ መመዘን እና ሐሳብን መከለስ ነው” ይላል።

ወጣቶች በኮሌጅ ቆይታቸው በሚያጠኑት የትምህርት ዓይነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ዕውቀት ይዘው መውጣታቸው በቂ አለመሆኑ ታምኖበት ሁለንተና ስብዕናቸውን የሚገነቡ ከትምህርት ዉጪ ያሉ የተለያዩ ተግባራት በየኮሌጁ ይከናወናሉ። እነኝህ ተግባራት ወጣት የኮሌጅ ተማሪዎች ስለማንነታቸው ግንዛቤ እንዲኖራቸው፣ ከትምህርት ውጪ ያላቸውን ስብዕና፣ የሚፈልጉትን ዝንባሌና ሌላውንም መረዳት እንዲችሉ ያግዛሉ።

በግሌ በኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እንዳደገና በትምህርት ሥርዓቱም እንዳለፈ ሰው ከቀለም ውጪ ማንነቴ፣ ፍላጎቴ፣ ድምፄ፣ የእኔ እውነት የምለውን እንዳገኝ ትምህርት ቤት አላገዘኝም ብዬ አምናለሁ። እነኝህን ሁሉ ለመመለስ (ተመልሶ የሚያልቅ ሳይሆን የሕይወት ሙሉ ጉዞ መሆኑ እንዳለ ሆኖ) የረዳኝ በኋላ ያለፍኩባቸው ሥልጠናዎችና የተለያዩ ዕድሎች ናቸው ብዬ አምናለሁ። እነኛ ዕድሎች ለብዙኃኑ የማይደርሱ በመሆናቸው ግን አሁንም ተማሪዎች ላይ ቢያንስ ተመራቂዎች ላይ መሥራት በሥራ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ የተሻሉ አሳቢዎችና አሰላሳዮች፣ ችግር ፈቺዎች መፍትሔ አመንጪዎች አዳዲስ ሐሳብ አቅራቢዎችና ፈፃሚዎች እንዲሆኑ ያግዛል።

በተረፈ ለዛሬ ንድፈ ሐሳብ ላይ ማተኮር ካልቀረልኝ ራስን ስለመሆንና የራስን ድምጽ ስለማዳመጥ፣ ታማኝነት ከራስ ይጀምራልና ለራስ ታማኝ ስለመሆን ከላይ የጠቀስኳቸውን ሐሳቦች ስለሚያጠናክሩልኝ የሚቀጥሉትን አባባሎች ጠቅሼ ጽሁፌን ላብቃ።

ማንነታችሁን እወቁና ለማንነታችሁ ታማኝ ሁሉ። የራሳቸሁ ሐሳብ ይኑራችሁ፣ ውጪ ያለው ጩኸት በርክቶ የእናንተን ሐሳብ ሊውጥ ሲሞክር አንገታችሁን ደፍታችሁ አሳልፉት።

የምትሠሩት ምንም ይሁን ምን ወደፊት መግፋታችሁን ቀጥሉ።

ክርስቲና ቶሲ
ለራሳችሁ ታማኝ ሁኑ ነገር ግን ለመማር ፈቃደኛ ሁኑ። ጠንክራችሁ ሥሩ፣ ከራሳችሁ በቅ ማንም ይፈፀማሉ ብሎ የማያስብ ቢሆን እንኳን ህልማችሁ አትተው። የሰለቸ አባባል ሊመስላችሁ ይችላል ሆኖም በሕይወታችሁ ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ ብትፈልጉ በመንገዳችሁ ላይ እንድትቆዩ ይረዳችኋል።

ፊሊፕ ስዊት
ራስን መሆን ወሳኝ ነገር ነው። በእያንዳንዱ ቀን ከመኝታችሁ ተነስታችሁ መስታወት ስታዩ በመስታወት ውስጥ መልሶ የሚያያችሁ ሰው የምትኮሩበት ዓይነት ሰው መሆን አለበት።ያንን ማድረግ የምትሉት ደግሞ ለራሳችሁ እውነተኛና ታማኝ መሆን ስትችሉና ከፍ ያለ ስብዕና ያላችሁ ሰዎች ስትሆኑ ነው።
በእያንዳንዱ ቀን ታሪካችሁን የመፃፍ ዕድል በእጃችሁ ነው።
አሮን ሮጀርስ

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here