እናትነት – የተፈጥሮ ሥልጣን

0
736

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ባሳለፍነው ሳምንት የእናቶች ቀን በተለያዩ መገናኛ ብዙኀንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ታውሶ አልፏል። የእናቶች ቀን እንዴት መታሰብ ያለበት ለሚለው የተገኘ ስርዓት ያለ አይመስልም፤ በተለይ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ግን ታሪኮችንና ፎቶዎችን በማጋራት ተከብሯል ማለት ይቻላል። እናትን በቃል ብቻ አይደለ በተግባር ማክበር እንደሚገባ ልብ ይሏል!

እናትነት ተፈጥሮ ለሴት ልጅ የሰጠቻት ሥልጣን ነው። ሰዎች ሥልጣን ብለው የሚያስቡት በሰው ሠራሽ ስርዓት የማኅበረሰባዊ ወይም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የሚገኙ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎችን ይሆናል። እናትነት ግን ከእነዚህ ሁሉ የላቀ፤ ከሰው የማይቀበሉትና ማንም ሊነጥቅ የማይችለው የተፈጥሮ ሥልጣን ነው። ይህን ስንል በመውለድ ስለሚገኝ እናትነት ብቻ አይደለም፤ ላልወለዱት ልጅ እናት የሆኑ ሰዎች አሉና እናት ሊሆኑ ስለወደዱ ሰዎች ሁሉ ስናነሳ ነው።

በእናትነት የሚገኝ ሥልጣን መንግሥት ከሚለው በሥልጣን ላይ ጾታን የማመጣጠን ጉዳይ ይለያል። ከአካታችና በየደረጃው ሴቶችን ከማሳተፍ አሠራርም አይገናኝም። የተለየ ሥልጠና እና ልዩ ድጋፍ አይጠይቅም፤ ክትትልና ቁጥጥርም አያሻውም። እንደውም ከእናትነት የሚልቅ ሥልጣን በምድር ላይ ያለ አይመስለኝም። እንዴት? ሰው የመሥራት ኃይል ስለሆነ።
ሴቶች በተለይም የእናትነትን ክብር ያገኙት ይህን ጉዳይ ሳያውቁት ቀርተው አይደለም፤ እየተጠቀሙበት መሆኑ ግን ያጠራጥራል። አንዲት እናት ወይም የልጅ አሳዳጊ ከልጇ ሆድ መሙላት፣ በአካል ጤናማ መሆንና ትምህርት ቤት ውሎ በሰላም መመለስ ባሻገር የመንፈሱና የማንነቱ ጤንነትም ያሳስባታል ወይም ሊያሳስባት ይገባል።

“ችግርን ከምንጩ ማድረቅ” እንደሚሉት ብሒል ነው፤ ሰው ከምንጩ ለማግኘት ልጅነት፣ ዕድገትና አስተዳደግ ወሳኙ ነጥብ ነው። ገበያ ላይ ለተሰራጨ አንድ ምርት ተጠያቂው አምራቹ ፋብሪካ ከሆነ፤ ከቤተሰብ ይልቁንም ከእናት ይልቅ ለዚህ ትውልድ ተጠያቂ አይኖርም ማለት ነው።

ሁላችን የአስተዳደጋችን ውጤት ነን። ያም ከሆነ ከመንግሥት ሹማምንት ይልቅ ሥልጣን ያለው ቤተሰብ ነበር ማለት ነው። በበኩሌ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ከካቢኔው ሃምሳ በመቶውን ሴቶች መሆናቸውና ምን ያህል ድርሻቸውን ተወጡ ከሚለው በላይ፤ በየቤቱ ያሉ እናቶች ምን እያሰቡና ምን እያደረጉ ይሆን የሚለው ያሳስበኛል። አገር ይቀድም የለ?

እናትነት ብዙዎች እንደሚሻሙት የውሳኔ ሰጪዎች ወንበር አይደለም፤ ግን አገርን መሥሪያ ነው። አንዲት ሴት በመሰረተችው ትዳርና ቤተሰብ ውስጥ ሥልጣን አላት፤ ልትመራው ትችላለችና። አንዲት ሴት በወለደችው ልጅ ላይ ሥልጣን አላት፤ ታሳድገዋለችና። እናም ከእናትነት የላቀ ሥልጣን፤ ያውም በተፈጥሮ የተገኘ፤ ወዴት አለ?

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here