አስተዳደሩ ተጨማሪ 1 ሺሕ ለሚጠጉ ግብር ከፋዮች የወንጀል ምህረት ሊጠይቅ ነው

0
590

የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር የገቢዎች ቢሮ ሚያዚያ 1 ሺሕ 70 ግብር ከፋዮች የወንጀል ምህረት ከተደረገላቸው በኋላ እየመጡ ላሉ ሌሎች ግበር ከፋዮቹ ምህረት እንዲደረግለት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን መጠየቁ ታወቀ። ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ ፖሊስ መምሪያዎች እና የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አጠቃሎ ያላካቸው መረጀዎች እንደአዲስ እየላኩ በመሆነቸው ለኹለተኛ ጊዜ ምህረት እንዲጠየቅ ምክንያት መሆኑም ታወቋል።

ከዚህ ቀደም 10ሩ የፖሊስ መምሪያዎች እና አራቱ የገቢዎች መስሪያ ቤቱ ቅርንጫፎች ያላቸውን የክስ መዝገቦች በማደራጅት እንዲልኩ የተጠየቁ ሲሆን የከተማው የገቢዎች ቢሮ የመጡትን መረጃ በማመሳከር ወቅት የመረጃ ክፍተት መኖሩን ለይቶ እንደነበር የቢሮው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የሕግ ማስከበር ዘርፍ ኀላፊ ታምራት ንጉሴ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በተጨማሪም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የለካቸው መረጃዎች ከሌሎቹ ጋር ሲተተያይ ልዩነቶች ቀድመው መለየታቸውን የገለፁት ታምራት ከውሳኔው አንገብጋቢነት አንጻር ግን ባለው እንዲወሰን ተስማምተው ለመላክ መገዳደቸውን አክለዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኩል መረጃው ተሰብስቦ እንዲመጣለት የጠየቀ ሲሆን የመጨረሸው ውሳኔ እስከተሰጠበት ጊዜ ያሉ ወንጀሎችን ለማካተት መታሰቡንም ለማወቅ ተችሏል። ለተፈጠረው ክፍተት እንደምክንያት ከተሰጡት መካከልም የቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች የወንጀል ክስ መረጃ ያለመያዛቸው ሲሆን ለዚህም እንደምክንያት የተሰጠው ፖሊስ በሥራው (‘ኦፕሬሽኖች’) ላይ አብሮ በመሳተፉ ክሶችን በቀጥታ ከፍቶ የመከታተል እና ወደ ዐቃቤ ሕግ የመላክ ልምዶች በመኖራቸው መሆኑ ታውቋል።

ክሳቸው እንዲቋረጥላቸው እየጠየቁ ካሉት ውስጥም በቅርቡ የገቢዎች ሚኒስቴር በተለያዩ ኦፕሬሽኖች ላይ ያለደረሰኝ ሲገበያዩ ይዤአቸዋለሁ ካላቸው መካከልም እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል።

ምህረቱን ከጠየቁት መካከልም ያለደረሰኝ ግብይት፣ ከዋጋ በታች በመሸጥ እጅ ከፍንች የተያዙ እንዲሁም በኮንትሮባንድ ንግድ እንደሆነ ታምራት ገልፀዋል። የጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ መሥሪያ ቤትም ያለፈው ውሰኔ ሲሰጥ ከቀረቡለት 1 ሺሕ 780 ምዝገቦች መካከል 530ውን አለመቀበሉን ገልፆ ነበር። በጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ውስጥ ውሳኔው ቅርበት ያለቸው ሰዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ያለፈው ውሳኔ ሲወሰን የመጨረሻ እንደሚሆን ታሳቢ የተደረገ ቢሆንም አሁንም ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ጥያቄውን ያነሱት ነጋዴዎችም ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ጋር ተመሳሳይ ክስ ያላቸው በመሆናቸው ጥያቄያቸውን ላለመቀበል በቂ ምክንያት እንደሌለ ገልፀው ቀድሞውንም ውሳኔው ሲወሰን ይህ ታሳቢ ሊደረግ ይገባ ነበር ብለዋል።

በመጋቢት ወር መጨረሻ የተሰጠውን የምህረት ውሳኔ የገቢዎች ሚኒስቴሯ አዳነች አቤቤ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በጻፉት ደብዳቤ መቃወማቸው የተታወሳል። በአዲስ አበባ ከንቲባ ታከለ ኡማ ለቀረበለት ጥያቄ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የገቢዎች ሚኒስቴርን አስተያየት በጠየቁት መሰረት በሰጡት የጽሁፍ መልስ በግብር ስርዓቱ ውስጥ ከፍተኛው ክፍተት የሕግ ማስከበር እንደሆነ ገልፀው በፌደራል ከተመዘገቡ ግብር ከፋዮች አብዛኛው ባዶ እና ኪሳራ የሚያሳውቅ መሆኑን ለዋቢነት ገልፀው ነበር።
በተጨማሪም የተጨማሪ እሴት ታክስ ጉዳይ የፌደራል ጉዳይ እንደሆነ እና በጉዳዩ ላይም የገንዘብ ሚኒስቴርን በማሳተፍ በመላው አገሪቱ ያሉ ግብር ከፋዮችን ያማከለ ውሳኔ መወሰን አለበት ማለታቸውም ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here