በዘመቻ ዘላቂነት ያለው ሥራ መሥራት አይቻልም!

0
541

ቅዳሜ፣ ግንቦት 3/2011 የአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል ማፅዳት ዘመቻ በሚመስል መልኩ በተለያዩ ቡና ቤቶች ድንገተኛ ፍተሻ በማድረግ የጅምላ እስር መፈፀሙ ይታወሳል። በዘመቻው 600 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ተመክረው ሲለቀቁ፣ 8ቱ በምርመራ ላይ መሆናቸው ተጠቅሷል’ ‘አንድ ነጻ ሰው ከሚታሰር፣ ዐሥር ወንጀለኛ ቢያመልጥ ይሻላል’ የሚለው የፍትሕ መርሕ ተጥሶ፣ ወንጀለኞችን ለማግኘት ብዙ ንፁኀንን በዘመቻ የማሰር አሠራር ከፍትሕ መርሕ ያፈነገጠ ከመሆኑም በላይ፣ ወንጀልን በዚህ መልኩ ለዘለቄታው መከላከል አይቻልም።

በዕለቱ 12 ሺሻ ቤቶች ከኹለት ሺሕ 500 የሺሻ ማጨሻዎች፣ ራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ ግማሽ ኪሎ አደንዛዥ ዕፅ እንዲሁም 1 ሽጉጥ በዘመቻው መወረሳቸውንና በማስረጃነት ፖሊስ መያዙን አስታውቋል። ይሁን እንጂ አዲስ ማለዳ በዘመቻ ዘላቂ ወንጀልን መከላከል አይቻልም ብላ በፅኑ ታምናለች። የዘመቻ ሥራ በአብዛኛውን ጊዜ ውጤታማ እንደማያደርግ ከበቂ በላይ ተግበራዊ ማሳያዎች እንዳሉ ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ ለማሳየት ትሞክራለች።

በዘመቻ መልኩ ከተሠሩ አኩሪ ከሆኑ አገራዊ ጉዳዮች አንዱ በደርግ ዘመነ መንግሥት በ1970ዎቹ የተካሔደው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ሲሆን መሐይምነትን ከመዋጋት አንፃር አርአያ የሚሆን አብነት ሆኗል። ብዙ ዜጎችን በተለይ ጎልማሶችን ከመሐይምነት ነጻ ያወጣው ዘመቻ ኢትዮጵያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በበጎ ከማስነሳቱም በተጨማሪ ለተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ድርጅት እስከ መሸለም አድርሷታል።

ምን ያደርጋል! የዘመቻ ነገር ነውና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ያ ሁሉ በዘመቻ የተሠራ ውሃ እንደ ተቸለሰበት የአንድ ጊዜ ጉዳይ ሆኖ ቀርቷል። የነበረው እንዳልነበረ፣ ፊደል ለይተው ቃላት ሰካክተው ማንበብ የጀመሩት የመሠረተ ትምህርት ሠልጣኞች ቀጣይነት የሌለው ነገር በመሆኑና የልምምድ ዕድሎችም አነስተኛ በመሆናቸው ወደ ቀደመ የመሐይምነት ዘመን አዝግመው ተመልሰዋል።

ይህ ከሆነ ከአራት ዐሥርት ዓመታት በኋላ ደግሞ ስንመለስ የአዲስ አበባን የፅዳት ዘመቻ እናገኛለን። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በተደጋጋሚ አዲስ አበባን የማፅዳት ዘመቻ መጥረጊያ ይዘው አደባባይ በመውጣት ሲመሩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርም ነገ እሁድ፣ ግንቦት 11 ለኹለተኛ ጊዜ የሚካሔድ የአዲስ አበባን እናፅዳ ዘመቻ መጥራታቸው ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ያለ በቂ ዝግጅት፣ ዕቅድ ያልተደረገበትና በተለይም ዘላቂነቱ አስተማማኝ ያልሆነ ዘመቻ ሀብትና የጊዜ ብክነት ከማምጣት በስተቀር የሚያመጣው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም። የአዲስ አበባ የፅዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ ፅዳት ጥበቃ ላይ ያመጣው ለውጥ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል።

ከተማን ማፅዳት ትልቅ ሥራ ሲሆን ከኅብረተሰቡ መሠረታዊ ፍላጎት መሟላት አለመሟት ጋር አብሮ መታየት የሚስፈልገው እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በቂ የመፀዳጃ ቤት ባልተገነባበት ሁኔታ ዘመቻው ከዳር ይደርሳል የሚል እምነት አዲስ ማለዳ የላትም።

ይህንን አቋም በማስረጃ ማስደገፍ ካስፈለገ፣ ‘Water Aid Report 2018’ን መመልከት በቂ ነው። በሪፖርቱ ከሰሃራ በታች ባሉ 344 ሚሊዮን የሚገመቱ ሕፃናት በቂ (ተገቢ) መፀዳጃ ቤት እንደሌላቸው ተጠቅሷል። በትምህርት ቤቶች የመፀዳጃ ቤት አቅርቦት እጥረት የመጀመሪያው የሆነችው ኢትዮጵያ ነዋሪዎቿ በቤታቸው መፀዳጃ ቤት እንኳን ማግኘት የተነፈጉባት አገር መሆኗን አጋልጧል። ሪፖርቱ 93 በመቶ ኢትዮጵያውያን በቤት ውስጥ የንፅሕና መጠበቂያ እንደሌላቸው ጠቅሷል። የመዲናችን ነዋሪም ቢሆን ከአጠቃላይ ሕዝቡ እምብዛም የተለየ አይደለም።

በዚህ መሠረት በዘመቻ መልክ የሚካሔዱ ነገሮች ፋይዳቸው ጊዚያዊ ብቻ ነው የሚሆነው። መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ጥናት፣ የረጅም ጊዜ ዕቅድ፣ ተግባራዊ አፈፃፀም፣ ቀጣይነት ያለው ሥራ እስካልተሠራ ድረስ የእምቧይ ካብ እንደሚሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በመሆኑም አዲስ ማለዳ በጥናት የተደገፈ፣ በመረጃ የዳበረ፣ በቋሚነት የሚሠራ ሥራ መሠራት እንዳለበት ታሳስባለች።

ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ከወንጀለኛ ማፅዳት እስከ እርዳታ ማሰባሰብ፣ ከአካባቢ ማፅዳት እስከ እርከን ግንባታዎች… በተለያዩ ዘርፎች የሚያደርጋቸው ዘመቻዎች ሕዝባዊ ግንዛቤን ለመጨመር እና የማንቂያ ደወል ለማድረግ አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ዘላቂ መፍትሔ ሆነው ሊወሰዱ አይችሉም።

ፅዳትም ይሁን ወንጀልን መከላከል፣ ትምህርት ማስፋፋትም ይሁን ጤና ጥበቃ፣ ብዙዎቹ በዘመቻ መሠረታዊ ለውጥ የሚመጣባቸው ጉዳዮች ሳይሆኑ ሥር ነቀል የፖሊሲ ማሻሻያ እና አተገባበር የሚሻቸው ጉዳዮች ናቸው። መንግሥት ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዘላቂ መፍትሔዎችን ነድፎ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here