በጌዲኦ ዞን የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ለጎርፍ ተጋላጭ ናቸው ተባለ

0
611
  • ለወባ መፈጠርና መስፋፋት አመቺ የአየር ሁኔታ በመኖሩ ሥጋት ተፈጥሯል

በጌዲኦ ዞን ወናጎ ከተባለችው ወረዳ በስተቀር ሁሉም ወረዳዎች ከመጪው የበልግ ዝናብ ጋር ተያይዞ ለጎርፍ ተጋላጭ መሆናቸው ታውቋል። በመሆኑም ክልሉ ይህንን አውቆ ዝግጅት እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

በዘንድሮው በልግ በአብዛኛው የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ ዝቅተኛና ሞቃታማ ቦታዎች ላይ ለወባ መፈጠርና መስፋፋት አመቺ የአየር ሁኔታ ይኖራቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር በየነ ሞገስ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ስለሆነም አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለክልሎቹ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በደቡብ፣ በደቡብ ምሥራቅና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የጎርፍ አደጋ መከሰቱ ይታወሳል። በዚህም በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር መንገዶች በመዘጋታቸው በአካባቢዎቹ የሚገኙ ነዋሪዎች ለችግር ተጋልጠው ነበር።

አሁን የሚጥለው ዝናብ ለእርሻና ለተለያዩ ተግባራት የሚጠቅምና የተጠበቀ ቢሆንም፣ መጠኑ ከፍተኛ ሊሆን ስለሚችል የተለያዩ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል የሚናገሩት የጉጂ ዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አበበ አባቡልጋ፣ ይህንን ዝናብ ተከትሎ በተለያዩ የኢትዮጵያ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች መንገዶች የመቆረጥ፣ ጸረ ሰብል ተባዮች መከሰት፣ በንብረት ላይ ጥፋት መድረስና የመሳሰሉ ጉዳቶችን ሊያስከትል እንደሚችል ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አይድሮስ ሐሰን እንደሚሉት መንግሥት ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ቦታዎች ላይ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን፤ ነገር ግን ከጎርፍ አደጋ ጋር በተያያዘ ከሶማሌ ክልል ውጪ ከሌሎች ቦታዎች ምንም ሪፖርት እንዳልቀረበ ይናገራሉ።

የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቋቋም በአንዳንድ አካባቢዎች ቀደም ተብሎ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን የማቅረብ ሥራ እንደተከናወነ የሚናገሩት አይድሮስ “በዚህ መሰረትም በቅርበት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፤ ከዚያ በላይ ከሆነ ደግሞ በሚቀርብ ጥያቄ መሰረት ከፌደራል መንግሥቱ አስቸኳይ ምላሽ ይሰጣል።”

ጨምረውም ከጌዲኦ ዞን ከጎርፍ አደጋ ጋር ተያይዞ የቀረበ ጥያቄ መኖሩን፣ ኮሚሽኑም ጥያቄውን ተቀብሎ አስፈላጊውን ቀድሞ የመከላከል እርምጃዎችን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አዲስ ማለዳ በፌደራል የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ በጌዲኦ ዞን አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ የሚሆን ዝናብ ሊጥል እንደሚችል ትንበያዎች መኖራቸውንና አሁንም የዕለት ተዕለት ትንበያዎችን ጥናት እያደረገ ለሚመለከታቸው አካላት ቀድሞ እንደሚያስታውቅ ከኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here