የእርዳታ ሠራተኞቹ ሽብርተኝትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ተጠረጠሩ

0
680

ፖሊስ የሶማሌ ክልል የሥራ ኀላፊዎችን ፍርድ ቤት ለማቅረብ ባለመቻሉ ምረመራው መጓተቱ ተገጿል

የካቲት 27/2011 በሶማሌ ክልል በቁጥጥር ሥር የዋሉት አራት የሴቭ ዘ ቺልድረን የእርዳታ ሠራተኞች ሽብርተኝትን በገንዘብ መርዳት እና በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን እና የምርመራ ሥራውንም የፌደራል ፖሊስ እያከናወነ መሆኑን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጹ፡፡

የክልሉ ፖሊስ በተጠየቀው መሰረት ለፌደራል መርማሪዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም በምርመራው ሪፖርት ላይ አስተያየት ሰጥቶ ለተጨማሪ ምርመራ መዝገቡ ወደ ፖሊስ መመለሱን የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሀሰን ሁሴን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል፡፡

“የፌደራሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለክልሎች በፌደራል ጉዳይ ላይ ውክልና በሰጠው መሰረት የምርመራ መዝገቡን በቅርበት እየተከታተልን ነው” ያሉት የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በምርመራ ሒደቱ ላይ እንከን በማጋጠሙ ሥራዎችን በወቅቱ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡

በተለይም የሶማሌ ክልል አመራሮችን እንዲያቀርብ በፍርድ ቤት የታዘዘው የሶማሌ ክልል ፖሊስ ላገኛቸው አልቻልኩም በሚል ለዞኑ ፍርድ ቤት በመመለሱ የምርመራ ሥራው መጠናቀቅ አልቻለም ብለዋል፡፡

የፌደራል መርማሪዎች ድርጊቱን መርምረው ሲያጠናቅቁ መዝገቡን እንደሚያስታላልፉለቸው ተናደገሩት ሀሰን በዛን ወቅት መደናገር እንዳይመጣ በሚል መዝገቡን ከጅምሩ እየተከታተሉ እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

“ታዋቂ የሆኑ ባለሥልጣኖችን ፖሊስ ማግኘት አልቻልኩም በማለቱ በአመራሮቹ አድራሻ መጥሪያው እንዲደርሳቸው መመሪያ ተሰጥቷል” ሲሉ ገልፀዋል፡፡ “ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀ ሲሆን አምስቱ የባንክ ሠራተኞች ግን ከተጠረጠሩበት ወንጀል አንጻር በዋስ ሆነው እንዲከራከሩ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ባንክ ሠራተኞች ገንዘቡን ከካዝና አውጥተው ክፍያው ወደ ሚፈፀምበት አካባቢ በሴቭ ዘ ቺለድረን መኪና ይዘው በመሔድ በመክፈል ላይ እያሉ ነበር በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ሥር የዋሉት፡፡

ከእርዳታ ሠራተኞቹ በተጨማሪም ኦሰማን ማሬ የተባለ አክቲቪስት አብሮ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኘውም ምንጮች ገልፀዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት በሶማሌ ክልል አፍደም ወረዳ ዳንሄለይ ቀበሌ ውስጥ ገነዘቡን በማከፋፈል ላይ የሚገኙትን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ካዋለ በኋላ ወደ አፋር ክልል በመውሰድ ለፖሊስ ማስረከቡንም ምንጮቻችን ጨምረው ገልፀዋል። መከላከያም ወደ አፋር ክልል 300 ኪሎ ሜትር ተጉዞ ተጠርጣሪዎቹን ማሰረከቡ ተገልፀዋል፡፡ የእርዳታ ሰራተኞች ይዘውት የነበረው ገንዘብም በኤግዚቢትነት ማያዙንም አረጋግጠዋል፡፡

ሴቭ ዘ ቺልድረን በበኩሉ አራት የእርዳታ ሠራተኞቹ ላለፉት 9 ሳምንታት ምንም ዓይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው እንደሁም ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይቀርብባቸው መቆየታቸው እንዳሳሰበው በሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ ሕይወት እምሻው ገለፀዋል፡፡ ከመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጋርም ስለተፈጠረው ችግር ለመረዳት በቅርበት እየሠራን ነው ያሉት ሕይወት ድርጅቱ ሠራተኞቹ ምንም ዓይነት ወንጀል ፈፅመዋል ብሎ ለማመን ምንም ምክንያት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡

“ሠራተኞቻችን ባግባቡ ሥራቸውን እየከናወኑ እንደነበረ ሙሉ ለሙሉ እንተማመናለን” ያሉት ሕይወት አክለውም “ይህ ጉዳይ በአፋጣኝ እንዲፈታ እና ሠራተኞቻችንም እንዲለቀቁ ጥሪአችንን እናስተላላፋለን፤ ክብር ሊሰጣቸው የሚገባ የሰብኣዊነት ሠራተኞች ናቸውና” ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here