በግጭቶች የወደሙ 167 የጤና ኬላዎችን መልሶ ለመገንባት አልተቻለም

0
693

85 የሚሆኑትን ኬላዎች ለመገንባት ከሠላሳ ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል

በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ጉዳት ደርሶባቸው በከፊል እና ሙሉ በሙሉ የወደሙ የጤና ኬላዎችን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ግለሰቦች የተገነቡትን ማዕከላት በማን አለብኝነት እንደሚያፈርሷቸው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች ጉዳት ከደረሰባቸው 167 የጤና ኬላዎች ውስጥ 85 የሚሆኑትን እንደገና ለመገንባት በጀት ተይዞላቸዋል።

በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በሶማሌ እና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች በርካታ የጤና ኬላዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል የወደሙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 85 የሚሆኑት እንደገና ለመገንባት ከሠላሳ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደተያዘላቸው ኢንቲትዩቱ አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል በከፊልና በሙሉ ከወደሙት የጤና ኬላዎች ውስጥ 32፣ ሶማሌ ክልል 19፣ ደቡብ ክልል በ16 እንዲሁም አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 14 የጤና ኬላዎች እንደገና ለመገንባት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የአማራ ክልል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ብቻ 14 የጤና ኬላዎች የወደሙ ሲሆን በሌላው የክልሉ አካባቢዎች ግን ምንም የወደመ ኬላ አልነበረም።

ምንም እንኳን በቅድሚያ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያወጣው መረጃ 215 የጤና ኬላወች ወድመዋል የሚል ቢሆንም በተደረገ ማጣራት በከፊል እና ሙሉ ለሙሉ ወድመው የተገኙት 167 ሲሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል 12 ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ የሚለው መረጃ ላይም ባደረገው ማጣራት 4 ጤና ጣቢያዎች ብቻ መውደማቸውን ማረጋገጡን ገልጧል። በዚህም ጋር ተያይዞ ከወደሙት በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልል የሚገኙት 4 የጤና ጣቢያዎች መልሶ ለመገንባትም በጀት ተይዞላቸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በከፊልና በሙሉ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትን በፍጥነት ገንብቶ መጨርስ ባለመቻሉ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ለመድረስ መቸገሩንም ጨምሮ ገልጿል። የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመግለጫው እንዳስታወቀው ለተፈናቃይና ተመላሽ ወገኖች ተገቢውን የጤና ምላሽ በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሶማሌ፣ ሐረሪ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 76 ወረዳዎች በአጠቃላይ ከ38 ሺሕ በላይ ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቋል።

እንደ ኢንስቲትዩቱ ገለፃ የሕክምና እርዳታውን ለመስጠት 205 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በኹሉም ክልሎች ተሰማርተው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለፉት ስድስት ሳምንታት ውስጥ ለመድኀኒትና ለመድኀኒት ግብዓቶች የሚውል 60 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪም የሰው ኃይል ለመመደብ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ። በጠቅላላው በስድስት ሳምንት ውስጥ 74 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here