ቦርዱ የምርጫ ማስፈጸሚያን ጨምሮ 4 ቢሊዮን ብር በጀት ጠየቀ

0
630

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ለሚካሒዳቸው አገር ዐቀፍ ምርጫ፣ ለኹለቱ የፌደራል ከተሞች ምርጫ ማስፈጸሚያ፣ ለሕዝበ ውሳኔዎች ማስፈፀሚያ እንዲሁም ለሥራ ማስኬጃ በውጪ አጥኚዎች የተጠና ተጨማሪ 4 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቀረበ’ የሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ከዛም ጋር ተያይዞ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር ማሻቀብ እስከዛሬ ከነበረው ምርጫ በተሻለ ጥራት ምርጫውን ለማካሔድ መታሰቡም ለበጀቱ ማደግ ምክንያት መሆናቸው ታውቋል።

ምክር ቤቱ መሻሻል አለባቸው ያላቸውን ነገሮች ገምግሞ ለቦርዱ የላከ ሲሆን ምክር ቤቱም አንዳንድ የማሻሻያ ሐሳቦች ተካተው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሰረት ማሻሻያውን አድርገው መላካቸውን የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ተናግረዋል።

ቦርዱ በየአምስት ዓመቱ የሚካሔደውን ቀጣዩን አገር ዐቀፍ ምርጫ 2012 ለማስፈፀም ከጊዜ ጋር ትንቅንቅ ፈጥሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀው፣ የቦርዱ ሥልጣን በተቀመጠው ጊዜ መሠረት ምርጫ ማስፈጸም በመሆኑ፣ ለዚህም ሥራ ማስፈጸሚያ የሚሆን ተጨማሪ በጀት ምርጫው በተያዘለት ጊዜ ይካሔዳል በሚል ግምት መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

“ባለን ጊዜ ውስጥ ከቦርዱ የሚጠበቁ ጉዳዮችን አከናውነን ምርጫውን እናስፈጽማለን ብለን እናምናለን” ያሉት አማካሪዋ፣ የጊዜ እጥረት ሊያጋጥም ቢችልም በአሁኑ ወቅት በርካታ ሪፎርሞችን በአንድ ላይ ነው እያስኬድን ያለነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሶልያና ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፤ የጊዜው ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ ጥያቄ የሌለው ሲሆን ተቋሙን ጫና ውስጥ መክተቱ የማየቀር መሆኑንም ተናግረዋል።

“የተለያዩ አካላት የፀጥታ ችግር መኖሩን፣ የጊዜ እጥረት እንዳለና የሕዝብና የቤት ቆጠራ ያለመደረጉን እንደ እንቅፋት ሲያነሱ ይደመጣሉ” ያሉት ሶሊያና፣ “እኛ ግን በተቻለ መጠን ውጪያዊ ችግሮችን ሳይሆን በእኛ በኩል ማድረግ ያለብንን ሁሉ አድርገን ዝግጅታችንን እናጠናክራለን” ብለዋል።

ምጫውን በመደበኛው ጊዜ የማሳካቱ ዕቅድ የማይሆን ከሆነ ለመቼ ማሳካት ይቻላል የሚለው አብሮ የሚታይ ጉዳይ መሆኑን ሶሊያና ገልፀዋል።

“እንደ ተቋም በአሁኑ ወቅት ዋናው ትኩረት ይደረጋል አይደረግም የሚለውን ሳይሆን ምርጫው የተሻለ ሆኖ እንዲካሔድ መሥራቱ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው” ብለዋል።

ቦርዱ በአሁኑ ወቅት የሪፎርም ሥራ እየሰራ እንደሆነ የገለፁት አማካሪዋ የለውጥ ሥራው ሳይጠናቀቅ ባልተቀየረ ሕግና ተቋም የሚደረግ ምርጫ ከበፊቱ የተሻለ ሊሆን አይችልም ሲሉ አማካሪዋ አክለዋል።

“ስለዚህም የቦርዱ ሥራ እንዲሠራ የሚፈለገው በፊት በነበረው ቁመና ላይ ሆኖ ነው ወይስ በተለወጠ መንገድ ነው የሚለውም አብሮ መጤን ይኖርበታል” ሲሉ ባለሙያዋ አሳስበዋል።

የሕዝበ ውሳኔው ጥያቄ ለቦርዱ የመጀመሪያ ሥራው እንደመሆኑ ምንም ዓይነት ልምድ የለውም በማለት ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት የክልል እንሁን ጥያቄ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተነስቶ ወደ ቦርዱ አለመምጣቱን አስረድተዋል። ስለዚህም ከምርጫም በተለየ ተጨማሪ ዝግጅትን እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 28 ግንቦት 10 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here