ኢትዮ ቴሌኮም ሁዋዊ ላይ የሚጣሉ እገዳዎች ያላቸውን ተፅዕኖ ለማወቅ ጥናት ጀመረ

0
536

በሁዋዊ ቴክኖሎጂ ላይ የአሜሪካ መንግሥት የጣለውን እገዳ እና ጉግል ይህንን ውሳኔ ተከትሎ አሳልፎ የነበረውን ክልከላ በማስመልከት ኢትዮ ቴሌኮም በሚጠቀማቸው የድርጅቱ አገልግሎቶች እና ቴክኖሎጂዎች ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጫናዎች ካሉ ለመለየት የሚያስችል ጥናት ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።

ከቴሌኮሙ ማስፋፊያ ፕሮጅከቶች ውስጥ የአዲስ አበባን ኔትወርክ ጨምሮ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸውን የኔትወርክ ሰንሰለት በመላ አገሪቱ የዘረጋው ሁዋዊ ከአሜሪካ መንግሥት ጋር የገባበትን ውጥረት ተከትሎ የአሁኑን ውሳኔ ቀድሞ የጠበቀው እንደነበረ ታውቋል። ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ ከኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ ኀላፊዎች ጋር ስለጉዳዩ መክሮ ነበር።

የኢትዮ ቴሌኮም ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጨረር አክለሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ውሳኔው የአሜሪካንን ሲስተሞች መጠቀም አይችልም የሚል እንደመሆኑ መጠን ጥያቄውም ምን ያህሉ የተዘረጉት ኔትወርኮች የአሜሪካንን ምርቶች ይጠቀማሉ የሚል መሆኑን ገልፀዋል። በአብዛኛው ሁዋዊ የራሱን ሶሉሽኖች ይጠቀማል ያሉት ጨረር፥ በተይም ውሳኔውን ቀድመው ስለጠበቁት ባደረጉት ዝግጅት የራሳቸውን ሲስተሞች ዴቭሎፕ ማድረጋቸው እንደማይቀርም አክለው ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግሥት በቻይናው የቴክኖሎጂ ድርጅት ላይ ለወራት ሲሰነዝር የነበረውን የደኅንነት ስጋትነት ጥያቄ ወደ ተግባር በማሸጋገር ከአሜሪካ ኩባኒያዎች ጋር እንዳይሠራ በጣለው እግድ መሰረት ጉግል መተግበሪያዎቹን ለሁዋዊ ምርቶች እንዳይሻሻሉ ወስኖ ነበር። ነገር ግን የአሜሪካ መንግሥት እንዲሁም የሁዋዊ ምርት ተጠቃሚ አሜሪካዊያን ዝግጅት እንዲያደርጉ ለ90 ቀናት ውሳኔው እንደተነሳ ታውቋል።

በተለይም ጉግል የአንድሮይድ መተግበሪያውን እንዳያሻሽል የሚያደርገው ውሳኔ ሁዋዊን አደጋ ውስጥ ይጥላል ቢባልም፥ ሁዋዊ ግን ሆነር 20 የተባለ አዲስ ምርት ይዞ ብቅ ብሏል። ኹለቱ ባግዙፍ ኢኮኖሚ አገራት የመጪውን ጊዜ የቴክኖሎጂ መሪነት ለመያዝ የሚያደርጉት ግብ ግብ ከቻይና እና አሜሪካ የንግድ ጦርነት ጋር ተደምሮ አሁን ለደረሱበት ውጥረት ዳርጓል ሲሉ ባለሞያዎች አሰተያታቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል።

በ5 ጂ ኔትዎርክ በዓለም መሪ መሆን የቻለው ሁዋዊ እንግሊዝን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አገራት ምርቱን ለመግዛት የነበራቸውን እሽቅድድም በመተው ውላቸውን እንደሚያዘገዩም መግለፃቸው ይታወሳል።

አሜሪካ በተመሳሳይ ክሶች ዚ ቲ ኢ ላይ ለሦስት ወራት የቆየ እግድ አሜሪካ አድርጋ የነበረ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮምም ተመሳሳይ ጥናት በማድረግ በአሜሪካ ውሳኔ ጫና ውስጥ የሚገቡ ምርቶች ካሉ ያስጠና ሲሆን ተመሳሳይ እርምጃ ለሁዋዊ እንደሚወስድ አስታወቋል።

ውሳኔው በዋነኛነት የወደፊት ምርቶች ላይ ጫና የሚያመጣ በመሆኑ በቶሎ የሚታይ ውጤት እንደሌለ ገልፀው በዘላቂነት የሚመጡ ውጤቶች ካሉ ግን በጥናቱ ውጤት መሰረት ቴሌኮሙ እርምጃ ይወስዳልም ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here