1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የተቆረጠለት መሬት ለራስ ቴአትር ተሰጠ

0
624
  • በከተማው አስተዳደር ለቴአትር ቤቱ ግንባታ 4 ሺሕ 500 ካሬ እንዲሰጥ ወስኗል

በተለምዶ አሜሪካ ግቢ ተብሎ የሚጠራው ቦታ ለስድስት ዓመታት ግንባታው ለተንጓተተው የራስ ቴአትር ግንባታ እንዲደረግበት በተለዋጭነት ተሰጠ።

በአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ባሕል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ዳይሬክተር ሜሮን ተሻለ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት 4 ሺሕ 500 ካሬ ሜትር አስተዳደሩ ባልተጠበቀ ጊዜ በመስጠቱ ከማስደሰቱም ባሻገር ከቦታው ስፋት አንጻር በሚሻሻለው ዲዛይን ውስጥ አዳራሽ፣ በሕንጻው ሥርና ፊት ለፊት የመኪና ማቆሚያ እና ዕጽዋት መትከያ አረንጓዴ መሬት እንደሚያካትት ተናግረዋል።
ራስ ቴአትር ግንባታ ሊሠራበት ታስቦ ከነበረው 2995 ካሬ ሜትር ይዞታ ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 265 ካሬ ሜትር በመወሰዱ ተዘጋጅቶ ለነበረው ዲዛይን አፈጻጸም ችግር ፈጥሮ ነበር ታውቋል። በወሰን ይገባኛል ጥያቄ እና በልማት ተነሺዎች ምትክ ቦታ አማራጮች ጋር በተያያዘ ግንባታው እንዳይጀመር እንቅፋት መሆናቸው ታውቋል።

የቴአትር ቤቱን ግንባታ ለማከናወን 335 ሚልዮን ብር በጀት ተይዞ የነበረ ሲሆን በአሁኑ በዲዛይን ለውጥ እንዲሁም በገበያ ዋጋ መናር ግንባታውን ለማከናወን የሚያሰፈልገው ወጪ ማሻቀቡ እንደማይቀር ሜሮን ጨምረው ገልፀዋል። በያዝነው ዓመት ፕላን ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ዲዛይንና አፈር ምርመራ የሚደረግ ሲሆን ግንባታ የሚያካሒዱ ድርጅቶች ጨረታ በመውጣት ግንባታ እንደሚጀምር ሜሮን ተስፋቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።

በ1929 ግንባታው የተጀመረው ቴአትር ቤቱ, በ1930 ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የወራሪው ጣሊያን ጦር ፋሽስታዊ ፕሮፖጋንዳ ይጠቀምበት እንደነበር የታሪበ ድርሳናት ተጽፎ ይገኛል። በ1933 የጣሊያን ጦር ድል ከተመታ በኋላ ሲኒማ ራስ ለጥቂት ጊዜያት ቢሠራም, በ1948 አገልግሎቱን በማቋረጥ በግሪካዊው አስመጪና ላኪ ሚስተር ጆርጅ ሜሪሊያስስ የቡናና የቦሎቄ ማበጠሪያና ወፍጮ ቤት በመሆን ማገልገሉም ታውቋል። በ1952 ዳግም ቢጀምርም ብዙ ሳይቆይ በ1955 ሊዘጋ ችሏል። ከዚህም በኋላም ለ3 ተከታታይ ዓመታት ለከረንቡላ መጫወቻነትና ለመጋዘንነት ማገልገሉንም ታሪክ ያስታውሳል። በ1958 ሮበርት ጀርማህያን የተባሉ አርመናዊ እስከ 1968 የሲኒማ ሥራውን ለዐሥር ዓመታት ካስቀጠሉ በኋላ የመርካቶው ሲኒማ ራስ በ1971 የቴአትር ሥራ በመጀመሩ ራስ ቴአትር የሚለው ስያሜ እንዲያገኝ ሆኗል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here