አገር፣ ሕዝብና መንግሥት

0
701

መላኩ አዳል ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ አገር፣ ሕዝብና መንግሥት የተሰኙትን በጥቅል ትርጉማቸው የሚታወቁ ወሳኝ ቃላት ብያኔዎችና ተያያዥ ሐሳቦችንን መሰረት በማድረግ ነባራዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ቃኝተዋል።

 

አገር ማለት የመሬት ግዛትን፣ ሕዝብንና መንግሥትን የሚያጠቃልል የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥርዓት ነው። ሕዝብ ማለት በአንድ የመሬት ግዛት ውስጥ እርስ በርስ የሚደረግ ጠንካራ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር የፈጠሩ ሰዎች ስብስብ ነው። በዚህ ውስጥ ግለሰቦች ዜጎች ይሆናሉ። መንግሥት ከሕዝብ ውል ወስዶ የሕግ የበላይነት የሚያሰፍን፣ ፍትሕ የሚያረጋግጥ፣ መብት የሚያስከብር፣ ግዴታ የሚጥል የአስተዳደር መዋቅር ነው። የመንግሥት እና የሕዝብ ዋናው ውል ደግሞ ሕገ መንግስት ይባላል። ዓላማውም ዜጎችን ከመንጋው እና ከራሱ ከመንግሥት ጥቃት መጠበቅ ነው።

አንድ ማኅበረሰብ ሕግ አልቦ የተበታተነ የአኗኗር ሕይወት ወጥቶ ተፈጥሯዊ መብቶቹን ማለትም በሕይወት መኖር፣ በነፃነት መኖር እና ንብረት ማፍራት ብሎም ደኅንነቱ ተጠብቆ በሰላም ለመኖር የሚያደርገውን የግል እና የቡድን ትግል በመሪዎቹ አማካኝነት በአንድ ጋራ ዕሴት ላይ ተመስርቶ ከላይ የተጠቀሱትን መብቶች የሚያስከብር ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ በመፍጠር በጋራ ትምምን ላይ የተመሠረተ አገር ይፈጥራል። ይህን ተከትሎ የማኅበረሰቡን ፍላጎትና ዕድገት እንዲሁም ዓለም ዐቀፍ ነባራዊ ሁኔታን ያማከለ የእርስ በእርስ ትድድር -ስርዓት-በማነበር፣ ስርዓቱን መሠረት ያደረገ ተቋማት፣ መዋቅርና የአመራር ግለሰቦችን አካሎ መንግሥት ይፈጠራል።

መንግሥት አንድ አገርን አገር ከሚያደርጉ አካላት (መሬት ወይም ግዛት፣ ሕዝብና መንግሥት) መካከል አንዱ ነው። መንግሥት ሰዎች ባላቸው ራስ ወዳድነትና በተፈጥሮም ውስጥ ያለው ሀብት ውስንነት ምክንያት ደካሞች በጠንካሮች እንዳይበሉ ለሕዝብ ደኅንነት በሕዝብና የመሪነት ብቃት ባላቸው ሰዎች በተደራጀ ማኅበረ-ፖለቲካ ድርጅት መካከል የሚደረግ ውል ነው። መንግሥት የሕግ አውጭ፤ የአስፈፃሚና ዳኝነት (ፍትሕ አካል) ያሉት ተቋም ነው። ካጠፋ በሕግ ተጠያቂ የሆነ ነፃ ሚዲያን ከሕዝብ የመገናኛ መንገድ አድርጎ ይጠቀማል። መንግሥት የሥርዓት አስከባሪነት ሚና የሚኖረው፣ ብሎም አስተዳደራዊ ቢሮክራሲ፤ የፍትሕ አካል፣ ወታደራዊ ተቋም፣ ርዕዮተ ዓለም አመንጭ የሆኑ የሲቪል ማኅበራት ወዘተ የዐቀፈ አካል ነው። መንግሥት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና የሚመራበትን ርዕዮተ ዓለም ከሲቪሉ ኅብረተሰብ ፍላጎት አንፃር ይቀርፃል። በሚያቋቁመው የአስተዳደር ሰንሰለት፣ ፖሊሲዎች የሚተረጎሙበትና የተግባራዊነታቸውም አፈፃፀም የሚቆጣጠርበትና የሚገመግምበት መንገድ ያደራጃል።

መንግሥት ከሕዝብ ባገኘው ውክልና መሠረት በራሱ ያለ ውጭ ኀይል ግፊት የመወሰን አቅም ያለው፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው፣ ዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎችን፣ ሕጎችንና ስምምነቶችን፣ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትንና ፖሊሲዎችን የአገሩን ሉዓላዊነት እስካልነኩ ድረስ የሚቀበል ነው። በተጨማሪም መንግሥት ከሌሎች መንግሥታት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ዓለም ዐቀማዊ ግንኙነት መመሥረት የቻለ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ድርጅት መሆን ይኖርበታል። መንግሥስት ከሕዝብ የተዋዋለውን ውል አፍርሶ አምባገነን የመሆን ዕድል አለው። በዚህ ጊዜ የገዥ መደብ ይፈጥራል። መንግሥት የተሰጠውን ኀላፊነት በብቃት ካልተወጣ ደግሞ ደክሟልና የሕዝብን ደኅንነት፣ የአገርን ሉዓላዊነትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማስጠበቅ አይችልም።

መንግሥት ለሕዝብ አብሮነት መከባበር፣ እኩልነት፣ ሥልጣን ማጋራት፣ ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግና በጋራ ዕሴቶች ላይ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። ከምንም በላይ የሚመራውን ሕዝብ ማሳመንና የሚመራበትም ስልት በትክክለኛው መንገድ መሆኑን ማሳመን ይኖርበታል። የሕዝብ ጉልበት ከምንም በላይ ከፍተኛ ነውና። የሁሉም ድርጊት መነሻው ለሕዝብ ደኅንነት፣ በሀብትና ትምህርት ለመበልፀግ፣ በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በማኅበራዊ ኑሮ ለመለወጥ የሚደረግ የሥራ እርብርብ እንደሆነ ሕዝብን ማሳመን፣ ውጤትም ማሳየትን ይጠይቃል። ለሕዝብ በእኩል ዓይን ማየትና ሁሉም የአገር ልጅ በእኩልነት ተጠቃሚ ሲሆን ማሳየት የአንድ ጥሩ አስተዳደር መገለጫዎች ናቸው። የሕዝብን ስሜት መግዛት ያልቻለ አስተዳደር ምንም የወታደርና የደኅንነት ጥንካሬ ቢኖረው ሕዝብን አንድ አድርጎ ለአንድ ዓላማ ማሰለፍ ስለማይችል አገርን ለውጤት አያበቃም። ለዚህም ለአገር አሳቢና አዋቂ ምሁራንን አማካሪ ማድረግን ይጠይቃል።

የአገረ መንግሥት ሁኔታ፣ ጠንካራ መንግሥት-ጠንካራ ሕዝብ፣ ጠንካራ መንግሥት-ደካማ ሕዝብ፣ ደካማ መንግሥት-ጠንካራ ሕዝብ እና ደካማ መንግሥት-ደካማ ሕዝብ ሊሆን ይችላል። በሕዝብና በመንግሥት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት መሠረት አድርገን መንግሥት ለኅልውናው አስገኝ የሆኑትን ጉዳዮች ሕዝብን ‘በአግባቡ’ በማስተዳደር ሲፈፅም እና እራሱን ደግሞ ካልተገባ የኀይልና የሥልጣን አጠቃቀም ሲቆጥብ የመንግሥትን ጥንካሬ ሊያሳይ ይችላል። ሕዝቡም ደግሞ መንግሥት ሲፈጠር የተሰጡትን ተግባራት እንዲፈፅም ማሳሰብ፣ ግፊት መፍጠር ብሎም ማስገደድ ሲችል እንዲሁም ከመንግሥት የሚደርስበትን ያልተገባ ጫና መቋቋም እንዲሁም ማስቆም ሲችል ጠንካራ ሕዝብ ልንለው እንችላለን።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግሥት በመሪው ፓርቲ እና በመንግሥት መዋቅሩ የነበረው ጥልፍልፍ መላላት ተከትሎ ዕለት በዕለት እየተከፋፈለ ነው። ይህም በአገሪቱ ለሕግ ተገዢ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በየአካባቢው እንዲፈጠሩ እና ሕዝቡም እንደ አንድ ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ ከመቆም ይልቅ በቡድን ተከፋፍሎ የመንግሥት መዋቅሩን ሲሻው በማፍረስ ሲሻው በመቀማት እና ከማዕከሉ በመለየት ላይ ይገኛል። ስለዚህም ፌደራሊዝሙ በነቢብ ካለው ቅርፅ ውጪ በተግባር በመፍረስ ላይ ይገኛል። በአጠቃላይ ሕዝቡም ሆነ መንግሥት ደካማ በሚባል ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት። ይህ በሒደት የአገረ መንግሥት ውድቀት ሊያመጣ እና መንግሥስት አልባሌ ያደርገን ይችላል።

አሁን በኢትዮጵያችን ያለንበት ሁኔታ ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል መንግሥስት አለን ለማለት አስቸጋሪ ከሆነበት ደረጃ ደርሰናል። ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያሉ አስተዳደሮች ተግባራቸውን በአግባቡ እየተወጡ አይደለም። እንደ ዘመነ መሳፍንት ሁሉም የጎጡ ንጉሥ ሆነዋል፤ በተለይም ፖለቲከኞችና ባለሚዲያዎች። ስለዚህም በመንግሥት አካላትና በመብት ተሟጋቾችች የመንጋ ቡድንን መደበቅ ይቁም፣ የፕሬስ ሕግን ተከትለው የማይሠሩ የሚዲያ አካላት ተጠያቂ ይሁኑ፣ ሁሉም የመንጋ ቡድኖች ተጠያቂነት ባደራጇቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በኩል ይፈፀም፣ ከሕወሓት ጋር ያለውን አለመተማመን በድርድር ይፈታ፣ ፌዴራላዊ መንግሥቱ አወቃቀሩ ይስተካከል፣ ፓርቲዎቹ በዘርና በሃይማኖት እንዳይደራጁ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ይከልከል፣ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያለው አስተዳደር ይስተካከል። በተጨማሪም መንጋነታችን ተረጋግጧልና የአገሪቱ መከላከያና ፖሊስ ሥርዓት እንዲያስጠብቅ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታዘዝ። ያለበለዚያ ግን የመንጋ ፖለቲካ በነገሠበት አገር ነፃ ምርጫና የዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ አይቻልም።

አንድ መንግሥት ጠንካራ ሆኖ ለአገሩ ክብርንና ብልፅግናን እንዲያመጣ ከተፈለገ አቅም ያለው የመከላከያ፣ የደኅንነት መዋቅርና የሰው ኀይል ከዘመናዊ መሣሪያ ጋር፣ ጥሩ የጦር ማሰልጠኛዎችና ሠፈሮች፣ ግጭቶችን የመፍቻ ዘዴዎችን የሚጠቀም፣ በዕውቀት የተመሰረቱ የአገር ውስጥና የውጭ ፖሊሲዎችና ተግባሮች፣ አሳታፊና ባለዕውቀት ዜጎችን ወደ ፊት የሚያመጣ፤ አዳዲስ የፍልስፍና የምርምር ዘዴዎችን ለአገራችን ሕግና አስተዳደር እንዲውል ማድረግና ሕዝብን በዘመናዊ መንገድ መምራት የሚችል፣ ሥርዓትና ደንብ፣ የመንግሥት አስተዳደርና አወቃቀር፣ የሹማምንት አሿሿምና ተግባር፣ የባዕላት አከባበር መወሰን፣ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚሰራና አድሎ ያስወገደ አስተዳደር መመሥረት ይጠየቅበታል። በባለሥልጣናት መካከል ያለን የሥልጣን ተዋረድ መጠበቅና ሁሉም የራሱን ኀላፊነት በአግባቡ እንዲፈፀም ማድረግ መቻል ወሳኝ ውጤቶችን የማግኛ ዘዴ ነው።

ኢትዮጵያችን ከዓለም ታላላቅ አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ጥሩ የሆነ የኅልዮትና የተግባር እውቀቶች የሚገኝበትን መንገድ መፈለግና ጥሩ የሆነ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው። ቅርሶቻችንን፣ መጻሕፍቶቻችንን፣ የደን ሀብቶቻችን መጠበቅና መንከባከብ የእኛ የዜጎች ኀላፊነት ነው።

ስለዚህ የአገራችን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን፣ ኦነግንና ጀዋርን ጥጋቸውን ማስያዝ አለባቸው። ሁሉም ነገር ቤትን ከማጽዳት ይጀምራል።

ለተመሳሳይ ዓላማና መራጭ የሚፎካከሩት የአምራው ብሔርተኛ ኀይልና የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚለው የአንድነቱ ኀይል ተደራደረው መፍትሔ ላይ መድረስ አለባቸው። መቀሌ የመሸገው የሕውሓት ቡድን የበለጠ እንዲዳከም መሥራት፣ ወደ ጦርነት የሚገባበትን መንገድም መዝጋት ያስፈልጋል።

ዐቢይ የኢትዮትጵያ ሕዝብ ድጋፍ የሚፈልግና የሁላችንም መሪ ከሆነ ጠባብ ብሔርተኞችን ከመንግሥቱ በማራቅ፣ ብሔራዊ ፓርቲ መመሥረት፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና የፌዴራል አወቃቀር ማስተካከል ይኖርበታል። በጠቅላላው ዐቢይ እየወሰዳቸው ከነበሩ የለውጥ እርምጃዎቹ የገቱትን ምክንያቶች ለሕዝብ ግልጥ ማደረግ አለበት።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here