ከ5 ሚሊየን ብር በላይ የወጣበት የሀብት መመዝገቢያ ሶፍትዌር ሥራ አልጀመረም

0
513
  • ‘ሳይበር ቴክ ሶፍትዌር መልቲሚዲያ’ ሥራውን ከተረከበ 6 ዓመት ሆኖታል

የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከስድስት ዓመት በፊት ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያደረገበት የሀብት መመዝገቢያ ሶፍትዌር እስካሁን ሥራ ላይ አለመዋሉ ታውቋል።

የባለሥልጣናቱን ሀብት በኮሚሽኑ ድረገጽ ይፋ ለማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር ለመሥራት ‘ሳይበር ቴክ ሶፍትዌር መልቲሚዲያ’ የተባለ የሕንድ ድርጅት በ198 ሺሕ ዶላር ዋጋ ሥራውን ከጀመረ ስድስት ዓመታት ቢቆጠሩም እስካሁን ሶፍትዌሩ ሥራ ላይ አለመዋሉን የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ከበበ ዳዲ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ ሳይበር ቴክ እስከ ሰኔ 17/2011 ሶፍትዌሩን ሠርቶ ማስረከብ ካልቻለ ውሉን ለማቋረጥ እንደሚገደድ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የሀብት ምዝገባ ሥራውን ቀልጣፋ ያደርገዋል የተባለው ሶፍት ዌር “ሥራችንን በእጅጉ ያቀልልናል” ብለው እንደሚያስቡ የተናገሩት ከበበ፥ በተወሳሰበ መንገድ የሚ፡ሠሩትን የሀብት ምዝገባ ሥራዎች በቀላሉ ለመከወን ያስችላል ተብሎ ተስፋ ቢጣልበትም ለስድስት ዓመታት ያህል ተግባራዊ ሳይደረግ መቅረቱን ተናግረዋል።

ከበበ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የኮሚሽኑ ተግባር ሀብትን መመዝገብ ብቻ ሳይሆን፣ ሹመኛው ወይም ሠራተኛው ያስመዘገበው ሀብት ትክክል ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ማረጋገጥ ጭምር እንደሆነ በመጥቀስ፥ መዝግቦ እና ማጣራት አድርጎ ያረጋገጠውን ሀብት ለሕዝቡ በግልጽ ይፋ ማድረግ በአዋጅ የተደነገገ ተግባሩ ቢሆንም ከሥራው ብዛትና ክብደት የተነሳ ኮሚሽኑ በዚህ ላይ መቸገሩን አንስተዋል። ይሁን እንጂ የተወሳሰበውን ሥራ ያቀላጥፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሶፍትዌር ስድስት ዓመት ሙሉ እልባት ሳያገኝ መቆየቱ ለሥራው አለመቀላጠፍ ምክንያት መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

ሶፍትዌሩ እስካሁን ሳይሠራ የቆየበትን ምክንያት ያስረዱት ከበበ፣ ድርጅቱ ከሕንድ እየተመላለሰ የሚሠራ በመሆኑና በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ የማሻሻያ ሐሳቦችና ቴክኖሎጂዎች ሲመጡ እንደገና በአዲስ መልክ ለመሥራት የሚደረጉት ጥረቶች ከድርጅቱ ትኩረት አለመስጠት ጋር ተያይዘው ሊያዘገዩት መቻላቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም፣ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሶፍትዌሩ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን የአሠራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ ጥናት ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል። ኮሚሽኑ ‘ለሙስና ተጋላጭ ናቸው’ ተብለው በተለዩ ተቋማት ላይ የአሠራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ ጥናቶች ያካሒዳል ተብሏል።

በማዕድን ዘርፍ የሚታየውን የአሠራር፣ የአሳታፊነትና የሙስና ተጋላጭነት ላይ የሚደረገው ጥናት ግኝት ለሚመለከታቸው አካላት የሚቀርብ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል። በተቋማት ላይ የሚታዩ የጥቅም ግጭቶችን ለማስቀረትና አስቀድሞ የሙስና ድርጊትን ለመከላከል የተጀመረው የተቀናጀ አሠራር በግሉ ዘርፍም ለማካሔድ መታቀዱን ከበበ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
ከ2003-2011 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከ180 ሺሕ በላይ ሹመኞች ሀብት መመዝገቡንም ከበበ ተናግረዋል። የተመዘገበውን ሀብት መጠን ለማጣራት ከፍተኛ ውጣ ውረድና እንቅፋቶች የበዙበት በመሆኑ የተመዘገበውን ሀብት ትክክለኛነት ማረጋገጥ ላይ ዝቅተኛ አፈፃፀም መታየቱንም ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ጠንካራ አቋም ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነሩ በአገሪቱ ሥር የሰደደውን የሙስና ችግር ለማስወገድ የተሻለ የፀረ ሙስና ትግል ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here