‘ገበታ ለሸገር’

0
549

ሰሞኑን ማኅበራዊ የትስስር ገፆችን ያጨናነቀውንና የመወያያ ብሎም የንትርክ መድረክ ሆኖ የከረመው የ‘ገበታ ለሸገር’ የእራት ድግስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቅርቡ ይፋ ያደረጉትን የአዲስ አበባ ወንዞችና ዳርቻዎቸችን የማልማት ሥራ ዕውን ለማድረግ ከ29 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለፃቸው ተከትሎ ጽሕፈት ቤታቸው ‘ገበታ ለሸገር’ በሚል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ለአንድ ማዕድ 5 ሚሊዮን ብር ዋጋ በመመደብ እራት ማሰናዳቱን ከገለጸ በኋላ ሒሳቡን ገቢ ያደረጉ ከ200 በላይ ግለሰቦች፣ ኩባንያዎችና የዲፕሎማሲው ማኅበረሰብ አባላት ያለፈው እሁድ በታላቁ ቤተ መንግሥት በአፄ ምንሊክ የግብር አዳራሽ ታድመዋል።

አንዳንዶች በፕሮጀክቱ ላይ ትችትና ነቀፌታ እንዲሁም በተግባራዊነቱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ በሰፊው አንጸባርቀዋል። በዚሁ ጎራ የሚመደቡ ሌሎች ደግሞ ሥራው ጊዜውን ያልዋጀ ሲሉ አጣጥለውታል። በአሁኑ ወቅት በርካቶች በተፈናቀሉበትና የአገር ኅልውና አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት ፕሮጀክቱን ማስተዋወቅ ቅንጦት ነው በማለት ተችተዋል።

አንዳንዶች በተቃራኒው ፕሮጀክቱን በማንቆለጳጰስ አዲስ አበባ ሥሟን የሚመጥናትና ክብሯን ከፍ የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን የአካባቢ ጥበቃንና ንጽሕናን በተመለከተ ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌታዊ ፋይዳ ያለው ነው ሲሉ አወድሰዋል።

በዕራቱ ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቧራ ማስነሳትና አሻራ ማኖር በሚል ርዕስ ዙሪያ ቀልብ ሳቢ ንግግር ማድረጋቸው ታውቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው ድካማችን፣ ትችቱና ነቀፌታው የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሥራው ተግባራዊ ሲደረግ የሚከስም እንደሆነ አዋዝተው ተናግረዋል። ነገን አሻግሮ የማየት ጉዳይ ነው ሲሉም አክለዋል። “አቧራው ይጭስ ተዉት፤ ስለእሱ ብዙ አታስቡ። እኛ አሻራችንን በክብር እናኖራለን። በክብርም በዚህች ሀገር ታሪክ እንታወሳለን” ሲሉ ለትችቱ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here