ታካሚው ላይ አድማ እየመታ ያለው ሐኪሙ ሳይሆን መንግሥት ነው!

በመላው አገሪቱ የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች የሥራ ከባቢያቸውን፣ የሥራ ላይ ደኅንነታቸው፣ ለሙያቸው ከተሰጠው ትኩረትና ከበሬታ እንዲሁም ጥቅማጥቅማቸውን መነሻ በማድረግ ለመንግሥት ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደነበርና የኋላ ኋላም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። ዶ/ር ዮሴፍ ወርቅነህ የሐኪሙን ጥያቄ በዛቻና ማስፈራሪያ፣ በጥቃቅን ጥቅማጥቅም፣ ፖለቲካዊ አንድምታ በመስጠት ለመግታት መሞከር ችግሩን ከማባባስ ውጪ የሚፈይደው ምንም ነገር የለም ሲሉ ይሞግታሉ።

ከምንም በላይ የሰው ልጅ ሕይወት ክቡር ነው። ሕክምናም የሙያዎች ሁሉ አባት ነው ብለን እናምናለን። የሰው ልጅ ከጤንነቱና ከመኖሩ በላይ አንዳች የሚያሳስበው ነገር ሊኖር አይችልም። መማርም፣ ሀብት ማፍራትም፣ በልቶ ማደርም ከጤንነት በኋላ የሚመጡ ናቸው። የሰውን ልጅ ነፍስ ለመታደግ ሁሉን ነገሩን ለሕዝብ የሰጠው ሐኪም ከምንም በፊት ክብር ሊሰጠው ይገባል። እንዲህ እናምናለን!

ማንም ሳይመርጥ ሐኪም የሆነ የለም። የትኛውም የዓለማችን ክፍል ላይ የሚኖር ሐኪም ለሐኪምነት የታጨው በምርጫው ብቻ ነው። ውጤት አስገድዶት ሐኪም የሆነ የለም። ሕክምናን ፈልገህ፣ ጥረህ ለፍተህ ግረህ ታገኘዋልህ እንጂ, ፈልጎ አያገኝህም!! ሕክምና ውስጥ የገባ ሰው የግድ ከፍተኛ ውጤት መያዝ ግድ ብሎታል። ይህ ሰው ሐኪም ባይሆን ኖሮ የትኛውንም ሙያ መርጦ በየትኛውም ሙያ ሰቃይ ሆኖ የመጨረስ አቅም ነበረው። ሕክምና ውስጥ የተሰገሰገው ጭንቅላት ለሰው ነፍስ ሲባል እየተኮረኮመ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ሳያይ ዓመታቱን ያጠናቅቃል!! እነኚህን ሁሉ የአገራችንን ጭንቅላቶች ሰብስቦ አንድ ሙያ ውስጥ መሰግሰግ ያስፈለገው ከሰው ልጅ ሕይወት ቀድሞ የሚመጣ አንዳች ቁምነገር ስለሌለ ነው።

ይሔን እውነት የዓለማችን አገራት ሁሉ ተረድተውት የመጀመሪያ ትኩረታቸውን ጤናው ላይ አድርገዋል። ማንም ጤና ካልሆነ የትኛውም የሥራ ዘርፍ ጉዳት ይደርስበታል። የአገር ኢኮኖሚ ይናጋል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ይበተናል። ሰው ሠርቶ ማድግ፣ ዘርቶ ማጨድ አይችልም። ስለዚህ የጤናውን ዘርፍ ቀጥ አድርገው የያዙት አካላት በሥራቸው እንዳይማረሩ የተቻለው ሁሉ ይደረጋል።

የአገራችን ሁኔታ ግን የተገላቢጦሹ ነው። ከትልቁ የአገር ጥቅም ይልቅ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል። ሕክምናው ቢበደል የሚያልቀው ዜጋ ሐኪም ያማርር ይሆናል እንጂ መንግሥት ላይ አያምፅም። መብራት ቢቆራረጥ ግን መንግሥት አደጋ ውስጥ ይገባል። ስለዚህ መንግሥት የመረጠው አማራጭ፣ ሆስፒታሎችን በቁሳቁስ ከማሟላት ይልቅ የጤናውን በጀት ቀንሶ ግድቦችን መገንባት ላይ ነው።

በመንግሥት ንዝህላልነት ምክንያት ሕዝብ እያለቀ ነው! ይሔን የሰማነው ከሚዲያ አይደለም። ከፖለቲከኛ ሹመኞች አንደበት አይደለም። ዕለት ተዕለት መዳን እየቻለ ሕይወቱ እስከወዲያኛው የሚያልፈውን ምስኪን በዓይናችን ዓይተን በጣታችን ዳብሰን ነው።

ሰው ታክሞ መዳን ካልቻለ የሚወቅሰው ሐኪሙን እንጂ ማንንም አይደለም። በዚህም ምክንያት እንደክርስቶስ የመንግሥትንም፣ የሙሰኛ አመራሩንም፣ የአገሪቷ ድኅነት መዘዙንም መስቀል በጀርባችን ተሸክመን እንኖራለን። ሆስፒታል ውስጥ አልጋ ጠፍቶ መሬት ለመሬት እየተጎተተ ለሚታከመው ታካሚ ነፍስ መንግሥት ኀላፊነት መውሰድ ነበረበት። ሆስፒታሎቻችንን ለወረሰው በሰው ነፍስ ላይ የሚነግድ አረመኔያዊ ሙስና መንግሥት ኀላፊነት ሊወስድ ይገባው ነበር። መሰረታዊ የምርመራ መሣሪያዎችን በማጣቱ ምክንያት በሬውን ሽጦ መጥቶ በከፍተኛ ወጪ በግል ተቋማት ለሚታከመው ገበሬ ሐኪሙ ሳይሆን መንግሥት ሊጠየቅ ይገባው ነበር። በጣር ላይ ያለ ልጇን ይጣ የመጣች እናት ‘ስፔሻላይዝድ’ ሆስፒታል ውስጥ ኦክስጅን ጠፍቶ ዓይኗ እያየ ሲያልፍባት ጣቷን መቀሰር የነበረባት ሐኪሙ ላይ ሳይሆን መንግሥት ላይ ነበር። በተለያየ የአመራር እርከን ያሉ ሰዎች በፈፀሙት አሻጥር የመንግሥት መድኀኒት የግል ቤቶች ውስጥ ብቻ እጅግ በጣም በተጋነነ ዋጋ ሲሸጡ ሐኪሙ ከአንስተኛ ደሞዙ ላይ ገንዘብ አዋጥቶ ታካሚዎቹን የማዳን ግዴታ አልነበረበትም።

የጤና ተቋማት ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌለው አሻጥር እየተፈፀመ ነው። በዚህ ምክንያት በመጀመሪያ ደረጃ እየተጎዳ ያለው መቀነቱን ፈትቶ ያስተማረን ደሃው ሕዝባችን ነው። ከሕዝቡ በመቀጠል ግን የጤና ባለሞያው ትልቁን ሸክም ተሸክሟል። በኑሮው ደስተኛ አይደለም። አክሞ ማዳን ዳገት ሆኖበት የሐኪም ሙያ ወደ ቀብር አስፈፃሚነት እየተቀየረ ነው። የእያንዳንዱን ግለሰብ ጭንቀት የሚሸከመው ባለሙያ ምንም ማድረግ እየቻለ ስላልሆነ በከፍተኛ የሥነ ልቦና ቀውስ ውስጥ ይገኛል። ለራሱም ያልበቃው ደሞዙ የታካሚዎቹን ምርመራና መድኀኒት በመግዛት እዛው ያልቃል። ራስን መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በማጣቱ ምክንያት ሊያክም የመጣ ሐኪም በሽታ ሸክፎ ይመለሳል። በገዛ ሆስፒታሉ ውስጥ ሲሠራ ለታመመው ሕመም እዛው ሆስፒታል ውስጥ እንኳን በነፃ የመታከም መብት የለውም። ከሰባት እስከ ኻያ ዓመታት ድረስ በትምህርት ላይ ያሳለፈው ሐኪም ቀን ሌት፣ በዐል አዘቦት፣ ቅዳሜ እሁድ፣ ክረምት በጋ ሳይል በግዴታም በውዴታም ሠርቶ ራሱንና ቤተሰቡን ማኖር፣ በኑሮ መለወጥና ማደግ አልቻለም። በዚህም ምክንያት ሺዎች አገር ለቀው ተሰደው በዚህ ሰዓት አገሪቱ ውስጥ 10 ሺሕ የማይሞላ ሐኪም ቀርቷል። ይሔንን ሁሉ ችግር ተረድቶ መልስ ይሰጠናል ያልነውም መንግሥት በሞያችን ክብር ላይ ተሳልቆ መቼም ቢሆን ልናየው ወደማንፈልገው የሥራ ማቆም አድማ እንድናደርግ እየገፋን ነው።

እስከዛሬ ለምን ዝም አላችሁ ሲል ሕዝቡ ይጠይቀናል። ለዓመታት በሰላማዊ መንገድ ስንጠይቅ ኖረን መንግሥት ድምፃችንን ጋን ውስጥ ዘግቶ እንዳስቀመጠው ግን የሚነግርልን የለም። ዛሬ አንድ እርምጃ ገፍተን መንግሥትን ማስጨነቅ ስንጀምር ጥያቄያችን የምንወደው ሕዝባችን ጋር መድረስ ጀመረ።

ለምን አገር እስክትረጋጋ አትጠብቁም ይሉናል። ጥያቄያችን አንድ ቀን ባደረ ቁጥር ሺዎች እየተቀጠፉ እንደሚሔዱ የተረዳ የለም። የሰው ጤና ለፖለቲከኞች እንጂ ለታማሚዎች ጊዜ አይሰጥም። በምጥ ላይ ሆና ደም እየፈሰሳት የመጣችን እናት የኦፕሬሽን ዕቃ የለም፣ መንግሥት ተረጋግቶ ምላሽ እስኪሰጠን ድረስ ጠብቂ አንላትም። ከየትኛውም ነገር በላይ የጤና ነገር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። አገር ብትረበሽም፣ ሕዝብ ቢፈናቀልም፣ ረሃብ ቢገባም፣ ወረርሺኝ ቢከሰትም ሚዲያ ላይ ከሚደረገው መሸፋፈን አልፎ ሀቅ ሀቁን ማየት የሚችለው ሐኪሙ ነው። እናም እንናገራለን! ከሁሉም ነገር በፊት ጤና ይቅደም!!
የዓለም ጤና ድርጅት አገራት በትንሹ ለጤናው ዘርፍ 15 በመቶ በጀታቸውን እንዲመድቡ ቢያስገድድም አገራችን ለጤናው ዘርፍ የምትመድበው ከ5 በመቶ መዝለል አልቻለም። የሐኪሙ ጥያቄ ይሔ መራር እውነት ከቁጥር ወርዶ መሬት ላይ የሚያስከትለው ዕዳ ሲታይ በብዙ ሚሊዮን አሰቃቂ ሞቶች ስለሚመነዘር መንግሥት በአስቸኳይ እንዲያስተካክለው ነው።
የሀኪሙን ጥያቄ በዛቻና ማስፈራሪያ፣ በጥቃቅን ጥቅማጥቅም፣ ፖለቲካዊ አንድምታ በመስጠት ለመግታት መሞከር ነገርን ከድጡ ወደማጡ መጨመር እንደሆነ እናምናለን። እኛ ሰልፍ እየወጣን ያለነው ታካሚዎቻችን መውጣት ስለማይችሉ መሆኑን ሕዝባችን ይረዳልን። በጤናው ዘርፍ ላይ ያለውን እንዝላልነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እስኪሰጠው ድረስ በይደር የማንተወው መሆኑን ሕዝባችን አውቆ ከጎናችን እንዲቆም እንጠይቃለን።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here