ከአዲስ አበባ-ሐዋሳ-ጌዴኦ

0
718

የጉዞ ማስታወሻ

መነሻ አዲስ አበባ
እሁድ፣ ግንቦት 10/ 2011 ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ለአንድ ዓላማ የተሰባሰቡ 16 አባላት ያሉት የጋዜጠኞች ቡድን በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ተገኝተናል። ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን የተወጣጣነው ጋዜጠኞች ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በጌዴኦ ዞን እና በምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን አቅሜ በፈቀደው መንገድ ለማቋቋም እየሞከርኩ ነውና የዜና ሽፋን ስሩልኝ በሚል ጥሪ ነበር። ይህንም ተከትሎ ጉዞ ወደ ውቢቷ ሐዋሳ ከረፋዱ 5 ሰዓት ላይ ተጀመረ። በኹለት ተሸከርካሪዎች ተጭነን ጉዞ ጀምረናል፤ በኤረር በር አድርገን የአዲስ- አዳማን የፍጥነት መንገድ ለመያዝ ቁልቁል ወደ ቱሉ ዲምቱ አቅጣጫ ገሰገስን። እኛን የጫነው ተሸከርካሪ ሚኒ ባስ በተለምዶ ‘high roof’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን እጅግ ቅንጡ እና ፈጣን ነው።

አሁን የአዲስ- አዳማን የፍጥነት መንገድ ተያይዘነዋል ስምንት ጋዜጠኞችን በጉያው ሸክፎ የሚወነጨፈው ተሸከርካሪ ከመንገዱ ምቾት ጋር ተዳምሮ የፍጥነት መንገዱ ላይ ነግሶበታል። እኛም አጠገባችን ካለው የጉዞ ጓዳችን ጋር የባጥ የቆጡን እያወራን ፣ በአንድ ሙያ እንደመገኘታችን የሚያግባባን ብዙ ነውና ባይተዋር የሆነ ሰው አልነበረም። ጨዋታችን እየጠነከረ ለብ ያለውን የምሥራቅ አቅጣጫውን አየር በከፊል በተከፈተው የመኪናው መስኮት በኩል እያስገባን፣ በስሱ ሰውነታችንን እየዳሰሰን ሞጆ ደርሰን ከፈጣን መንገዱ ወጣን።

በኮንቴነር ክምችት የተጥለቀለቀችው ባለደረቅ ወደቧ ሞጆ ሞቅ ደመቅ ያለች ከተማ ናት። እኛም ግራና ቀኝ የተሰደሩትን የንግድ ተቋማት እየገላመጥን ከተማዋን መሐል ለመሐል ሰንጥቀን ወደ ሐዋሳ ከተማ የሚያመራውን መንገድ ተያያዝነው። ከሞጆ ከተማ ወደ ሐዋሳ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ ከፍጥነት መንገድ ለወጣነው ለእንደኛ ዓይነት ተጓዦች የሚመች አልነበረም። የመንገዱ መጥበብ ከሚያስተናግደው የመኪና ብዛትና የመኪኖች ትልቀት ጋር ተዳምሮ አስቸጋሪነቱን እጥፍ አድርጎታል። በእርግጥ ስለ መንገዱ ይህ ብቻ አይበቃም፤ ከመጥበቡም በላይ መንገዱ ላይ የተፈጠሩት ጉድጓዶች ለአሽከርካሪዎች ፈተና ለመኪኖች ጭንቀት ነው።

ከሞጆ ከተማ ርቀን ሔደናል፤ አሁን ከአዲስ አበባ 86 ኪ/ሜ የምትርቀውና ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጋር ሥሟ የሚነሳው ቆቃ ከተማ ደርሰናል። ጥንቅቁ አሽከርካሪያችን የቆቃ ከተማን በጥንቃቄ በማለፍ የነዳጅ መስጫውን ተጭኖ መኪናውን ማስወንጨፍ ጀመረ። ግራና ቀኝ በትላልቅና ነጫጭ ድንኳኖች የተሞላውን የአበባ እርሻዎችን እየታዘብን በሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሐብሐብ ምርቷ ወደ ምትታወቀው መቂ ከተማ አቀናን። መቂ ሞቅ ያለች የንግድ ከተማ ስትሆን በተለይ የሽንኩርት ምርቷ ብዛት ከተማዋን ረግጠን ለምናልፈው ለእኛ እንኳን ሽታውን አልነፈገንም። የሚቀጥለው መዳረሻችን ዝዋይ ከተማ ሲሆን በጉዞ አስተባባሪያችን ለምሳ የምንቆመው እዛው እንደሆነ ተነግሮናል።

በፈጣን መንገድ ላይ ለብ ያለው አየር ፀባዩን ቀይሮ ሞቅ፣ ጋል እያለ ነው። እኛም ከአየር ሁኔታው ጋር አለባበሳችንን በመቀየር ደረብረብ አድርገን የነበርን ከላይ ያደረግነውን በማውለቅ ቀለል ባሉ ልብሶች ብቻ ቀርተናል። ግራ እና ቀኝ ፈንጠር ፈንጠር ብለው የበቀሉት የግራር ዛፎች ቅጠል የሚባል ነገር በላያቸው ላይ የሌላችው እና አካባቢውን በርሃማነት የሚያሳብቅ ነው። ይባስ ብሎ ያሉትንም ግራር ዛፎች በሕገወጥ መንገድ በመቁረጥ ከሰል ለማክሰያነት እንደሚውሉ ታዝበናል። አሁን 160 ኪ/ሜ ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ተጉዘን ዝዋይ ከተማ ደርሰናል። ዝዋይ በርካታ የአበባ እርሻዎችን እና የካስቴል የወይን ማምረቻን በውስጧ የያዘች የኢንዱስትሪ ከተማ ስትሆን፤ በየጊዜው እየተለጠጠች አሁን ካለችበት ስፋት ደርሳለች። ምሳ በዝዋይ የግማሽ ሰዓት ገደማ ቆይታ ካደረግን በኋላ ሐዋሳ ከተማ ለመድረስ የሚቀረንን የ120 ኪ/ሜ ጉዞ ጀምረናል።

የአየር ንብረቱ ከምንቋቋመው በላይ ሞቃት እየሆነብን ነው። ከደቂቃዎች በፊት ለምሳ በቆምንበት ዝዋይ የገዛነው ከበረዶ መለስ ያለው ውሃ አሁን ቅዝቃዜው ጠፍቶ ጭራሽ ለብ ብሏል። በመኪና ውስጥ እናዳምጠው የነበረው በመሣሪያ የተቀነባበረው ሙዚቃ በአሽከርካሪያችን ምርጫ በመንፈሳዊ መዝሙር ተተክቷል። እኛም ጨዋታችንን ጋብ አድርገን በየፊናችን በሐሳብ ነጉደን ይሁን ወይም የገጠር መንደሮችን እየታዘብን ብቻ ዝምታ መኪና ውስጥ ነግሷል። ባለፍንባቸው መንደሮች እና የገጠር ከተሞች አዝናኝ እና ፈገግታን የሚያጭሩ የንግድ ቤት ሥያሜዎችን ታዝበናል። በተመሳሳይም ሞጆ ከፈጣን መንገድ ወጥተን የሐዋሳን መንገድ ከጀመርን ጀምሮ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መለያ የሆነውን ዓርማ እና ቀለም በስፋት አስተውለናል።

አርሲ ነገሌ ከተማ ደርሰናል፤ በመጠኑም ቢሆን ዝዋይን ከለቀቅን ጀምሮ ሰፋ ያለ ከተማን ማየት ችለናል። በዚህ ከተማ የኦነግ ዓርማ ያልተቀባበት ነፃ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች ጣራ ሳይቀር በቀለሙ አሸብርቀዋል። ግርምት የጫረብን ነገር ቢኖር ግን አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አጥር ሙሉ በሙሉ በኦነግ ዓርማ ማሸብረቁ ነው።

በመቀጠል በተባይ ማጥፊያ ማምረቻዋ ምትታወቀው አዳሚ ቱሉ ሙቀቷን ጋብ አድርጋ ተቀብላናለች። አሁን በትንሹም ቢሆን አየሩ ቀዝቀዝ ብሏል፤ ጉዟችንም ወደ ሻሸመኔ ከተማ ተቃርቧል። ሻሸመኔ ከተማ ወደ ወላይታ ሶዶ እና ወደ ሐዋሳ የሚወስዱት መንገዶች መገናኛ ናት። የሐዋሳን መንገድ መርጠን ተንደረደርን አመሻሽ 12 ሰዓት ላይ ሐዋሳ ከተማ ደረስን። ሐዋሳ ድረስ ጉዞውን ሲያስተባብር የነበረው ወጣት ለሌላ ባልደረባው አስረክቦን ወደ አርባምንጭ ከተማ ጉዞውን ቀጠለ። ሐዋሳ ከተማ ሌዊ ሆቴል ነበር እና ማረፊያ የተዘጋጀልን ከመኪናችን ወርደን ሰብሰብ ብለን አንድ የማስታወሻ ፎቶ ከወርልድ ቪዥን ሠራተኞች ጋር በመነሳት ወደ ሆቴሉ የእንግዳ ማረፊያ ገባን። በእንግዳ ማረፊያው ውስጥ እንደሆንን ስለሚቀጥለው ቀን የጉብኝት መርሓ ግብር ገለፃ ከተደረገልን በኋላ ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ወደ ማረፊያችን አመራን።

ጉዞ ወደ ዲላ-ይርጋ ጨፌ
በማግስቱ ግንቦት 11/2011 ሐዋሳ ከሌሊት ጀምሮ ሲዘንብ እንደነበር አላቋረጠም። እኛም በተባልነው ሰዓት ተገኝተን ወደ መኪናችን ገብተናል። ከሐዋሳ ከተማ 100 ኪ/ሜ ወደ ምትርቀው የጌዴኦ ዞን መናገሻ ዲላ ከተማ ጉዞ ጀምረናል። ሐዋሳ የጀመረው የማለዳ ዝናብ ወትሮም ቢሆን ዓመቱን ሙሉ ዝናብ በማይለየው አካባቢ ደግሞ ጭራሽ ብሶበታል። ከሐዋሳ ተነሳን ሐዌላ ቱላ፣ ሞሮንቾ ቱላ እና ሌሎች የገጠር ከተሞችን በማለዳ በቅጡ ሳይነቁ እያለፍን ይርጋዓለም ከተማ ደረስን። ከዓመታት በፊት የተጀመረው ከሐዋሳ – ዲላ – ሞያሌ የሚዘልቀው አስፓልት አሁንም ባለመገባደዱ ጉዟችንን አስቸጋሪ አድርጎብናል። ይሁን እንጂ ግራ እና ቀኝ የሚታዩት የልምላሜ ጥግ የሆኑት የአካባቢው መልክዓ ምድር ቀልባችንን ገዝቶታል። የማኅበረሰቡ ከተፈጥሮ ጋር ያለው መሰናሰል የሚደንቅ ነው። አንድ ሰዓት ከግማሽ ያህል ተጉዘናል፤ ያለመሰሰት ምድሪቱን የሚያረሰርሰው ዝናብ ሳያግዳቸው ብላቴናዎች በዛፍ ከተከለለው መኖሪያቸው ተፈትልከው በመውጣት የያዙትን ፍራፍሬ ለሽያጭ ያቀርባሉ። በነገራችን ላይ ጌዴኦ ዞን የፍራፍሬ ዓለም ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ማንጎ እና አናናስ ደግሞ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው።

አሁን ዲላ ከተማ ደርሰናል። የ15 ደቂቃ የሻይ እረፍት ካደረግን በኋላ አልቃሻውን ሰማይ እየታገልን ወደ ቡና አምራቿ ይርጋጨፌ ጉዞ አደረግን። ከዲላ 42 ኪ/ሜ የምትርቀው ይርጋ ጨፌ ለመድረስ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የሚባል መንገድን ማለፍ ግድ ይላል። ሌሎች ጋዜጠኞችን በመጫን ከፊት ለፊት የሚሮጠው መኪና ከጭቃው አደገኛነት እና ከቦታው ዳገታማነት የተነሳ ወደ ፊት ከሔደበት ይልቅ ወደ ጎን የተንሸራተተበት ይበልጥ ነበር። ዳገታማነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ይርጋጨፌ መንገድ እንደክቡር ዘበኛ ግራና ቀኝ ቀጥ ብለው ካጀቡት ዛፎች ጋር ሲመለከቱት አስቸጋሪነቱን ማስታወስ አይሆንልዎትም። ወደ ከፍታ እየወጣን በመሆኑ በመስኮት በኩል አሻግረን ስንመለከት ልብን የሚሰልብ ልምላሜ ጋር ተገጣጠምን። “ይህ ተይዞ ረሃብ እንዴት ደፈረን?” የሚል ከመካከላችን አልታጣም፤ ምላሽ የሰጠው የለም እንጂ። ሁሉም በሚያየው አረንጓዴነት ተደንቆ ደንዝዟል።
ይርጋጨፌ, ሞያሌ ድረስ የሚዘልቀው አስፓልት ረግጧት ነው የሚያልፈው ይሁን እንጂ ንግድ እንቅስቃሴዎች እምብዛም አይታይባትም። ይርጋጨፌ ደርሰን መኪና ለመቀየር ቆመናል። ከዚህ በኋላ የሚኖረን ጉዞ በቅንጡው መኪና የሚታሰብ አይደለም ከወጣነው ከፍታ በላይ, ሌላ ከፍታ ከበጣም አስቸጋሪ ዳገት ጋር ይጠብቀናል። እኔን ጨምሮ ኹለት ጋዜጠኞች የ1998 ስሪት ቶዮታ ላንድክሩዘር ወደ ሆነ የመስክ መኪና ተሸጋገርን።

ሕይወት በጭርቁ ቀበሌ
ሦስት ጋዜጠኞችን ከኋላ እና የወርልድ ቪዥን ባልደረባን ጋቢና አድርጎ መኪናው ከባዱን ዳገታማ እና ጥርጊያ መንገድ ተያይዞታል። በዚህ ጉዞ አሁንም ከልምላሜ ወደ በጣም ልምላሜ እየተሸጋገርን በመሆኑ አስቸጋሪውን መንገድ ረስተነዋል። አስቸጋሪውን ዳገት ከቁብ ሳይቆጥር የሚሰግረው መኪና ጭርቁ ቀበሌ ደርሶ አቆመ።

ከአዲስ አበባ ያስመጣን አንዱ ምክንያት ወርልድ ቪዥን በዚህ አካባቢ ለ5 መቶ ተፈናቅለው ለነበሩ አባውራዎች ቤት መገንባቱን በማስመልከት ነው። በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ ጭርቁ ቀበሌ ቤቶች ተገንብተዋል የእህል ዘሮችም ተከፋፍለዋል፣ ወርልድ ቪዥን አንድ ዓመት በአካባቢው ሥራ ላይ መቆየቱን አጭር ገለፃ በእንግዳ አሻ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአፋጣኝ እርዳታ ማስተባበሪያ ኀላፊ ተደረገልን።

ከመግለጫው ጀምሮ ተዘዋውረን ለመጎብኘትና ነዋሪዎችንም ለማነጋገር ችለን ነበር። ሰባት ልጆች እናት የሆኑት ዘሪቱ ከበደ “ቤት አልተሰራልኝም በዳስ ውስጥ ነው የምኖረው” የሚል ቅሬታቸውን አስቀድመው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በአካባቢው ስለተፈጠረው ችግር አዲስ ማለዳ ጠይቃቸዋለች። “ከምዕራብ ጉጂ የመጡ ሰዎች ከቦታችን አፈናቀሉን” የሚሉት ዘሪቱ ግንቦት 30/2010 ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በአቅራቢያ ወደሚገኘው ሐሩ የሚባል የገጠር ከተማ መሸሻቸውን ይናገራሉ። አያይዘውም ሰኔ 1/2010 ቤቶቻቸው እንደተቃጠለ እና አሁን ተመልሰው የመጡበት የቀድሞ መኖሪያቸው ሙሉ በሙሉ ወድሞ እንደነበር አልሸሸጉም። እንደ ዘሪቱ አባባል ይህ ዓይነት ችግር 1987 ተከስቶ እንደነበርና እስከ 2010 ግን ሰላም እንደነበር ለመረዳት ተችሏል።

ዘሪቱ በመቀጠልም አሁንም መፈናቀልና ጉዳት መድረሱ በቀጣይም ይፈጠራል ብለው እንደሚያስቡና ፍራቻ እንዳለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሌላ የቀበሌው ነዋሪ የ22 ዓመቱ ተከተል መምህሮ ለአዲስ ማለዳ ከተናገረው “ሲያቃጥሉ እንሰቱንም ጨፍጭፈውብናል፣ ከምዕራብ ጉጂ የመጡ ኦነጎች ናቸው” ብሏል። የስድስት ልጆች አባት የሆኑት ኩራባቸው መንገሻ አዲስ ማለዳ እስክትጠይቃቸው አልጠበቁም “ቡና ፣ ቆጮ፣ አራት ማሳ ሙሉ ተጨፍጭፎብኛል ፖሊስ መጥቶ ምንም ምላሽ አልሰጠንም” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ድጋፍ ወደ ቀያቸው የተመለሱትና አምስት መቶ መኖሪያዎች የተገነባላቸው የጭርቁ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁንም እርዳታው አልተዳረሰልንም በሚል ቅሬታቸውን ያሰማሉ። በወጉ የለበሰ ሕፃን ልጅ ማየት እጅግ ከባድ ነው ወይም የለም፣ ፊታቸው በዝንቦች የተሸፈነ እና እራፊ ጨርቅ እላያቸው ላይ ጣል ያደረጉ ሕፃናት ግን አካባቢውን ሞልተውታል። በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በኩል ስለ እርዳታ አመዳደብ ፍትሐዊነት ለአዲስ ማለዳ ሲገልፁ እንግዳ አሻ “ወደ ቀያቸው ከተመለሱ ሰዎች ውስጥ የድሃ ድሃ የሆኑትን መርጠን ነው ቤት የገነባንላቸው፤ በቀጣይም እንደወርልድ ቪዥን አቅም ተጨማሪ ቤቶችን እንገነባለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የጭርቁ ቀበሌ ነዋሪዎች መከላከያ በአካባቢያቸው ቢሰፍርም እና ሲጠብቃቸው ቢያድርም ድጋሚ ላለመፈናቀላቸው ግን አሁንም ማረጋገጫ ካለመኖሩም ባለፈ ፍራቻም አላቸው።

ኹሉም ነዋሪዎች አምና ግንቦት 30/2010 መሸሻቸውን የሚናገሩ ሲሆን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ዕድሜያቸውን በውል የማያውቁት የዕድሜ ባለፀጋ መሰለች ዋቆ ያን አስቸጋሪ መንገድ በደካማ አቅማቸው ወጥተው ነብሳቸውን ማትረፋቸውን ያስታውሳሉ።

ኤዲዶ ቀበሌ
አሁን የጭርቁ ቀበሌን ለቀን ወደ ኤዲዶ ቀበሌ መንገድ ጀምረናል። በዚህ ቀበሌ ደግሞ ምግብ ነክ ነገሮች ይከፋፈላሉ። አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተጠቃሚዎች ግን አሁንም እርዳታው በቂ አለመሆኑን እና እየተቀነሰ እንደሚሰጣቸው ነው የሚናገሩት። በቀበሌው የወርልድ ቪዥን የምግብ ድጋፍ ኃላፊ ኤልያስ ማሞ እርዳታው የካቶሊክ እርዳታ ድርጅት፣ የአሜሪካ ተራድኦ እና ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን እንደሚሰጥ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አረንጓዴ ድርቅን በአካል ያየንበት የኤዲዶ ቀበሌ አንዱ ነው። ዙሪያ ገባው አረንጓዴ ምንጣፍ እንጂ ደን የማይመስል አካባቢ ከተረጅነት አልተላቀቀም። እኛ በደረስንበት ወቅት በቤተሰብ አባል ብዛት በሰው 15 ኪሎ አተር ክክ፣ 15 ኪሎ ስንዴ እና ግማሽ ሊትር ዘይት ሲከፋፈል ነበር። በዚህ እርዳታም ተጠቃሚ የሆኑት 2 ሺሕ 500 ነዋሪዎች ከኹለት ቀበሌዎች የውስጥ ተፈናቃይ የሚባሉ 267 ሰዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ግን የድሃ ድሃ ተብለው የተለዩ ናቸው።

በኤዲዶ ቀበሌ የምግብ ጣቢያ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ከበደ ኩርሴ “ወርልድ ቪዥን 15 ኪሎ ይላል እንጂ 10 ኪሎ ነው በሰው እየደረሰን የሚገኘው” በሚል ቅሬታቸውን ያሰማሉ። በየወሩ እርዳታው እንደሚደርሳቸው ኤልያስ ቢናገሩም ከበደ ኩርሴ ግን በየ3 ወሩ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።

ገደብ ወረዳ
የሰኞ፣ ግንቦት 12 ጉብኝታችን በዚህ ተጠናቆ አዳራችንን ዲላ ከተማ አድርገናል። ማክሰኞ ጠዋት ጉዞ በሞያሌ አቅጣጫ 70 ኪ/ሜ ገደብ ወረዳ ሆኗል። ከሰዓታት ጉዞ በኋላ ገደብ ወረዳ፣ ገደብ ጉበታ ቀበሌ ደርሰን መኪናችን ወደ ቀበሌው መግባት ስለማይችል በእግር በመጓዝ አኗኗራቸውን መታዘብ ቻልን ። በአካባቢው በርካታ የጉጂ ኦሮሞዎች ተፈናቅለው ወደ ምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ቡሌ ሆራ ወረዳ ሔደው እንደነበርና ከተመለሱ 3 ሳምንት እንደሆናቸው ነው የተናገሩት። የተወሰኑት ተፈናቃዮች በቀድሞ ቦታቸው ላይ ቤት ሰርተው እየኖሩ ቢሆንም 130 አባውራዎች ግን አሁንም በዋጩ ዱቤ የሮሆቦት ቤተክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው ይኖራሉ። ከእነዚህም ውስጥ 300 የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ሕፃናት ይገኙበታል። በገደብ ጉበታ ቀበሌ ለተመለሱ ሰዎች ምንም ዓይነት ቤት እንዳልተገነባላቸው አዲስ ማለዳ ተዘዋውራ ታዝባለች። ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ድጋፍ እየተደረገላቸው ቢሆንም አሁንም የዘር መዝሪያ ጊዜ ሳያልፍባቸውዘር እና የእርሻ መሣሪያዎች እንዲደርሳቸው ልመናቸውን የሃምሳ ዓመቱ ዋጩ ጉሚ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአንፃራዊም ቢሆን ከጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ ገደብ ጉበታ ቀበሌ ተፈናቅለው የነበሩና ወደ ቀያቸው የተመለሱት ጉጂ ኦሮሞዎች በአንፃራዊነት በሚገባ የለበሱ፣ ከምግብ ጥያቄ ይልቅ የሚተኙበት ምንጣፍ እና ብርድ ልብስ የሚያሳስባቸው ናቸው። እኛም በተገኘንበት ወቅት ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ 600 ምንጣፍና ብርድ ልብስ በታማኝ በየነ አማካኝነት ተሰጥቷቸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here