ኢሕአዴግ መንፈስ ነው?

0
1061

የብሔር ድርጅቶች ጥምረት የሆነው ኢሕአዴግ ተመሳሳይ ብሔር ያላቸው ፖለቲከኞች ጥምረት ብቻ ሳይሆን ‘አብዮታዊ ዴሞክራሲን’ እንደ ኅልውና መርሕ ተቀብለው የነበሩ ድርጅቶች ግንባር ነው የሚሉት ይነገር ጌታቸው፥ ግንባሩ አዲስ አስተሳሳሪ ርዕዮተ-ዓለም መቅረፅ ካልቻለ ‘አለ’ ለማለት ይቸግራል ይላሉ።

የቀድሞው የፍትሕ ሚኒስትር ሀርቃ ሀሮዬ ስለ ስልሳዎቹ ትውልድ በጻፉት ድርሳን ላይ ‘ኢሕአፓ መንፈስ ነው’ ይላሉ። በርግጥ በመቶ ሺሕ የሚቆጠር ወጣት የረገፈለትን ፓርቲ መንፈስ ነው ማለት ያስደነግጥ ይሆናል። ግን እውነት ከሆነስ? አንድ ትውልድ ከጎኑ ያሰለፈው ፓርቲ ይናገራል እንጅ አይታይም፤ አለ ይባላል እንጅ አይዳሰስም። የኢሕአፓ ዓለም የሚጨበጥ አልነበረም። ማሕተሙን እንጂ ተስፋውን ማየት አልተቻለም።

ዛሬ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድራት ፓርቲም በዚህ የውድቀት አዙሪት ውስጥ ገብቷል። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ያላትን አገር እየመራ መሆኑ ባያከራክርም ‘አለ’ ለማለት ግን ያዳግታል። የግንባሩ አባላትም መደማመጥ ተስኗቸዋል። የሐሳብ አንድነት ርቋቸዋል። የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አባል ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሀርቃ ሀሮዬን ንግግር በሚያስታውስ መልኩ ሚሊዮን ተከታይ ያለውን ድርጅት ሕልውና የለውም ብለዋል። ይህ ሐሳብ ግን በግንባሩ ሊቀመንበር ተቀባይነት የለውም። ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እኔ የምመራው ፓርቲ በታሪኩ እንደዚህ ጠንካራ ሆኖ አያውቅም ሲሉ ደጋገመው ተደምጠዋል። ጥያቄ ግልጽ ነው። ኢሕአዴግ አለ ወይንስ የለም?

ኢሕአዴግን ወረቀት ላይ አጣሁት
ኢሕአዴግ አለ ወይንስ የለም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመሪያ ኢሕአዴግ እራሱ እንዴት ያለ ነው ማለት ያስፈልጋል። መሐሪ ታደለ (ዶ/ር) “The old EPRDF is dead, can its system be saved? Five seeps to save the federation” በተባለ ጽሑፋቸው ገዥው ፓርቲ አምስት የራሱ መለያዎች አሉት ይላሉ። እነዚህ መለያዎችም ግንባሩ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በፀደቀው ሕገ-መንገግሥት ውስጥ ጉልህ ቦታ ይዘው እንደሚታዩ ይጠቅሳሉ። መሐሪ የኢሕአዴግ መለያ ብለው በቅድሚያ ያነሱት ሐሳብ ለብሔር ብሔረሰቦች መብት የቆመ መሆኑ ነው። ገዥው ፓርቲ የ1960 ትውልድ ክፋይ በመሆኑ በኢትዮጵያ የብሔር ጥያቄ አለ ብሎ ያምናል። በዚህ መነሻም በፓርቲው ርዕዮተ ዓለምም ይሁን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የብሔር ጥያቄን አንድ መሠረታዊ ነገር አድርጎ ተመልክቶታል።

የኢሕአዴግ ሌላው መልክ መሬትን የመንግሥት ሀብት ማድረጉ ነው። የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከብሔር ጥያቄ ባልተናነሰ መልኩ ዋና መፈክር አድርጎ የያዘው ሐሳብ መሬት ላራሹን ነበር። የዚህ ፖለቲካ ታሪክ አካል የነበሩት የኢሕአዴግ መሪዎችም መሬት በጥቂቶች እጅ እንዳይያዝ የራሳቸውን መፍትሔ ለማስቀመጥ ሞክረዋል። ገዥው ፓርቲ ከሌሎች የአገር ውስጥ የፖለቲካ ኃይሎች በተለየ መንገድ መሬት አይሸጥም አይለወጥም የሚል አቋም የመያዙ መነሻም ከዚህ የሚቀዳ ነው። መሐሪ ስለ ኢሕአዴግ የራስ መልክ ሲያነሱ ከላይ የተጠቀሱትን ጉዳዮች በጉልህ ያስቀምጡ እንጅ ብቸኛ አለመሆናቸውን ይጠቅሳሉ። ለማርክሲስት ሌኒኒስት አስተምኅሮ መገዛት፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች ፈጣን አፀፋ መውሰድና ሕዝባዊ አገልጋይነት የሚሉት ገጽታዎችም በገዥው ፓርቲ ቤት ውስጥ የሚስተዋሉ ነበሩ ይላሉ።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ በውሉ የሚመረምሩት መሐሪ የኢሕአዴግን መለያ በአምስት ነገሮች አጠቃለው ቢያስቀመጡም የግንባሩ መልክ ግን ይህ ብቻ ነው ብሎ መግለጽ አዳጋች ነው። እንደውም የፓርቲውን የውስጥ አሠራር ደንብ በአግባቡ ለተመለከተ ሰው ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የራሱ ብቻ የሆኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉት ይረዳል። በ2002 የፀደቀው የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ግንባሩ እንደ ግንባር እንዲቀጥል ዘጠኝ ጉዳዮችን መርሕ አድርጎ ዘርዝሯል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ኹለቱ ለፓርቲው ሕልውና ወሳኝ በመሆናቸው ቀዳሚው ረድፍ ላይ ተቀምጠዋል። የመጀመሪያው ሐሳብ የፓርቲው አብዮታዊ መሆን ነው። ግንባሩ በመተዳደሪያ ደንቡ መግቢያ ላይ “ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም የሚመራና በፕሮግራሙ ላይ ለሰፈሩት ዓላማዎች የሚታገል ድርጅት ነው”ይላል።

ኹለተኛው ጉዳይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በግለሰቦች ትግል ሳይሆን በብሔሮች ትግል ብቻ የሚፈታ መሆኑን ማመኑ ነው። ግንባሩ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራ የሚከተለውን ይላል “ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አገር እንደመሆኗ የተለያዩ ብሔሮቿንና ሕዝቦቿን በአንድነት አሰባስቦ ለማታገል የሚቻለው ግለሰቦችን በተናጠል በሚያሰባስብ ኅብረ ብሔር ድርጅት ሳይሆን የድርጅቶች በተለይ ደግሞ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶች ግንባር በሆነ አደረጃጀት አማካይነት ነው”። ኢሕአዴግ እንዲህ ያለ አቋም የሚያራምደው በግብታዊነት አይደለም። ይልቁኑም የብሔር ድርጅት መሆኑ ኹለት ፋይዳዎች እንዳሉት በማሰብ ነው። የመጀመሪያው ነገር ከአገሪቱ የፖለቲካ መልካዓ ምድር የሚቀዳ ነው። ኢትዮጵያ ብዝኀ ባሕል ያላት አገር በመሆኗ ወደ ሥልጣን የሚመጣው አካል ሁሉንም እኩል እንዲያገለግል ከተፈለገ የብሔር ስብጥር ሊኖር የግድ ይላል። እንዲህ ያለው አሰተሳስብ ደግሞ በአገራች ፖለቲካ ውስጥ ሐቅ ነው። “ባለፉት 25 ዓመታት የተመሠረቱ ፓርቲዎችን የቱንም ያህል ኅብረ ብሔራዊ ነን ቢሉ ከዚህ አዙሪት አልተላቀቁም። በአገራችን የሚካሔዱ ምርጫዎችም ብሔርን እንጅ ርዕዮተ ዓለምን ታሳቢ ማድረግ የቻሉ አልነበሩም። የምርጫ ዘጠና ሰባት ውጤት የሚያሳየውም ይህንን እውነት ነው።ኅብረ ብሔራዊ ነን የሚሉ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል ያሸነፉት በአንድ አከባቢ ብቻ ነበር። ለዚህ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩ አንዱና ወሳኙ ነገር መራጩ ሕዝብ ከርዕዮተ ዓለም ይልቅ ብሔርን ማስበለጡ ነው።

ኢሕአዴግ ከኅብረ ብሔራዊነት ይልቅ ለብሔር ድርጅትነት የማድላቱ ሌላ መነሻ አብዮታዊ ዴሞክራት ነኝ ማለቱ ነው። ድርጅቱ የሚያወጣቸውን የልማት ዕቅዶች እንደየአከባቢው ነባራዊ ሁኔታ መተግበር አለባቸው ብሎ ያምናል። ለዚህ ድግሞ የብሔር ድርጅቶች ወሳኝ መሣሪያ መሆናቸውን ይገልጻል። በመግቢያው ላይ ያነሳነው ኢሕአዴግ አለ ወይንስ የለም ጥያቄ ከእነዚህ ሁሉ ጋር የሚተሳሰር ነው። ገዥው ፓርቲ ‘ከስሟል’ ካልን ከላይ እያነሳናቸው ያለናቸው መገለጫዎቹ ተንደዋል ማለታችን ነው። ‘አለ’ ካልንም በእነዚህ ጉዳዮች መኖር ላይ መግባባት ይኖርብናል።

ኢሕአዴግን ጉልህ መለያው ነው ካልነው የብሄር ፖለቲካ ድርጅትነት አንፃር ከተመለከትነው ያለፈው አንድ ዓመት ጉዞው ፅልመት የዋጠው ነው። የግንባሩ ሊቀመንበር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደውም ድርጅቱ ኅብረ ብሔራዊ መሆን አለበት ብለው እንደሚያምኑ ደጋግመው ተናግረዋል። የብሔር ፖለቲካን እንደሚፀየፉም በተለያዩ መድረኮች ለማሳየት ጥረዋል። ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን የሚለው የመጀመሪያው ቀን ንግግራቸውም ከቆሙበት የብሔር ድርጅት አንፃር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ዐቢይ የሚያራምዱት እንዲህ ያለ አቋም ድርጅታዊ አጥፍቶ መጥፋት የሚሉት ዓይነት ነው። በብሔር ትግል ወደ መሪነት መጥቶ የብሔር ትግል ሳይሆን ኅብረ ብሔራዊ ትግል ነው የሚያስፈልግ ማለትም ተቃርኗዊ ነው።

ከለውጡ በኋላ በኢሕአዴግ ቤት የተፈጠረው አምባጓሮ አንዱ መነሻም ከዚህ የሚመነጭ ነው። ሦስት ዐሥርታትን የኢሕአዴግ አስኳል ሆኖ የኖረው ሕወሓት ገዥው ፓርቲ ግምባር ሆኖ እንዲቀጥል ይፈልጋል። በቅርቡ ባወጣው መግለጫም ድርጅቱ በዚህ ስርዓት ወደ ውሕደት ያመራል ማለት የዋሕነት ነው ብሏል። የሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል ጌታቸው ረዳ በቅርቡ እንደተናገሩት ለሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት የብሔር ፖለቲካ ይከስማል ብሎ የሚያምን ካለ ተሳስቷል ብለዋል። ይህ የጌታቸው ንግግር አድራሻ የሌለው መልዕክት አይደለም። ይልቁኑም የኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት አባሉ ፍቃዱ ተሰማ (የኦዲፒ አባል) ግንባሩ ለመዋኸድ እየተንደረደረ ነው፤ ያልፈለገ አለመሳተፍ መብቱ ነው ለማለታቸው ምላሽ የሚሆን ይመስላል። የዛሬው ኢሕአዴግ ተወደደም ተጠላም የብሔርን ጉዳይ ቅድሚያ የሰጠ ድርጅት አይደለም። ሊቀመንበሩም ሆኑ የለውጥ ኃይል የሚባለው ቡድን ከብሔር ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ይበልጣል እያለ መስበኩም ለዚህ አብነት ይሆናል። ይህ ደግሞ ደግሞ ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ አድርጎ ያቆመው አንዱ ምሰሦ መሰበሩን ያረጋግጣል።

ግንባሩ ከላይ እንዳነሳነው በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚያዊ ፍልስፍናውም ከሌሎች አገራዊ ፓርቲዎች የተለየ ነው። የመሬት ላራሹ አስተሳሰብ ምርኮኛ እንደሆነ የሚነገርለት ኢሕአዴግ በኢኮኖሚው ውስጥ ጠንካራ የሚባል ተሳትፎን መንግሥት ማድረግ አለበት ብሎ ያምናል። በዚህ እምነቱም ከዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር አተካራ ውስጥ ሲገባ ኖሯል። በኢኮኖሚክስ የኖቤል ሽልማትን የተቀናጁት ጆሴፍ ስትግሊዝ (ፕ/ር) ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከብዙዎቹ ሥልጣን ላይ ካሉ አፍሪካዊ ፓርቲዎች በተለየ መንገድ በገብያው ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ ማድረጉ በምዕራቡ ዓለም የሚወደድለት አልነበረም ይላሉ።

በዚህ ምክንያትም የምዕራቡ ዓለም በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት ገበያውን ለውጭ ድርጅቶች ክፍት እንዲያደርግ ሲጎተጉት ቆይቷል። ይሁን እንጅ ገዥው ፓርቲ አንድም ከራሱ ርዕዮተ ዓለም በመነጨ አንድም አገራዊ ጥፋቱ ይጎላል በማለት ነገሩን ሳይቀበል ኑሯል። እንዲህ ያለው ጠንካራ የኢሕአዴግ መለያ ግን ዛሬ የለም። ግንባሩ ባለፈው ዓመት ባሳለፈው ውሳኔ ትላልቅ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል። በርካታ የምዕራቡ ዓለም ድርጅቶችም ግዥ ለመፈፀም ሰልፍ ይዘዋል። የገዥው ፓርቲ ይህን ዓይነት የአቋም ለውጥ ከምንዛሬ ጥረቱ አንፃር የሚጠበቅ ቢሆንም የኢሕአዴግ ሌላው መለያ ስለመጠልሸቱ ግን የማስተባበል አቅም የለውም።

ከተመሠረተ ሦስት ዐሥርታትን ያስቆጠረው ኢሕአዴግ ከውጭ ሲመለከቱት ከላይ በተጠቀሱት ኹለት ጉዳዮች ከራሱ ጋር ተኳርፏል። ከውስጥ ሲመለከቱትም የራሱን መሠረት ንዷል። እዚህ ላይም ተጨማሪ ነገሮችን በማሳያነት ለማንሳት እንሞክር። መሪው ፓርቲ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልጽ እንዳሰፈረው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የኅልውናው መሠረት ነው። የግንባሩ እህት ድርጅቶች አብረው የመኖራቸው ምስጢርም ይኼው የጋራ ቃል ኪዳናቸው ነው። የአዴፓም ሆነ የኦዲፒ፣ የደኢሕአዴንም ሆነ ህወሓት የጋር ግዛታቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሆኑ አያከራክርም። የአብሮነታቸው ርዕይ የተገመደው ከርዕዮታቸው ነው። ያ ካልሆነ ለደብረፅዮን አብረሃ ደስታ ይቀርባቸዋል። ለኦቦ ለማ መገርሳ ዳውድ ኢብሳ ይሻላቸዋል። ለሞፈሪሃት ካሚል በየነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) ይበልጡባቸዋል። ለደመቀ መኮነን ደሳለኝ ጫኔ(ዶ/ር) ይሻላቸዋል። ግን እንደዛ አልሆነም። ኢሕአዴግ የተሰባሰበው በብሔር ሳይሆን በርዕዮተ ዓለም ነው።

አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚሉት ርዕዮት ሁሉንም ያስተሳሰረ ገመድ ነው። ገዥው ፓርቲ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አንድ አድርጎኛል የሚለው የሐሳብ ግዛት ስለሆነው ብቻ አይደለም። ኢሕአዴግ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ እህት ድርጅቶቹ አንድ ሆነው የሚቀጥሉት አብዮታዊነታቸው ከሐሳብ ያለፈ የተግባር የጋራ ግዛት ከሆናቸው ነው ይላል። በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 7 ላይ “ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አገራዊውን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም በየክልላቸው የመፈፀም ግዴታ አለባቸው” ማለቱም ከዚህ የመነጨ ነው። ለዚህ ያልተገዙ እንደሆነም ከድርጅቱ እንደሚሰናበቱም በአንቀፀ 13 በዝርዝር ጠቅሷል። ወረቀት ላይ ያለው ኢሕአዴግ በዚህ ቢያምንም የዛሬው እውነታ ግን ከዚህ የሚለይ መሆኑ አያከራክርም።
የግንባሩን እህት ድርጅቶች የጋራ ርዕይ ያላቸው አይደሉም። አንድርያስ እሸቴ (ፕ/ር) ፍሪድሪክ ኧርበርት ስቲፍቱንግ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ የለውጥ ኃይሉ የያዘው መሥመር ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እጅጉን የራቀና ለሌበራል ዴሞክራሲ የቀረበ ነው ይላሉ። ይህ የሌበራል ዴሞክራሲ ጅምር ግን ገና ዳዴ የሚል ነው። በዚህ ምክንያትም የግንባሩ እህት ድርጅቶች የአብሮነት ቃል ኪዳናቸውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ ጎን ቢገፋም የጋራ ነገር መፍጠር ተስኗቸዋል። ደኢሕዴንን ኢሕአዴግ የሚያስብል፣ ሕወሓትን ኢሕአዴግ ብሎ የሚያስጠራ፣ አዴፓን ብሎም ኦዲፒን የአንድ ግንባር አባል እንድንላቸው የሚያደርግ ርዕዮተ ዓለማዊ ምክንያት ዛሬ ያለ አይመስልም።

መሐሪ “Can Ethiopia make the Transit to Stability” በሚለው ጽሑፋቸው በኢሕአዴግ ቤት ካለው የርዕዮተ ዓለማዊ መቀራረብ ይልቅ እህት ድርጅቶቹ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለቸው ተመሣሥሎ የጎላ ነው ይላሉ። ሕወሓት ከኦነግ ጋር በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚቀራረብ አቋም አለው። የኦዲፒ አመራር ከሕውሓት ይልቅ ግንቦት ሰባት ጋር ያለው የሐሳብ ዝምድና የላቀ ነው። ይህ ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ያለው የግንኙነት መሥመር ከሞላ ጎደል እንዲይቋረጥ አድርጓል። ፓርቲው ውስጥ ያለው አመራርም መደማመጥ ተስኖታል። በጋራ ግብ ላይ የተመሠረተው የእህት ድርጅቶቹ አብሮነትም በግለሰብ መፈቃቀድ ላይ ተመሥርቷል። በዚህ ምክንያትም ኢሕአዴግ በሥም እንጂ በግብር የለም። የዛሬው ሕልውናውም ‘ደ ፋክቶ’ ልንለው የምንችለው ነው።

ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ የማድረግ ፈተና
ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ የማድረግ ፈተና ገዥውን ፓርቲ የፖለቲካ ድርጀት የማድረግ የቤት ሥራ ማለት ነው። ይህ የቤት ሥራ ፈርጀ ብዙ ተግባራትን ይጠይቃል። የመጀመሪው ተግባር የጋራ ሕልም መፍጠር ነው። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አባልና ደጋፊዎቹ የሚጋሩት የወል አስተሳሰብ ሊኖረው ይገባል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ኹለት ፋይዳዎች ያሉት ነው። የመጀመሪያው ጉዳይ ፓርቲው ከግለሰቦች ፍላጎት ተላቆ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው ያደርጋል። ሌላው ጠንካራ ፓርቲያዊ አንድነት ይፈጥራል። በፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ የጋራ ራዕይ የሚቀዳው ግን ከሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም ነው። ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ ለማድረግ ከሁሉም በፊት አባላቱ የሚያልሙት አንድ ሕልም ሊኖራቸው ይገባል ሲባል ጠንካራ ርዕዮተ ዓለም ያስፈለጋል ማለትም ነው። ገዥው ፓርቲ ትናንት የመጣሁበት መንገድ አላዋጣኝም ካለ በሥምምነት አዲስ ርዕዮት ሊፈጥር ይገባል።

ይህ አዲስ የርዕዮተ ዓለም ፈጠራ መንትዮችን በቀዶ ጥገና ከመለያየት ጋር የሚመሳሰል ነው። ኢሕአዴግ የተወለደው ከአብዮታዊ ባሕሪ ጋር ነው። ከሦስት ዐሥርታት በኋላ ድርጅቱን ከዚህ ርዕዮተ ዓለም ማላቀቅም አዲስ ፓርቲን ከመመሥረት የማይተናነስ ተግባር ነው። እዚህ ላይ ኹለት ነገሮችን ማንሳት ተገቢ ይመስላል። አንደኛው ግንባሩ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ከቀየረ እህት ድርጅቶቹ አብረው የመቀጠላቸው ፈተና ነው። ለአብነት ያህል ሕወሓት የርዕዮተ ዓለም መቀየር ጉዳይ በዚህ ጊዜ መሆን የለበትም የሚል አቋም ስታራምድ ቆይታለች። ይህ የፓርቲ አቋም ነገ ከሌሎች ጋር ተዳምሮ ሕወሓትን ከኢሕአዴግ ቤት ላለመሸኘቱ ማንም እርግጠኛ አይደለም። እንዲህ ያለው ተግባር ደግሞ ዳሩ ሲነካ መሐሉ ዳር ይሆናል የሚለውን ተረት በኢሕአዴግ ቤት እንድናይ ሊያደርገን ይችላል። ኹለተኛው ጉዳይ በአንፃሩ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተጠመቁ የፓርቲው አመራርና ደጋፊዎች ድርጅታቸው የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ቢያደርግስ እነሱ ከውስጣቸው ይቀየራሉ ወይ የሚለው ነው።
ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ የማድረግ ፈተና የጋራ ሕልም በመፍጠርና አዲስ ርዕዮ ዓለም በማበጀት ብቻ የሚሳካ አይደለም።

ገዥው ፓርቲ ስትራቴጅካዊ አመራር የለውም። ከዚህ ቀደም በዚሁ አምድ ላይ እንደገለጽኩት የኢሕአዴግ አንዱና ግዙፉ ችግር ሐሳብ የማመንጨት አቅሙ የከዳው መሆኑ ነው። ድርጅቱ አገራዊና ነባራዊ ሁኔታዎችን አስቀድሞ መተንበዩ ከተፈጠሩ በኋላም ፈጣን መፍትሔ የሚሰጥበት አቅሙ ተሟጧል። በዚህ የተነሳም አገራዊ ቀውሶችን ከሕዝቡ ጋር አብሮ ወደ መሞቅ ተሸጋግሯል። የእህት ድርጅቶቹ አመራሮችም ከዚህ ለማምለጥ ሕዝበኝነትን ምሽግ አድርገዋል። እርስ በእርስ በመካሰስም የአደባባይ እሰጥ አገባ ፈጥረዋል። በመሆኑም ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ ለማድረግ ስትራቴጅካዊ አመራር ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ኃይል የራሱ ማኅበራዊ መሠረት መፍጠር የቻለ አይደለም። በዚህ ምክንያትም ቁሜለታለሁ የሚለው የኅብረተሰብ ክፍል የቱ እንደሆነ አይታወቅም። አብዮታዊ ዴሞክራሲን ማተቡ ያደረገው ኃይል በአፍም ቢሆን የቆምኩለት ሕዝብ አርሶ አደሩ ነው ይል ነበር። ዐቢይ መራሹ ኢሕአዴግ ግን ለአርሶ አደሩ ቁብ አይሰጥም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አርሶ አደር መንደር የተገኙበት አጋጣሚ ጥቂት ነው። የሚመሩት ለውጥ ለአርሶ አደሩ ምን እንደሚፈይድም አልነገሩትም።

ኢሕአዴግን ኢሕአዴግ ማድረግ ኢትዮጵያን የማረጋጋት አንድ አካል ነው። የገዥው ፓርቲ ውስጣዊ አለመረጋጋት በአገራዊ አለመረጋጋቱ ላይ የበኩሉን ሚና ሲወጣ ኖሯል። የፌደራል ስርዓቱን በማናጋቱም በ‘ደ ፋክቶ’ ኢትዮጵያ የኮንፌደሬሽን ባሕሪ ተላብሳለች። በመሆኑም ገዥው ፓርቲ ከቆመበት የገደል አፋፋ መራቅ ይኖርበታል። ይህን ማድረግ የሚችል አመራር አለ ወይ የሚለው ጥያቄም ነገን ተንተርሷል።

ይነገር ጌታቸው ተለያዩ መገናኛ ብዙኀን በማገልገል ላይ የሚገኙ ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው
mar.getachew@gmail.com ሊገኘኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here