የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ እግድ ተገቢ ወይስ የደቦ ፍርድ ያመጣው ውሳኔ?

0
1225

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እና የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ሲተላለፍ የቆየውን የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ ሸማቾችን የሚያሳስት መልዕክት ይዟል በሚል ምክንያት ከግንቦት 6/2011 ጀምሮ በማንኛውም ሚድያ እንዳይተላለፍ ያስጠነቀቀበት አግባብ የፍትሓዊ ጥያቄ ያስነሳል ሲሉ ቤተልሔም ነጋሽ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

 

“በማስታወቂያ ብዙ የቴክኒክ ሰዎች አሉ። ሕጎቹን በሙሉ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ማስታወቂያ ማግባባት መሆኑን ይረሱታል። ማግባባት ደግሞ ሳይንስ አይደለም። ማስታወቂያ የማግባባት ጥበብ ነው።”

ዊሊያም በርናባች
ለሳምንታት ተመልካቹን ምን ይሆን የሚል ልብ ሰቀላ ውስጥ ከትቶ ካቀየ በኋላ ያ የአንበሳ ምልክትና “ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም” መፈክር ሌላ የቢራ ምርት መሆኑ ሲገለጽ ነበር ጫጫታው የጀመረው። እንደኔ በኋላ ተጋኖ ምርቱ ላይ ባለመጠቀም ተአቅቦ እናድርግ ወደሚለው እስኪሸጋገር ድረስ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ተቃውሞ ይሔን ያህል ተጋኖ ፣ ልባችንን ሰቅሎ ሲያበቃ ሌላ ቢራ ሆኖ አረፈው ዓይነት ተቃውሞ ይመስለኛል። እንጂማ! ቢራ ማስተዋወቅ በሕግ ተከልክሎ በፓርላማ ፀድቆ እያለ, ጥቂት ሳምንታት የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ እስከዛሬ ሁሉም ቢራዎች ሲደምሩት ከቆዩት ሚዲያውን የመቆጣጠር አባዜ አንፃር ውጤቱ እምብዛም አልነበረም።

አንበሳ ቢራ ከመጠጥ ጋር የማይገናኝ የተጋነነ ተምሳሌት አምጥቶ ለማስተዋወቅ በመሞከር የመጀመሪያው አይደለም። ቢራን ከአገር ፍቅር ጋር፣ ቢራን ከኢትጵያዊ ማንነት ጋር፣ ከጥቁርነትና ከፓን አፍሪካኒዝም አንፃር የሚቃኝ ሐበሻ የሚባል ቢራ ማስታወቂያ ሲነገር ምናልባት ወደ ኹለት ዓመት ይጠጋል። ሌላው ቀርቶ በዚሁ በሰሞናችን ከግንቦት 21/2011 ጀምሮ ማንኛውም የአልኮሆል ማስታወቂያ በመገናኛ ብዙኀን መተላለፉ እንደሚቆም የሚደነግገው ሕግ ተግባራዊ መሆኑ ያሳሰበው የሚመስል እርምጃ ሐበሻ ቢራ አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሔድ ነበር። ኹለት ኹለት የሆኑ ፀጉራቸው አፍሮ የሚባለው ዓይነት ስታይል ያላቸው ባለ ጥቁር ቀሚስ ሴቶች ከተማውን ሲያጥለቀልቁት ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው “ምንድን ናቸው?” እያለ ፎቷቸውን ሲቀባበል ከቆየ በኋላ የሐበሻ ቢራ አንድ ውድድርን ያካተተ ማስታወቂያ መሆኑ ሲታወቅ ምላሹ የተደባለቀ ነበር። የአንበሳ ቢራውን ያህል ተቃውሞ ባያስነሳም በዛ የሚል አልጠፋም። ጎልቶ የወጣው ተቃውሞ ደግሞ “እንዴት ሲደረግ ሴቶችን በአደባባይ እያዘዋወረ ማሻሻጫ ያደርጋቸዋል?” የሚለው ነበር። ይህን ስመለከት የመጣልኝ “ሴቶች ማሻሻጫ መሆናቸውን ያያችሁት/የሰማችሁት ዛሬ ነው ወይ?” የሚል ነበር። በተጨማሪም ሴቶችን ከማይገናኝ ማስታወቂያ ጋር ሁሉ እየሰነቀሩ ምርቱን ሳይሆን ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ በሚመስል አኳኋን ማቅረብን የምቃወም መሆኔ እንዳለ ሆኖ “ሴቶቹ መጠቀሚያ ሆኑ” የሚለውን አባባል ሙሉ በሙሉ አልስማማበትም። ሴቶችን እንደ ተጠቂ ወይም ረዳት አልባ የሚደርጉትን የማያውቁና ጥበቃ የሚያሻቸው አድርጎ ከማቅረብ የመነጨ ነው ብዬ ስለማስብ። ፈቃድ እንዳላቸው፣ ክፍያ ተከፍሏቸው፣ ፈቅደው ሊሠሩት መቻላቸውንም ማሰብ ጥሩ ነው።

ለዛሬ ሐሳባችን መነሻ ወደ ሆነው የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ እግድ ስንመለስ፤
የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በፃፈው ደብዳቤ መሠረት በተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እና የኅትመት መገናኛ ብዙኀን ሲተላለፍ የቆየውን የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ ሸማቾችን የሚያሳስት መልዕክት ይዟል በሚል ምክንያት ከግንቦት 6/2011 ጀምሮ በማንኛውም ሚድያ እንዳይተላለፍ አግዷል።

ማስታወቂያው የታገደው የቢራ መጠጥ በሳይንሳዊ የፍተሻ ሒደትም ሆነ በኑሮ ልማድ ባለ ዕውቀት ብሩህ ተስፋ ላለው ልባም ተጠቃሚ ሊጠመቅ የሚችል መጠጥ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት መረጃ በሌለበት ሁኔታ “ብሩህ ተስፋ ለሚታየው ልባም፤ ለልባሞች ከልብ የተጠመቀ” በሚል እንዲተዋወቅ መደረጉ ስለንግድ ማስታወቂያዎች የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፉ መሆኑም ተገልጿል።

በንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀፅ 19/8 መሰረት በአዋጁ መሰረት የንግድ ዕቃ ወይንም አገልግሎትን በመጠቀም የሚጠበቅ ውጤትን አሳሳች በሆነ መንገድ መቅረፅ ክልክል እንደሆነ የሚገልፀውን አንቀጽ በመተላለፉ መሆኑን ደብዳቤው ይጠቅሳል።

የእገዳ ደብዳቤው ለሁሉም የኤሌክትሮኒክስ እና የኅትመት ሚድያዎች እንደተሰራጨ እና እገዳውን በመተላለፍ የንግድ ማስታወቂያውን የሚያስተላልፍ ማንኛውም አካል በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆንም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
እግዱ ተገቢ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ክርክር በኋላ የምመጣበት ሆኖ በቅድሚያ የሸማቾች ባለሥልጣን ደብዳቤ ባዘዘው መሠረት እየተተገበረ ነው ወይ የሚለው ላይ ግን ጥያቄ አለኝ።

አጋለጥሽ አትበሉኝና ባለፈው ሰኞ፣ ግንቦት 12 ለምሳሌ ማታ የሳተላይት ቴሌቪዥን ቻነሎችን ስቀያየር አንዱ ቻነል ላይ ማስታወቂያውን አይቼዋለሁ፤ ምናልባት ኢቢሲ ራሱ አስተላልፎት ይሆናል። እገዳው ቢልቦርድ ማስታወቂያዎችን ይመለከስ ይሆን በግልፅ አልተመለከተም። ጠዋት ጠዋት ከቤት ወደ ሥራ በምመላለስበት መንገድ በየባቡሩ ፌርማታ ላይ የተለጠፈውን ማስታወቂያ ስመለከት ያሰብኩት ይህንን ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ቢራ አምራቹ ማስታወቂያው እንዲተላለፍለት የረጅምም ይሁን የአጭር ጊዜ ውል ገብቶ ቢሆን ይህ የሚስተናገድበትን አግባብም አላመለከተም። አመልክቶም ከሆነ በደብዳቤው በግልጽ አልተቀመጠም። ይህ ባልሆነበት ማስታወቂያው በተለያዩ መንገዶች መተላለፉን ቀጥሎ ስናይና በተለይ በእኔ አስተያየት ባለሥልጣኑ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ የሚባሉ ኹነቶች ሲፈጠሩ የት ነበር የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። ሕግ ማስከበር ዛሬ ላይ መጀመር ይቻላል ብለን ብናስብም የንግድ ውድድር ባለበት ለአንዱ ተፈቅዶ ለሌላው ሲከለከል የፍትሐዊነት ጥያቄም ያስነሳል።

ስለማስታወቂያ የወጣው አዋጅ ቁጥር 759/2004 በሚሰጠው ትርጓሜ መሠረት
“ማስታወቂያ” ማለት የምርት ወይም የአገልግሎት ሽያጭ እንዲስፋፋ ወይም ሥም፣ ዓርማ፣ የንግድ ምልክት ወይም ዓላማ እንዲተዋወቅ በማስታወቂያ ማሰራጫ መንገድ አማካኝነት የሚሰራጭ የንግድ ማስታወቂያ ሲሆን የሕዝብ አገልግሎት ማስታወቂያንና የግል ማስታወቂያን ይጨምራል፤ ካለ በኋላ ስለ ባሕርያቱ በዘረዘረበት አንቀጽ ሥር የሚተዋወቀውን ምርት ወይም አገልግሎት እውነተኛ ባሕሪ፣ ጥቅም፣ ጥራትና ሌላ መሰል መረጃዎችን የሚገልጽ፤ መሆን እንዳለበት ደንግጓል።

ክፍል ሦስት ቁጥር 7 ሕግን ወይም መልካም ሥነ ምግባርን ስለሚፃረር ማስታወቂያ በሚለው ሥር ደግሞ የሚከተሉት ማስታወቂያዎች ሕግን ወይም መልካም ሥነ ምግባርን የሚጻረር ይዘት ወይም አቀራረብ እንዳላቸው ሆነው ይቆጠራሉ ካለ በኋላ ንዑስ ቁጥር (1) ለምሳሌ ቋንቋን፣ ፆታን፣ ዘርን፣ ብሔርን፣ ብሔረሰብን፣ ሙያን፣ ሐይማኖትን፣ እምነትን፣ ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ አቋምን አስመልክቶ የሰው ልጅን ስብዕና፣ ነጻነት ወይም እኩልነት የሚጻረር ምስልን፣ አነጋገርን ወይም ንጽጽርን የያዘ ማስታወቂያ፤ ብሎ ሌሎችን ከዘረዘረ በሁላ በቁጥር 12 በሌላ ሕግ የተከለከለ ይዘት ወይም አቀራረብ የያዘ ወይም ማንኛውም ሕግ እንዲጣስ የሚያነሳሳ ማስታወቂያ።

በሚል ጥቅል ሐሳብ ያስቀምጣል።
ይህን ያነሳሁት አንድ ምሳሌ በማሳየት በሴቶች ገጽታ ላይ አሉታዊ ምስል የሚሰጥ፣ በሕግ የተረጋገጠውን የፆታ እኩልነትና ሴቶችን ማንቋሸሽን የሚከለክለውን ሕግ የሚጋፋና የሚፃረር ንጽጽር ከዚህ ጋር መቅረቡን ለማሳየት ነው። ይኸውም የምታስታውሱ ካላችሁ ሐረር ቢራ በአንድ ወቅት ያስነግረው የነበረ ማስታወቂያ ሲሆን አንድ ወጣት መጠጥ ቤት ተቀምጦ ወደ ፊት ለፊቱ በደስታና በፈገግታ ሲመለከት ያሳይና ከፊት ለፊቱ የምትመጣን ሴት ያሳያል። ሁላችንም ፈገግታው ለሴቲቱ እንደሆነ ስንገምት ሴቲቱን ትቶ አስተናጋጅ ወደ ሚያመጣለት ቢራ ሰፈ ብሎ ሲሔድ ያሳያል። በወቅቱ ራሴን ጨምሮ ይህን ማስታወቂያ የተቃወምን ስለመኖራችን አላስታውስም። ባለሥልጣኑም ይህንንና ሌሎች በሕፃናት ሥነ ልቡና ላይ ጉዳይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጨምሮ ሌሎች ጥሰቶች ሲካሔዱ በዝምታ ተመልክቷል።

በእኔ ግምት የታገደው ማስታወቂያ ብቸኛ ችግር ያልተመጣጠነ የሚባል ዓይነት ግነት ወይም ለቢራ የማይገባ የተካበደ ነገር መጥቀሱ ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የቀረበበት ወቅት የቢራ ማስታወቂያ ብዛትና ሚዲያውን ያለ ሰዓት ገደብ መቆጣጠር ተቃውሞ ጫፍ ደርሶ በነበረበት ወቅትና የተጠራቀመ ተቃውሞ ብሶት ያመጣው መሆኑ ውጤት ይመስለኛል።
እንጂማ! እስከዛሬ ከቀረቡት አንፃር ከመስመር የወጣ ስለሆነ ወይም አሳሳች ስለነበር አይደለም።

ለምሳሌ ከላይ በጠቀስኩት አዋጅ ቁጥር 8 ስለአሳሳች ወይም ተገቢ ያልሆነ ማስታወቂያ በሚለው ሥር አንድ ማስታወቂያ አሳሳች ነው የሚባለው የሚከተሉትን ካካተተ ነው በሚለው ሥር ከተዘረዘሩትና በቤታ ጥበት ምክንያት ላሳያችሁ ከማልችለው 18 ነጥቦች መካከል የአንበሳ ቢራ ማስታወቂያ ሊወቀስበት የሚችለው ግነትን የሚከለክል አንድም ነጥብ የለም።

ማስታወቂያ በዓለማችን ላይ ታላላቅ ኩባንዎችና የንግድ ድርጅቶች ተጠቃሚውን ወይም ሸማቹን ለመቆጣጠር የሚጠቀሙበት ከፍተኛ ጉልበትና የማግባባት ኀይል ያለው መሣሪያ ነው። በየትኛውም የዓለም ክፍል መድኀኒትና የማነቃቃት ኀይል ያለው ወይም ለአንድ ውስን ውጤት (ለምሳሌ ኀይል ሰጪ መጠጥ) ተብሎ የተዘጋጀ ካልሆነ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ እንዲኖረው አይጠበቅም።

ማስታወቂያ የፈጠራ ችሎታ የሚጠይቅና የተመልካቹን ቀልብ ለመያዝ ሲባል ግነት የሚጠቀም መሆኑ ግልጽ ነው። ሁሉንም ማስታወቂያ እንገምግም ቢባል እንደየግለሰቡ አመለካከት ብዙ አቃቂር ሊወጣለት ይችላል። የሚሻለው እንደ አንድ የጥበብ ዘርፍ ወስዶ ሰዎች የፈጠራ ችሎታቸውን ተጠቅመው እንዲሠሩ ነፃነት መስጠት ነው።

ሊዮ ቡርኔት የተባለ ሰው በእኔ አመለካከት፣ በማስታወቂያ ማሳካት የሚቻለው አንድ ትልቅ ነገር ተዓማኒነትን ነው ፣ እናም ከምርቱ በላይ ተዓማኒ የሚሆን ምንም የለም እንዳለው ተመልካቹ ያን ያህል የዋህ ነው ብሎ ማሰብስ ይቻላል? ቢራ ጠጥቼ ግድግዳ እጠረምሳለሁ ብሎ ያምናል? ልባም የምሆነው ያንን ቢራ ስለጠጣሁ ነው ይላል? በፍፁም አይመስለኝም! የቢራን ጥቅም ያውቃል፣ የሚጠጣበትንም ምክንያት እንዲሁ ይገነዘበዋል ተብሎ ይታሰባል። በዚያ ደረጃ መገመትም አግባብ አይመስለኝም።
ሊዮ ቡርኔት ጨምሮ እንዳለው “እኔ ማስታወቂያ የሚመጣብኝ ሥጋት ሰዎችን ያሳስታል ወይ የሚለው ሳይሆን አሰልቺ ሆኖባቸው ይደበሩ ይሆን ወይ” የሚለው ነው።

ሌላው አገር የማስታወቂያን ፈጠራ ውጤትነትን ከማመኑ ባሻገር ደባሪውን ትቶ ምርጡን ይሸልማል። ሽልማቱን ብንተወው እንኳን በግልጽ የሚታይ ውሸትና ጥፋት ባልተፈፀመበት ማስታወቂያን ማገድ ስሜታዊ ሆኖ ሆ! ብሎ የተቃወመውን ሕዝብ ለማስደሰት ካልሆነ በስተቀር ውሃ የሚቋጥር ምክንያት የለውም። እንዲያውም በፈጠራና ራስን በመግለጽ ነፃነት ላይ ጣልቃ መግባት ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here