‘ሴት ሲበዛ…’

0
515

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“ሴቶች ሲሰበሰቡ ስለምን ያወራሉ? ስለባሎቻቸው” በማለት ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጡ አሉ። “ያላገቡትስ?” ብቻ በጥቅሉ ጥናት የሚፈልግ ጥያቄ ነው። ብሒላችን እንደሆነ ‘ሴት ሲበዛ ጎመን ጠነዛ’ ነው የሚለው፤ ሴቶች በተሰበሰቡበት ሥራ የሚያስፈታ ወሬ እንጂ ቁም ነገር የሚባል ነገር እንደማይገኝ አድርጎ ይገልፃል። “ነገሩ እንደዛ ነው ወይ?” ምን አውቄ። ግን ሴቶች በበዙበት ተዓምር የሚፈጥር መላ ማምጣት ይቻል ነበር።

“እውነት ግን ሴቶች ስንሰበሰብ ስለምን እናወራለን?” የቱ ነው ርዕሳችን፡- ውበት? ወንዶች? አልባሳት? ኳስ? ፖለቲካ? ሥራ? በእርግጥ በዘመነ ዲሞክራሲ ያሻንን ብናወራስ ማን ገዶት። ነገሩን ግን ያነሳሁት ብሒሉን ለመፃረርና ለማስተካከል ጉዳዩን ቸል ማለት ጥሩ አይሆንም ከሚል ነው።

ሴቶች በተለያየ አጋጣሚ ለመሰባሰብ ዕድል ይገጥሞናል። በአንድ ጎን በበዓላት ሰበብ፤ በተጓዳኝ ሻይ ቡና ለማለትና ለመወያየት። በእነዚህ መሰባሰቦች ውስጥ መልካም የሐሳብ ልውውጥ ሁል ጊዜ አለ ለማለት ባልደፍርም፤ መሰባሰቡን ግን ለሐሳብ ልውውጥ በብዙ መጠቀም ይቻላል። ለአንዲት ሴት የከበደ ችግር ለሌላዋ ቀላል መውጫ ያለው ይሆናልኮ!
ነገር ግን ችግራችንን አውጥተን ከመመካከር ይልቅ መደባበቅና አንድ ጓደኛ መምረጥ ይቀናናል። ያም ብቻ አይደለም እንደ መገናኛ ዓውዱ ቢለያይም ስንሰባሰብ የባጥ የቆጡ ሲነሳ መፍትሔ ሊገኝበት የሚችለውን የጋራ ችግርና የየግል ጉዳያችንን እንዘነጋለን።

ይህን ያመጣው መፈራረድ፣ መተማማትና ፍራቻ ነው። በእርግጥ በችግሮቻቸው ዙሪያ አስፍተው የሚመካከሩ የሉም ማለት አይደለም። ሰብሰብ ሲሉ “ምን ይደረግ? ምን ይሠራ?” ወዘተ ብለው የሚመካከሩ አሉ። ይሔኔ በሴቶች በብዛት መሰባሰብ መላ ይገኛል እንጂ ጎመን አይጠነዛም።

ሴቶች በበዙበት ቤት አይዝረከረክም፤ ይደምቃል። ጓዳው ሙሉ…ቤት ፅዱ ነው። ተጋግዘው ለሠርግም ይሁን ለተዝካር፤ እልፍ እንግዳ የሚያስተናግድ ዝግጅት ያደርጋሉ። በትብብርና በመጠያየቅ ቅመማ ቅመም ተጨምሮበት ምግብ ቢሠሩ ይጣፍጥላቸዋል። በጋራ ቀምሰው አስተያየት ይሰጣሉ፤ በጋራ ይቋደሳሉ። ለደስታም ለችግርም ይጠራራሉ፤ ማኅበራዊ ኑሯችን ራሱ እንደዛ ሆኖ ተሠርቷል።

ይሔ የአብሮነት ጥበብ ለሕይወትና ለኑሮም ሊሠራ ይገባል። መደጋገፋና መመካከሩ ያለመተማማትና ያለመፈራረድ በግልፅ ቢሆን ያምራል። ስንበዛ ብዙ ሐሳብ የምናመጣ፤ መፍትሔ የምንፈጥር፣ መላ የምናገኝ ልንሆን ይገባል። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ስለአገር ሰላም ብለው በሴቶች ስብስብ የተደራጁ ማኅበራት ቅንጅት ፈጥረው ነበር። የሔዱበትን ርቀትና ያመጡትን ለውጥ ቆጥረን አልተረከብንም፤ ግን መቀናጀት እንደሚቻል አሳይተው ነበር። እና በአገር ደረጃም ይሁን በየጓዳችን ብሒሉም ሆነ ሰው የሚለውን ውድቅ ለማድረግ፤ በውጤት እናሳይ ለማለት ነው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here