የእርጅና ስሌት ቅናሽ መነሳቱ የመኪናን ዋጋ የበለጠ እንዳያንረው ተሰግቷል

0
671
  • 30 በመቶ የእርጅና ስሌት ቅናሽ ሙሉ በሙሉ እንዲቀር ተደርጓል

ወደ አገር ውስጥ በሚገቡት መኪናዎች ላይ የተመረቱበትን ዓመት ታሳቢ አድርጎ የሚነሳው የቀረጥ አወሳሰን እንዲቀር መደረጉ የመኪና ዋጋን እንዳያንረው ተፈርቷል። እስከ 30 በመቶ ድረስ የቀረጥ ቅናሽ ይደረግበት የነበረው የእርጅና ጊዜ ስሌት (depreciation) እንዲነሳ መደረጉ በአገር ውስጥ የሚሸጡ ያገለገሉ መኪኖች ዋጋ ያሻቅባል ተብሎ ይጠበቃል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ግንቦት 7/2011 ባወጣው መመሪያ መሰረት ማንኛውም ያገለገለ ዕቃ ተሽከርካሪን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ቀረጥና ታክሱን ለመወሰን ምንም ዓይነት የእርጅና ቅናሽ እንደማይደረግ አስታውቋል። የሚኒስቴሩን መመሪያ ተከትሎም በአዲስ አበባ በርካታ የመኪና መሸጫ ቤቶች የዋጋ ማስተካከያ ለማድረግ ሐሙስ፣ ግንቦት 15/2011 ሥራ ሳይሠሩ ዘግተው የዋሉ ሲሆን፤ ቀሪዎች ደግሞ ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ መኪና አስመጪው ናትናኤል ሀብቶም ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፥ “በየቀኑ ዋጋቸው እየጨመረ የመጡትን መኪኖች ጭራሽ ዋጋቸው እንዳይቀመስ ያደርገዋል” ይላል። በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም እስከ 250 ሺሕ ብር ቀረጥ ይከፈልባቸው የነበሩት በብዛት ከተማ ውስጥ የሚታዩት ቪትዝ መኪኖች አሁን ካሉበት ከ400 ሺሕ ወደ 550 ሺሕ ብር ከፍ ይላሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ለአዲስ ማለዳ ጨምረው ገልፀዋል። ናትናኤል “ከዚህ ቀደም የገቡት መኪናዎችም ቀረጥ ከተከፈለባቸው የቆዩ ቢሆኑም፤ የአሁኑን መመሪያ ተከትሎ በአስመጪዎች በኩል ጭማሪ ስለሚደረግባቸው የተጋነነ ዋጋ እንደሚወጣባቸው ይጠበቃል” ብለዋል።

“ጫናው ዞሮ ዞሮ ሕዝብ ላይ ነው” የሚሉት ናትናኤል ከመኪና በማስመጣት ሒደት ሰንሰለቱ ላይ ያሉ ባለድርሻዎችን ማለትም የጉምሩክ አስተላላፊዎችን፣ የኮሚሽን ሠራተኞችን እንደሚጎዳም አመላክተዋል።

ሌላው የአበባ ግደይ መኪና አስመጪ ባለቤት የሆኑት ብርሃነ ግደይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት “30 ከመቶ የቀረጥ ቅናሹ የሚነሳ ከሆነ በሥራችን ላይ የሚያመጣው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ፊታችንን ለማዞር እንገደዳለን” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በገቢዎች ሚኒስቴር የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ደግሞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ያገለገሉ መኪናዎች በማዳከም አዲስ መኪኖች እንዲገቡ ለማበረታታት እንደሆነ የተጠቆመ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ አዲስ የመኪና ማስመጣትን የማያበረታታ ፖሊሲም እንደሚኖራት ታውቋል። በዚህ አዲስ በሚወጣው ፖሊሲም መኪኖች የተመረቱበት ዕድሜ ገደብ የሚኖራቸው ሲሆን ከተመረቱ ዐሥር ዓመት የሆናቸው መኪኖች ወደ አገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ እንደሚደረግ ታውቋል።

ሐሙስ፣ ግንቦት 15/2011 በገንዘብ ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥም የታሪፍ መለያ መፅሐፉ ላይ በባለድርሻ አካላት ላይ ውይይት መደረጉ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here