በላይነህ ክንዴ የሰሊጥ ግብይት ለጊዜው ማቆማቸው ተሰማ

0
683
  • ኩባንያው የሰሊጥ የወጪ ንግድ 10 በመቶ የገበያ ድርሻ አለው

የኢትዮጵያን የሰሊጥ የወጪ ንግድ 10 በመቶ የገበያ ድርሻ ይዞ የሚገኘው በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ ኩባንያ ባለፉት ሳምንታት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ የናረው የሰሊጥ ዋጋ እሰኪረጋጋ ድረስ ግብይት ማቋረጡን የዓይን እማኞች ገለፁ። የድርጅቱ ተወካዮች በምርት ገበያው የመገበያያ መደብ ላይ ቢሰየሙም ግብይት እያካሔዱ አለመሆኑን ተገልጿል።

ሚያዝያ 9/2011 ነጭ የወለጋ ሰሊጥ 5 ሺሕ ብር አካባቢ እና ነጭ የሁመራ ሰሊጥ ደግሞ 5 ሺሕ 500 ብር የተሸጠ ሲሆን ከ12 ቀናት በኋላ በሚያዝያ 21 ነጭ የሁመራ ሰሊጥ 6 ሺሕ 158 ብር ሲሸጥ ነጭ የወለጋ ሰሊጥ ደግሞ በ 5ሺሕ 963 ብር ተሸጧል። በምርት ገበያው ሕግ መሰረት በቀን ካለፈው መሸጫ ዋጋ ላይ 5 በመቶ በመጨመር ያለማቋረጥ የናረው ዋጋ በሚያዝያ 28 የሁመራ ሰሊጥ 7 ሺሕ ብር ገደማ እና የወለጋ ሰሊጥ 6 ሺሕ 100 ብር አካባቢ ተገበያይቷል።

በዓለም ዐቀፍ ገበያ አንድ ቶን ሰሊጥ ከሚሸጥበት ዋጋ እስከ 700 የአሜሪካን ዶላር ድረስ በምርት ገበያው ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲደረግ የነበረው ግብይት ባለፈው ሳምንት የተወሰነ መቀነስ በማሳይት ላይ እንደሆነ ታውቋል። ይሁንና አሁንም ግብይቱ ጤናማ የሚባል ደረጃ ላይ ባለመድረሱ በላይነህ ክንዴ ከምርት ገበያው ሰሊጥ መግዛት አለመጀመራቸው ታወቋል።
ግንቦት 14 ነጭ የሁመራ ጎንደር ሰሊጥ በ6 ሺሕ 584 ብር ሲገበያይ የዋለ ሲሆን ነጭ የወለጋ ሰሊጥ ደግሞ በ6 ሺሕ 94 ብር ሲሸጥ ውሏል። ነገር ግን ነባር የሰሊጥ ላኪ ድርጅቶች ወደ ግብይቱ በሙሉ አቅማቸው መግባት እንዳልጀመሩ ታውቋል።
ወደ ምርት ገበያው የግብይት ስርዓት እየገቡ በሚገኙ አዳዲስ ተገበያዮች ዋጋውን በመስቀል የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት ተብሎ በሚደረገው ግብግብ ገበያው መረበሻቸውን ነባር ተገበያዮች ይገልፃሉ።

በላይነህ ክንዴም ዋጋው መጨመር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ጫናውን ተቋቁሞ ከወራት በፊት የተቀበሉትን ትዕዛዞች በኪሳራም ቢሆን ገዝቶ ሲልኩ የነበረ ሲሆን ዋጋው በመሰቀሉ ግን ግብይት እንዳቆሙ ታውቋል። ለአዲስ ማለዳ እህት መጽሔት ‘ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው’ የድርጅቱ የወጪ ንግድ ክፍል ኀላፊ የሆኑት ደረጄ አጥናፉ እንደገለፁት ድርጅቱ ለተከታታይ ሳምንታት ወደ ውጪ መላክ ማቆማቸውን ገልፀዋል።

ቀድሞ ውል የተገባላቸው ግዢዎች ፍላጎትን ለማሟላት ሲባል በቶን እስከ አንድ መቶ ዶላር እየከሰሩ ሲለኩ መቆታቸውን እና አሁን ያለው ኢምክንያታዊ ዋጋ ግን ለመቋቋም የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ ዋጋው እስኪረጋጋ ግን በቅርበት እየተከታተሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የሰሊጥ ንግድ ውስን ኩንታል ብዙ የውጪ ምንዛሬ ለማገኘት ማመቸቱ ለዋጋው መናር እንደምክንት ቢጠቀስም ለውጪ ገበያ ለማቅረብ በሚደረጉ የማበጠር እና የማጓጓዝ ሒደት ብዙ ብክነት በመኖሩ የትርፍ ኅዳጉን በመቀነስ ሥራውን አስቸጋሪ ያደርገዋል።

ድርጅቱ በቀጣይ ዓመት እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ የሰሊጥ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እየገነባ ሲሆን ዕሴት በመጨመር ለመላክ ማሰቡ ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here