የጀርመኑን ተራድኦ ሠራተኛ ፖሊስ መያዝ እንዳለቻለ አስታወቀ

0
579

በሐይማኖት አሸናፊ እና መሰረት አበጀ
ዓለም ዐቀፉ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት ጂ አይ ዜድ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሠራተኛ ሐሰተኛ ሰነድ በድርጅቱ ሥም በማዘጋጀት ያለአግባብ የቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም የተጠረጠረው ግለሰብ ፌደራል ፖሊስ ማግኘት እንዳልቻለ ማክሰኞ፣ ግንቦት 13 ለፍርድ ቤት ገለፀ። በሚያዚያ አጋማሽ ላይ አምስት ግለሰቦች 219 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ ቁሳቁሶች ያለውን ዓለም ዐቀፍ የዲፕሎማቲክ መብት በመጠቀም በድርጅቱ ሥም ዕቃዎችን በሐሰተኛ ሰነድ ወደ አገር ውስጥ ሊያስገቡ ሲሉ መያዛቸውን ጉመሩክ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።

በወቅቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል የድርጅቱ ሠራተኛ የሚገኝ ሲሆን በተጨማሪም የራይድ አስተላላፊ (ትራንዚተር) ባልደረቦችም አብረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። ጠርጣሪዎቹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢንተርናሽናል ካርጎ አገልግሎት ተቋማት የወጡ ሰነዶችን አስመስሎ የሐሰት ሰነድ በማዘጋጀት ተጠርጥረው ፖሊስ ምርመራውን እያከናወነ እንዳለ ለፍርድ ቤቱ ገለጿል።

ግምታቸው 52 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚሆን 349 ሺሕ 84 የተለያዩ የሞባይል ስክሪኖች፣ ግምታቸው 118 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚሆን 687 ካነን ካሜራዎች እና 20 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ 6 ሺሕ 734 የተለያዩ የመኪና መለዋወጫዎች ከተያዙት ዕቃዎች መካከል ይገኛሉ። በተጨማሪም ፕሮጀክተሮች፣ መድኀኒቶች፣ የብር ጌጣጌጦች እና ድሮኖች አብረው መገኘታቸውን ጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቆ ነበር።

ፖሊስ ምርመራውን ለማካሔድ ተጨማሪ 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን ኹለት አስተላላፊዎች እና አንድ የድርጅቱ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ጂ አይ ዜድ 410 ኪሎ ግራም ዕቃን የዲፕሎማቲክ መብትን በመጠቀም ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የተሰጠውን ሰነድ መነሻ በማድረግ 4 ሺሕ 100 ኪሎ ግራም ዕቃ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ እንደተፈቀደለት በማስመሰል ወደ አገር ውስጥ ዕቃው መግባቱን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለፆ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here