- ሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎችም በውሕደቱ ሊሳተፉ እንደሚችሉ ታውቋል – ኦነግን ገንጣይ ቡድን አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው ተብሏል
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና በዳኦድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ውሕደት ለመፍጠር ቅድመ ዝግጅት መጀመራቸውን አስታወቁ። ፓርቲዎቹ በኦሮሚያ ጉዳዮች፣ እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈንና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መሥማማታቸውን ገልጸዋል።
ከውሕደቱ በፊት ኦነግ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና እስኪያገኝ ድረስ እንደሚጠብቁ የኦፌኮ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎችም የውሕደቱ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው፥ ኹለቱ ፓርቲዎች የኦሮሞ ሕዝብ ድምፅ እንዳይከፋፈል በጋራ ለመሥራት መሥማማታቸውን አሳውቀዋል። የሥምምነታቸው መሠረትም የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን የኹለቱ አመራሮች ገልጸዋል።
የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ቶሌራ አዳባ፣ ከኦሮሞ ፓርቲዎች ጋር ውሕደት መፍጠሩ ያስፈለገበት ምክንያት፣ በአብዛኛው የፓርቲዎቹ መመሪያና ደንብ ተመሣሣይ በመሆኑ በውሕደት ለመሥራት በሚያስችሉን ጉዳዮች ላይ በመወያየት መግባባት ላይ ደርሰናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኦነግ ኦሮሚያን መግንጠል በሚለው ጥያቄ ላይ መልሥ የሰጡን ቶሌራ፥ “ማንኛውም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብት አለው ብለን እናምናለን፤ ሁሉም ሕዝብ ተከባብሮና ተሥማምቶ በጋራ መኖር እንዳለበትም ስንናገር ቆይተናል። ኢትዮጵያን መገንጠል የሚፈልግ ማንም የለም፤ ከዚህ ውጪ ኦነግን ገንጣይ ቡድን አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ከውሕደቱና ሌሎች ቀጣይ እንቅስቃሴዎች በፊት ኦነግ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ለማግኘት በሒደት ላይ መሆኑን የተናገሩት ቶሌራ፣ በቅርቡ ዕውቅና አግኝተው በዕቅዳቸው መሠረት መንቀሳቀስ እንደሚጀምሩ አክለው ገልጸዋል።
ኹለቱ ፓርቲዎች የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ ለመፍታትና ለአገር ሰላም በትጋት እንደሚሠሩ የተናገሩት ሙላቱ፣ በተናጠል የሚደረጉ ትግሎች ውጤታቸው አጥጋቢ እንዳልሆነና ለሕዝቡም መሠረታዊ ጥያቄዎች ጠንካራ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሚሆን አንስተው የተለያዩ ፓርቲዎች ጥምረት ግን ሁሉንም ችግሮች ለመፍታት ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ፓርቲዎቹ ሰፊ የሆነ የዓላማ ልዩነት የሌላቸው እንደመሆኑ በጋራ መቆማቸው ለሕዝቡም ጠቀሜታ እንዳለው ያወሱት ሙላት በቀጣይ በፓርቲዎቹ መካከል ጠንካራና ሰፊ ውይይት ተካሒዶ ለውሳኔ የሚተላለፍ እንደሚሆን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት ጥናቶችና የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፥ በቀጣይም አገር ዐቀፍ ምርጫ እየደረሰ እንደመሆኑ የተለያዩ ዕቅዶችን በማውጣት እየተንቀሳቀሱ ስለመሆኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ኦነግ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር በሰጠው መግለጫ ኦፌኮ ጋር ጥምረት ለመፍጠር ውይይት ማድረግ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 29 ግንቦት 17 2011



