የኢትዮጵያ ምሁራን ተልዕኮ ምንድን ነው?

0
862

ምሁር የሚለውን ቃል በአንድ ወጥ ብያኔ ማስቀመጥ በጣም አዳጋች መሆኑን በርዕሱ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍት ያመላክታሉ። መላኩ አዳል የኢትዮጵያን ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ምሁራዊ ኀላፊነት ለመወጣት አቅምም አላጎለበትም፤ በጎ ፈቃድም የላቸውም ሲሉ ምክንያታቸውን በመዘርዘር ሞግተዋል።
ምሁራን የተሳሳተ አካሔዳቸውንም ሆነ ከተሸበቡበት ወጥተው ለጋራ አገራዊ ግንባታ የአቅማቸውን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ይሞግታሉ።

የትምህርት ዋናው ዓላማ የአገርን ወግና ትውፊት፣ ባሕልና ታሪክ፤ በመመርመር መስተካከል ያለባቸውን እንዲስተካከሉ የሚያሰፈልገውን መንገድ የሚጠቁም፤ ጠንካራ ጎኖች ደግሞ የሚቀጥሉበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። የዘመናዊነት ማሳያ የሆኑትን የጥሩ ፖለቲካዊ አስተዳደር መንገዶችን፣ የውጭ ግንኙነትን፣ ሕግና ደንብን፣ የግል ነፃነትን፣ የመንግሥትና ሃይማኖት መለያየትን፣ የሐሳብ ብዛኀነትን፣ የፆታ እኩልነትን፣ የአገር ሀብትን እንዴት ማልማትና መጠቀም እንደሚቻል ማሳወቅንና ማጥናትን ያካትታል። በተጨምሪም በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተካነ፣ የአዲስ ሐሳቦችና የፈጠራ ባሕሉ ያደረገ ትውልድ መፍጠርንና ለቀጣይነት ማበረታታትን ያጠቃልላል። ይህም ማለት የትምህርት ዓላማ አንድ ኅብረተስብ የተሟላ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖረው፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ በመልካም ሥነ ምግባርና የሥነ ዜጋ እሴቶች የተገነባና በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ተፈላጊ ውጤት ማምጣት የሚችልና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ በአመክንዮ መኖር የሚችል ኅብረተሰብ መፍጠር ነው።

ዘመናዊነት የሰውን ልጅ ማዕከል ባደረጉ ዕውቀቶች የበለፀገና በፍልስፍና የተካነ የባሕል መሰረት ያለው ኅብረተስብን ይጠይቃል። በአገራችን የዘመናዊነት የትምህርት ስርዓት ከእኛነታችን ተለይቶ፣ የአገርን ወግና ትውፊት፣ ባሕልና ታሪክ፤ ከመመርመርና መስተካከል ያለባቸውን እንዲስተካከሉ ከማድረግ፣ ጠንካራ ጎኖች የሚቀጥሉበትን መንገድ ከማሳየት ወጥቶ ሁሉንም ማንነቶቻችን አራግፈን ትተን የምዕራባውያን ሥልጣኔ ብቻ ናፋቂዎች እንድንሆን አድርጎናል። በተለይም በሥነ ሰብዕ (‘ሁማኒቲ’) የትምህርት ዘርፎች (ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ሥነ ጽሑፍና ኪነ ጥበብ) የተደረገው ዘመቻ፣ እሱነቱን የማያውቅ፣ በሌሎቹ ሐሳብና ፈጠራ ብቻ የሚመራ፣ የራሱ የማሰቢያ መንገድ (ፍልስፍና) የሌለውና በአገሩ ጉዳይ ፊት ላይ ለመሆን የሚፈራ ትውልድ ፈጥሯል። ይህ ደግሞ የትምህርትን በራስ ላይ የባሕሪይ ለውጥ ማምጣትን፣ አሳቢ ኅብረተሰብን የመፍጠርን፣ በኅብረተስቡ ውስጥ ደካማ ባሕልና ልምድን በመተው፣ ጥሩ የሆኑትን የባሕልና የልምድ እሴቶቻችን ወደ ዘመናዊ የባሕል መሰረት በማዋሐድ ለሕዝብ ሥልጣኔና ለአገር ዕድገት ማዋልን አደናቅፏል።

የአፄ ኃይለሥላሴ የዘመናዊ ትምህርት ትውፊትንና ባሕልን እንዲያካትት ቢታሰብም የነበሩት መምህራን የውጭ በመሆናቸው በታለመለት መንገድ ሊጓዝ አልቻለም። በተጨማሪም ውጪ አገራት ተምረው የሚመለሱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከአገሪቱ ባሕልና ልምድ የራቁ ነበሩ። ይህም ምንም እንኳን የጠያቂነትን ባሕል ቢያጎለብትም የማንነት ጥያቄን ያልመለሰ እንዲያውም የምዕራቡ ዓለም ጥገኞች እንድንሆን አድረጎናል። የተማሩ ዜጎቻችንንም በኅብረተሰቡ ውስጥ ተሳትፎዋቸው እንዲቀንስ አድረጓል። ስለዚህም የአገርን ጉዳይና የአገር በቀል ዕውቀትን ያካተተ፣ ከራስ ማንነት የተነሳ የትምህርት ስርዓት መንደፍ ይጠበቅብናል።

ማንኛውም የትምህርት ስርዓትና ፖሊሲ የኅብረተሰቡን ችግር ነቅሶ አውጥቶ ለመፍትሔ የሚሠራ መሆን አለበት። በዝግጅት ጊዜ የአተገባበርን፤ ምዘናን፣ የሰው ኀይልና የመምህራን ጥራትን፣ የምርምር ልምድን፣ የገንዘብ አቅምን፣ ከተለያዩ የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስር፣ ተደራሽነትን ያገናዘ በመሆን አለበት። የትምህርት ስርዓታችን ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥኑ የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ መሆን አለበት። በተለይም የሒሳብ ትምህርት በማንኛውም ደረጃና ትምህርት ክፍል በተገቢ መልኩ መሰጠት ይኖርበታል። ይህም የሚያስፈልገውን ሳይንስና ቴክኖሎጂ በቀላሉ እንዲገባን ብሎም ፈጣሪዎች እንድንሆን ያግዘናል። የፖለቲካ ውሳኔ የሚጠይቁ የመማሪያ የቋንቋ፣ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት ዕርዳታ ስለተገኘ ብቻ የሚተገበሩ መርሃ ግብሮች፣ የመምህራን ነፃነትና የደሞዝ ሁኔታ፣ በየዩኒቨርሲቲዎቹ ለመምህሩ ጥቅም ብቻ ያለበቂ ሰው ኀይልና የአስፈላጊነት ጥናት የሚከፈቱ ፕሮግራሞች፣ የ70-30 ጉዳይ፤ ዩኒቨርሲቲዎች የሚከፈቱበት መስፈርት ፖለቲካ ወይስ አስፈላጊነት መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል። በተጨማሪም የትምህርት ሥርዓቱ በሙሉ አገሪቱ ከመተግበሩ በፊት የፓይለት (የሙከራ መተግበሪያ) ፕሮገራም ቢኖር ይመረጣል።

ምሁር በመማርም ሆነ በሕይወት ልምዱ የጨበጠውን ዕውቀትና የአዕምሮው ብቃት ተጠቅሞ ያለፉትን ዘመናት ታላላቅ ሐሳቦች እንደቅርስ የሚጠብቅ፣ አዲስ ሐሳብ ማመንጨትና ሐሳቦችን ለሌሎች ማካፈል የሚችል፣ ለሚሠሰራው ሥራ ታማኝ የሆነ፣ ያመነጨውን ሐሳብ የበርካቶች ሐሳብ እንዲሆን ያደረገና የአስተሳሰብና አመለካከት ለውጥ ያመጣ፣ የኅብረተሰቡን ፍላጎት የተረዳ፣ የወደፊቱን ካሉት ሁነቶች ተነስቶ መተንበይ የሚችል፣ እውነትን የሚፈልግ፣ ለዕውነት የሚቆምና የሚሟገት፣ ዕምነትና ግንዛቤ ሊገዛ የሚችል ኀይል የመሆን ብቃት ያገኘ፣ ጎጂውን ከጠቃሚው የለየ፣ ለተወሰነ ማኅበራዊ መደብ ብቻ ወግኖ የማይሠራ፣ እነዚህንም ክህሎቶችና ሐሳቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ማደረግ የቻለ ግለሰብ ወይም የብዙ ዘርፍ ሙያተኞች ስብስብ ማኅበረሰብ ነው።

ሐሳብ በአገር ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትልቅ ሚና አለው። አሳቢ ምሁራን የሌላት አገር የማደግ ዕድሏ የመነመነ ነው። ምክንያቱም ሐሳብ ለአመክንዮ መኖር፣ ለጥሩ ባሕል መዳበርና የሕይወት ፍልስፍና ግብዓት በመሆኑ ነው። የምሁራን ዋናው ተልዕኮም የኅብረተሰቡ ቃል አቀባዮችና ድምፅ በመሆን ነፃነቱን ማረጋገጥ፣ አንድነትና ልዩነትን አቻችሎ ማስኬድ፣ ዕውቀትንና ክህሎትን መፍጠርና ማሻሻል፣ ባሕልን መቅረጽ፣ ኋላ ቀር አስተሳሰቦችንና አሰራሮችንም መቃወምና እንዲስተካከሉም መንገዱን ማሳየት፣ ለሰፊው ኅብረተስብ ሐሳቦች እንዲደርሱ በትምህርት ተቋማት፣ በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በሌሎች መገናኛ ብዙኀንና ሌሎች ተቋማት በኩል ወደ ሕዝብ የዕውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲኖር ማደረግ መቻል ነው። ይህም የሚያሳየው በዕውቀትና በክህሎት የበለጸገና በጎ ፈቃድ ያለው ምሁር ኀላፊነት አዲስ ሐሳብና ዕውቀት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን ኅብረተስቡን ከማንነቱ፣ ከዕምነቱ፣ ከታሪኩ፣ ከባሕሉና ከልምዱ ተነስቶ ማንቃት፤ ኅብረተስቡም ያለውን ሐሳብ እንዲያወጣውም በመልካም አርዓያነትና ግልፅነት ማገዝ ነው። በተጨማሪም የመነጩ ሐሳቦች ሁሉ ጥሩ ሊሆኑ ስለማይችሉ ለሒስ ዝግጁ መሆን፣ የተገኙ አዲስ ሐሳቦች በሒስ ከታረቁና በውይይት ከአዳበሩ በኋላ ለአገር ግንባታ የሚውሉበትን መላ መፈልግ ነው።

በተጨማሪም ምሁራን ራሳቸው ተሳታፊ በመሆን ለአገር ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ መሪዎችን ከማፍራት በተጨማሪ የመሪነቱን እርከን በመጨበጥ ለአገር ዕድገት የራሳቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ምሁራን በወቅቱ አስተሳሰብና ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ተፅዕኖ የመውደቅ ዕድል ቢኖርባቸውም፤ በተቻለ መጠን ከታሪክ በመማር ከወቅታዊ ሁኔታ ወጥቶ የሩቁን ማየት የሚችሉ፣ ከግል ጥቅም ይልቅ ለኅብረተሰብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ መሆን አለባቸው።

የኢትዮጵያ ምሁራን ተልዕኮ ከቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ ልዩነት ይህንንም ተከትሎ ከሚመጣው ችግሮች መጠነኛ ልዩነት ውጭ፣ ከሁሉም የታዳጊ ዓለም ምሁራን የተለዩ አይደሉም። የኢትዮጵያ ምሁራን ግን የአገራቸውን ችግሮች ከመለየትና ከመፍታት ይልቅ፣ የችግሮች ምንጭ በመሆን ያላቸው ሚና ጎልቶ ይታያል። በአገራችን ለሚታዩ የታሪክ መጣረሶች፣ ለጥቅም መደለሎች፣ አምባገነን መንግሥታትን በመደገፍ፣ በምን አገባኝ ባይነትና የዘር ፖለቲካ በማቀንቀን ከችግር ፈችነት ይልቅ ችግር ፈጣሪዎች ሆነዋል። ይህም የሚያሳየው በምንማረው ትምህርት ጥራት ችግር ምክንያት የተማሩ የተባሉት ዜጎች አገሪቱ ያለባትን በርካታና ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ችግሮችዋን ከመፍታት አኳያ የሚፈለገውን አቅም አልገነቡም ወይም በጎፈቃድ የሌላቸው መሆኑን ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ መደበላለቅና መቀራረቡ ቢኖርም ወደ ፍፁም ውሕደትና ዜጋዊ ብሔርተኝነት እንዲያመራ የሚያደርጉ ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ባለመሟላታቸው የተነሳ ዛሬም ለእውነተኛው የሕዝቦች ውሕደት መጣር ያለባት አገር ሆናለች። ምሁራኖቿም ይህን ዜጋዊ ብሔርተኝነት ከመገንባት ይልቅ ረዥም በሆነው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተቃርኖ የበዛበት የታሪክ አረዳድና ብሔርተኝነት እንዲሰፍን በማደርግ፣ ባሕልና ዕሴቶቻችንን በመግፋት፣ በአገሪቱ ውስጥ የነበረውን የመደብ ጭቆና ወደ ጎን በመግፋትና ያልነበረ የጨቋኝ ተጨቋኝ የብሔር ፖለቲካ በማቀንቀን አንድ ወጥ የጋራ ርዕዮት እንዳይኖረን፣ ለአንድ አገራዊ ዓላማ እንዳንነሳ፣ ለደኅንነታችንና ሰላማችን መደፍረስ፣ ለአገር አንድነት መሰናክልና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተግዳሮት ሆነዋል።

ስለዚህም ምሁራኖቻችን ከዘር ብሔርተኝነትና ባላንጣነት ወጥተው፣ ተደማምጠው፣ ተደራደረው፣ በልዩነታቸው ተከባብረው፣ የጋራ ብሔራዊ ተልዕኮና ርዕዮት ሊቀረጹ፣ ኅብረተሰቡንም ዲሞክራሲያዊ የመፍትሔ ሐሳቦች አስታጥቀው ሊያደረጁትና ሊመሩት ይገባል። የእንትና ብሔር ምሁራን ተሰበሰቡ እየተባሉለ ፖለቲካ ፍጆታ ከመዋል ወጥተው፣ ለጋራ አገራዊ ግንባታ አቅማቸውን ማዋል ይጠበቅባቸዋል። በተለይም መመስረት ያለበት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሕዝቦችን ዜግነት ከግንዛቤ ያስገባና የሁሉንም ብሔረሰቦች አባላት የሆኑትን ኢትዮጵያ ዜጎች እኩልነት የሚያስከብር እንዲሆን በጋራ መሥራት አለባቸው።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here