የግንቦት 20 በዓል ‘ይከበር፣ አይከበር’ ንትርክ

0
471

ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በከፍተኛ ደረጃ ቃላት ያሰናዘረው የግንቦት 20 መከበር ‘ይገባዋል፣ አይገባውም’ የሚለው ተቃርኖዊ ሙግት ነበር።

መከበር የለበትም ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ ከነበሩት መካከል፣ ግንቦት 20 የድል ቀን ሆኖ ለመከበር ሁሉንም ያካተተ የደስታ ቀን መሆን ይገባዋል በማለት ባሏን ያጣች ሚስት፣ አባቱን ያጣ ልጅ፣ ወንድሟን ያጣች እህት፣ ልጇን ያጣች እናት እና ልጁን ያጣ አባት ባለበት ሁኔታ እንዴት የሁሉም በዓል ሊሆን ይገባል ሲሉ ይጠይቃሉ። በተጨማሪም ግንቦት 20 ከአንደኛው አምባገነን አገዛዝ ወደ ሌላኛው የተሸጋገርንበት በመሆኑ ማክበሩ ፋይዳ ቢስ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፤ መስከረም 2 በተሻረበት አግባብ ሊሻር ይገባዋል ሲሉም ሞግተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መከበር አለበት የሚሉት ወገኖች፣ ቀኑ አምባገነኑ የደርግ መንግሥት የተገረሰሰበት ከመሆኑም ባሻገር ዴሞክረሲያዊ ሕገ መንግሥት እንዲኖር፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብቶች የተከበሩበት እና እራሳቸው በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በር የከፈተ ቀን በመሆኑ ዕወቅና አለመስጠት ንፉግነት ብቻ ሳይሆን ታሪክን እንደመካድ ቆጠራል ሲሉ ተከራክረዋል።

ግንቦት 20 በአገር ዐቀፍ ደረጃ እንደከዚህ ቀደሙ ትኩረት ተሰጥቶት በድምቀት የተከበረው በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ይመስላል። አክሱም ላይ በተከበረበት የዘንድሮው ግንቦት 20, በየዓመቱ ደማቅነቱን ሳይለቅ በየተራ በተለያዩ ከተሞች እንደሚከበር የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ‘እኔም አለኝ ቁስል፤ ያንተን የሚመስል’ በሚል ርዕስ ባስተላለፉት ኹለቱንም ወገኖች በማያስቀይም ጥንቃቄ በተሞላበት መልዕክት፣ ቀኑ ኢትዮጵያ በታሪኳ ካለፈችባቸው ዐበይት የታሪክ ምዕራፎች አንዱ ነው ብለዋል። ያለፉት ዘመናት ቁስል ይብቃን፤ መድኀኒቱንም በጋራ እንፈልግ በማለት እርስ በርሳችን ቁስላችንን እየነካካን እንዳያገረሽና እንዳይድን አናድርገው ሲሉ መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here