የምርጫ ፖለቲካ ባሕላችን

0
788

የኢትየጵያን ምርጫ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እስከ 2007 ምርጫ የወፍ በረር ቅኝት ያደረጉት አበበ አሳመረ፥ ምንም እንኳን ከምርጫ ልምምዳችን አንፃር በአግባቡ አልተጠቀምንም ቢሉም፣ መጪው ምርጫን የተሳካ ለማድረግ የሁሉም አካላት በተለይም የምሁራን ተሳትፎ ላቅ ያለ መሆን ይገባዋል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

በማንኛውም አገር የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሕዝብ መሪውን ወደ ሥልጣን ለማምጣት የሚያደርገው ምርጫ መሠረታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኖ ኖሯል። ይህም የፖለቲካ ጉዳይ የምርጫ ፖለቲካ (electoral politics) በመባል ይጠራል። በዚህ የምርጫ ፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ከዋናዎቹ ተዋናዮች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት ምርጫና የፓርቲ ፖለቲካ እጅግ በጣም የተቆራኙ ጉዳዮች ናቸው። ምርጫ በሌለበት የፓርቲ ፖለቲካ ብዙም ትርጉም የለውም። ይሁን እንጂ እነዚህ ጉዳዮች በቀላል ቋንቋ ተገልጸው የሚታለፉ አይደሉም። የግንኙነታቸውን ባሕርይና ይዘት እንደየአገሮች የፖለቲካ ባሕል፣ የዴምክራሲ ልምድና ትግበራ በጣም ውስብስብ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በንጉሡ ዘመን መጨረሻ ገደማ ለተወሰነ ጊዜ የፓርላማ እንደራሴዎች ምርጫ በግል ውድድር የነበረ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲ ግን በሕግ አይታወቅም ነበር። በእንደራሴዎች ምርጫ ላይ የተሳተፉ ሰዎች እንደሚናገሩት ግን ምርጫው በተወዳዳሪዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር የተደረገበት አጋጣሚ እንደነበርና እንደራሴዎቹም ለሕዝቡ ቃል የገቡትን ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርጉና ቃላቸውን ማሳካት የቻሉም እንደነበሩ ይናገራሉ። የዚህ ጽሑፍ አሰናጅ አባት በንጉሡ ጊዜ በጉለሌ የነበረውን የእንደራሴዎች ምርጫ በተመለከተ የተወዳዳሪዎች ምልክት ምን እንደነበርና በየጠጅ ቤቱ ይደረግ ስለነበረው የምርጫ ቅስቀሳና ስለግብዣው፣ ወዘተ. ጭምር ለጸሐፊው ትውስታቸውን አካፍለውታል። ስለሆነም ይህ የእንደራሴዎች ምርጫ ወደ ዳበረ የምርጫ ፖለቲካ ባሕልነት በተለይም ወደ መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሳያድግ በ1966 በተከሰተው አብዮት የተነሳ ተጨናግፎ ቀረ። እንደራሴዎቹ የሚያነሷቸውና የምረጡኝ ዘመቻ የሚያደርጉባቸው አጀንዳዎች በአብዛኛው የምርጫ ክልላቸውን የሚመለከቱ ችግሮች ስለነበሩ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣቸው ነበር። ከምርጫ መሠረታዊ ዓላማ አንፃር ትክክል ነበር። የፓርቲ ፕሮግራም ይዘው ባይወዳደሩም ቢያንስ ይህን እናደርግልሃለን በማለት ለመራጩ ቃል የሚገቡበት ጉዳዮች ነበሯቸው።

የ1966ቱ አብዮት ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረቱ ሶሻሊዝም በመሆኑ የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ጉዳይ የሚታሰብ አልነበረም። በዚህ የተነሳ የነበሩት ፓርቲዎች ፕሮግራማቸው የተመሠረተው በሶሻሊዛም ቅኝት ላይ ሲሆን ፓርቲዎች ለምርጫ ፉክክር ሳይበቁ እርስ በርሳቸው በነበረው ሽኩቻ የተነሳ ተበላልተው በመጨረሻ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ብቻ ሕጋዊ መሠረት ያለው ሆኖ አገሪቱን ሲያስተዳድር ቆይቶ በ1983 እሱም ከሰመ። ስለሆነም በወቅቱ በተለይም በአብዮቱ የመጀመርያዎቹ ዓመታት የወጣቱንና የምሁራኑን ቀልብ ስበው የነበሩት እንደ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል (ኢጭአት) ወዘተ. የመሳሰሉት ፓርቲዎች ቀስ በቀስ የተዳከሙ ሲሆን አንዳንዶቹ ለምሳሌ ኢሕአፓ በአገር ውስጥ በኅቡዕና በውጭ አገር ደግሞ በግልጽ አለው ሲል ቆይቶ በቅርቡ አመራሮቹ ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ችለዋል።

ኢሕአዴግ የሥልጣን መንበሩን ከተቆጣጠረበት ከ1983 በኋላ ኢትዮጵያ በግልጽ የመድብለ ፓርቲ የምርጫ ስርዓትን እንደምትከተል ያወጀች ሲሆን በ1987 የወጣው ሕገ መንግሥትም የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሳዊ ምርጫ የሥልጣን መያዣ መሠረት እንደሆነ ዕውቅና ሰጠ። በዚህ መሠረትም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዲኖረው ተደረገ። ይህንኑ ተከትሎ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሕጉን መሠረት በማድረግ ተቋቁመው በምርጫ ውድድርም ተሳትፈው ሥልጣን ለመያዝ የሞከሩ ቢሆንም ምርጫውና የፓርቲ ፖለቲካው ሁሌም በችግር የተተበተበ ሆኖ በመቆየቱ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በዚህ የተነሳ በምርጫ ሰሞን ከሚታየው ግርግር ያለፈ የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ የምርጫ ውጤት ሳያይ ቆይቷል።

ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ሆነ ብሎ የማጨንገፍ እኩይ ሥራ በገዢው ፓርቲ በኢሕአዴግ ሲከናወን የኖረ ለመሆኑ በርካቶች ሲጽፉና ሲናገሩ የኖሩበት ሐቅ ሲሆን፥ ኢሕአዴግ ግን ሲያስተባብለው ነበር። በዚህ የተንኮል ሥራ የተነሳ በመጠኑም ቢሆን ሊያድግ የሚችል ዲሞክራሲያዊነት የታየበት በ1997 የተካሔደው ምርጫ ነበር። በዚህ ምርጫ ወቅት ከ140 በላይ የተቃዋሚ መቀመጫ የነበረው ፓርላማ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሽቆልቁሎ በተከታዮቹ ምርጫዎች ኢሕአዴግ ብቻ ወደ ተቆጣጠረው የፓርላማ ወንበር መቀየሩ ኢሕአዴግ ፍፁም በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደማያምንና ሥልጣኑን በምርጫ ላሸነፈው ወገን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ አረጋገጧል። በዚህ የተነሳ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እያደገ የሚመጣና የተደላደለ የፖለቲካ ባሕል እየሆነ ሊሔድ የሚችልበት ዕድል እንደሌለ ሁሉም በውስጡ አመነ።

በመሆኑም አስቀድመው ተስፋ አድርገው የነበሩት አብዛኞቹ ተስፋ ቆርጠው ገዢውን ፓርቲ በተለያየ ትግል ዘዴ ለማንበርከክ በመወሰን አዲስ የትግል ምዕራፍ ውስጥ ገቡ። ከ2007 ጀምሮ በእነዚህ ኀይሎች በሁለንተናዊ መልኩ የተከፈተ ትግል ኢሕአዴግን ከማራከስና ከማብጠልጠል አንስቶ በየቦታው የሚደረገውን ሕዝባዊ አመፅ ኢሕአዴግን አብረክራኪ ብቻ ሳይሆን ቁጭ ብሎ ለሕዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት አስገደደው። በዚህም የተነሳ ጥፋቱን እንዲያምን ከመገደድ በተጨማሪ በግልጽ ሕዝቡን ይቅርታ ጠየቀ። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ይህ አዲስ ክስተት ነበር።

ኢሕአዴግ በውስጡ የተፈጠሩት የለውጥ ኀይሎችም ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደረጉ መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ የተነሳ ለዓይን የተጠሉት የቀድሞው አመራሮች ገለል እንዲሉ የተደረጉ ሲሆን ለዚህ ሁሉ መዘዝ መነሻ የሆነው በምርጫ የመቀለድ አባዜም ከዚህ በኋላ ሊቀጥል እንደማይችል መተማማን ላይ ያደረሳቸው ይመስላል። በመሆኑም የምርጫ ዲሞከራሲን በተመለከተ የበፊቱ የኢሕአዴግ መሰሪ ሥራዎች ሊደገሙ በማይችሉበት ሁኔታ መጪውን ምርጫ ደረጃውን የጠበቀና ውጤቱንም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ በይፋ ተጀምሯል።

ብዙዎች ፍፁም አይሳካም የሚሉበትና በዛው ልክም ብዙዎች ይሳካል ብለው ተስፋ የሚያደርጉበት ቀጣዩ ምርጫ, በእርግጥም እኛ ብቻ ሳንሆን የዓለም ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው መሆኑ አያነጋግርም። ስለሆነም ከተሳካ የትንሣኤያችን መጀመርያ ሲሆን ካልተሳካ ደግሞ ምናልባትም እስከዛሬ ከነበሩት ውድቀቶች ሁሉ የከፋ ነገር ሊገጠመን ይችላል። በእኔ እምነት ግን ይሳካል የሚል ተስፋ አለኝ።

እንዲሳካ ሁላችንም የሚጠበቅብንን አበርክቶት ሁሉ ማድረግ አለብን። በዚህም መሠረት የፓርቲ ፖለቲካ ባሕላችንን፣ የምሁራን ዝምታን፣ የፖለቲካ ተሳትፎ ሸሽትን፣ “ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ ነው” ከሚለው አስተሳሰብ አንስቶ ለፖለቲካና ፖለቲከኛ መጥፎ አመለካከት የመያዝን የፖለቲካ ባሕላችን መቀየር ያስፈልጋል። ዛሬ በሁሉም ነገር የምንቀናባቸው የምጣኔ ሀብታዊ ብልፅግና ማማ ላይ ያሉትና በዴሞክራሲያዊ ባሕላቸው የዳበሩ አገራት እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱት በእውነተኛ ምሁራኖቻቸው እውነተኛ የፖለቲካ ተሳትፎና ከፍተኛ አበርክቶዎች አማካኝነት ነው።

ኢትዮጵያ በርካታ የለውጥ ዕድሎችና ተስፋዎች ሲመክኑባት የኖረች አገር ነች። ታዋቂው የምጣኔ ሀብት ሊቅ የነበሩት እሸቱ ጮሌ (ዶ/ር) እንደሚሉት አገራችን ሁሌም ተስፋ ወደ ቅዠት የሚለወጥባት አገር መሆንዋ ሁላችንንም ሲያስቆጨንና ከንፈር ሲያስመጥጠን ኖሯል። በዚህ የተነሳ ሁላችንም በተሰበረ መንፈስ መኖርን ብቻ ሳይሆን ምንም የተሻለ ነገር አይመጣም፣ ኢትዮጵያ ያልታደለች አገር ነች የሚለውን አስተሳሰብ ከአጥንትና ደማችን ጋር አዋሕደን ቁጭ ብለናል። የሚለወጥ ነገር ካለ በሚልም በሌሎች መስዋዕትነት ላይ ተስፋ ጥለን መጠበቅን የመረጥን ይመስላል። ይህ ግን ትክክል አይደለም። ለመጪው ምርጫ አዎንታዊ አበርክቶት ለማድረግ ከዚህ ስሜትና እምነት መውጣት የግድ ነው። ይህንን በፍጥነትና በትጋት ማድረግ የተሻለ ውጤታማ ያደርጋል።

አበበ አሳመረ የሕግ አማካሪና ጠበቃ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው aasamere@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here