ግንቦት እና ኢትዮጵያ

0
1623

እንደ መንደርደሪያ
ግንቦት በሞቃታማው በጋ እና በክረምቱ መካከል የሚገኝ የሙቀትና የወበቅ ወር ነው። ይህ ወር አየር ንብረቱ በቅጡ የማይታወቅ፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ የሚፈራረቅበት እንደመሆኑ ለሰዎች ጤና ተስማሚ አለመሆኑን የሚናገሩት የታሪክ ጽሁፎችን በትዊተር ገጻቸው በማስፈር የሚታወቁት ጌታቸው ሺፈራው፣ ‘ግንቦትና ግንቦታውያን’ በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጽሑፍ፣ ሙቀትና ቅዝቀዜው ድብልቅልቅ ባለበት በዚህ ወር አብዛኛው አርሶ አደር በበሽታ ይጠቃል። በዝናብ እጥረትና በረዥሙ በጋ ምክንያት ከብቶቻቸው ያልቃሉ። በአጠቃላይ ግንቦት ለአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የመከራ፣ የስቃይና ቁጣ ወር ነው ሲሉ አስፍረዋል። ሜጀር ጀነራል አመኃ ደስታ ’ግንቦትና የኢትዮጵያ እርምጃ’ በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ጽሑፍ ላይ ግንቦት በገደቢስነት በመፈረጁ በተለይ በመሃል ሀገር ጋብቻ የማይፈጸምበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ግንቦት በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ወር ነው። ኢትዮጵያ በግንቦት ወር ታዋቂ ልጆቿን ወልዳለች፤ ወደማይቀረው ዓለምም ሸኝታለች፤ መሪዎቿን ወደ ሥልጣን አምጥታለች፤ ከሥልጣናቸው ሽራለች፤ አስከፊ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፤ ከነዚህ ታሪካዊ ክስተቶች በተጨማሪ ግንቦት ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት ወርም ነው። ታዲያ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ልዩ ቁርኝት ያለውን ግንቦት ከመሰናበታችን በፊት ወሩ ካስተናገደቻቸው ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ በአጭሩ ለመቃኘት እንሞክር።

ግንቦት እና ልደት
የግንቦት ወር በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ አለው ይለናል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ‘ስንክሳር’ መጽሐፍ ምክንያቱ ደግሞ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት የሆነችው ቅድስት ማርያም በወሩ መጀመሪያ ግንቦት 1 መወለዷን ተከትሎ ነው። በሮም ነገስታትም ዘንድ አማልክቶቻቸው እነዜዩስ መስዋዕት ይቀርብላቸው የነበረው በዚህ ወር እንደነበር ‘ዘ ባቢለን ፎለን’ የሚለው መጽሐፍ ያትታል፤ የግሪኮቹ ማርዱክና፣ የግብጻውያኑ ሲን፣ ሻማሽና ኢሽታር የተሰኙ አማልክቶችም በዚህ ወር የልደት በዓላቸው ተሰይሞ ተዘክረዋል። ወሩ የቁጣ ወር የሆነበትም አንዱ ምክንያት ይህ መሆኑንም አስነብቧል።

የገናናው የሸዋ ንጉሥ፣ የንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የልጅ ልጅ፣ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የአክስት ልጅ፣ እንዲሁም የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አባት የሆኑት ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል የተወለዱት በግንቦት የመጀመሪያው ቀን በ1844 እንደነበር ተክለጻዲቅ መኩሪያ ‘የኢትዮጵያ ታሪክ’ በሚለው መጸሐፋቸው አስነብበዋል።

ጳውሎስ ኞኞ ‘አጼ ሚኒልክ’ በሚለው መጻሕፉ የውጫሌ ውል ያስከተለው የትርጉም ለውጥ መፍትሔው ጦርነት ሲሆን ልዑል ራስ መኮንን ሠራዊታቸውን ይዘው ከአምባላጌ እስከ አድዋ በተደረጉት ውጊያዎች ላይ በመሳተፍ ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል። ከቤተ መንግሥት ባለሟልነት ጀምረው በወታደርነት፣ በጦር መሪነት፣ በግዛት አስተዳዳሪነትና በዲፕሎማትነት በፈጸሟቸው አኩሪ ተግባራት ምክንያት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የዙፋናቸው ወራሽ ሊያደርጓቸው ያስቡ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። እኚህ ታላቅ የአገር ባለውለታ የግንቦት ትሩፋት መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት መስክረዋል።
በግንቦት ወር መፈንቅለ መንግሥት የተሞከረባቸውና በግንቦት ወር አገር ጥለው የሔዱት የደርግ ሊቀመንበር ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ እንዲሁም በሳቸው ምትክ በትረ ሥልጣኑን የያዙት መለስ ዜናዊም የተወለዱት በግንቦት ወር ነው።
መንግስቱ የተወለዱት፣ ወታደሩን የተቀላቀሉት፣ የመግደል ሙከራ የተደረገባቸው፣ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገባቸው፣ በርካታ ጀነራሎቻቸውን ያስገደሉት እና አገር ጥለው የወጡ በግንቦት ወር መሆኑ ግርምት ያጭራል። በመንግሥቱ እግር የተተኩት መለስ ዜናዊም የተወለዱት፣ ሥልጣነ መንበር የተቆናጠጡት፣ ከኤርትራ ጋር የተደረውን ጦርነት ያወጁበት፣ ምርጫ 1997 ቀልብሰዋል የሚባሉበትእንዲሁም የቀድሞው ቅንጅትን አመራሮችን በማሰርና በይቅርታ እንዲወጡ ያደረጉት በዚሁ ጥቅምት ወር ነበረ።

ግንቦት እና ሞት
ገናናውና መናኙ የታላቋ አክሱም ንጉሥ አፄ ካሌብ ያረፉት በግንቦት ወር በ20ኛው ቀን እንደነበር ‘ታሪከ ነገስት’ በሚለው መጽሐፋቸው የተነተኑት ደሴ ቀለብ (መምህር)፣ አፄ ካሌብ ከአክሱምና አካባቢው አልፈው ቀይ ባሕርን ተሻግረው የደቡብ አረቢያ ሕዝቦችን ያስገበሩ ታላቅ ንጉሥ እንደነበሩና፣ ከአይሁዳዊው ንጉሥ ፊንሐስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት በድል ካጠናቀቁ በኋላም አባ ጰንጠሌዎን ገዳም ገብተው እንደመነኑ ጽፈዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ሥማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱት እንስቶች መካከል አንዷ የሆኑት እቴጌ ምንትዋብ ያረፉትም በግንቦት ወር ነው። የአፄ በካፋ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ምንትዋብ፣ ጎንደር የኢትዮጵያ ነገሥታት ማዕከል በነበረችበት ወቅት የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደነበር ታሪክ ጸሐፊው ተክለጻዲቅ መኩሪያ አስነብበውናል። ባለቤታቸው አፄ በካፋ ከሞቱ በኋላ በተከታታይ በነገሡት በልጃቸው ዳግማዊ አፄ ኢያሱ እንዲሁም በአፄ ኢዮአስ ዘመነ መንግሥታት ትልቅ ሚና ነበራቸው። ከፖለቲካ ተሳትፏቸው በተጨማሪም ዛሬ ድረስ በበርካታ ጎብኚዎች የሚጎበኙ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል። ከዚሁ ከመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ሳንወጣ አፄ ሠይፈአርዕድ እና አፄ እስክንድር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በግንቦት ወር መሆኑን በታሪከ ተመዝግቧል።

የኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ስዩም አለማየሁ (ዶ/ር) ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ባለቤት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ በግንቦት ወር 1860 ማረፋቸውን ይጠቅሳሉ፤ እቴጌዋ ያረፉትም ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ከልጃቸው ከልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ጋር ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ እንደሆነ በታሪክ መዘገቡንም አስታውሰዋል።

አንጋፋውና ዝነኛው ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ይቺን ዓለም በሞት የተለያት ግንቦት 29/1984 መሆኑን ዜና እረፍቱ ይናገራል። የጳውሎስ ኞኞ ሥም ሲነሳ ወደ አብዛኛው ሰው አዕምሮ የሚመጣው በቀለም ትምህርት ብዙም ሳይገፋ, በድፍን ኢትዮጵያ ዝነኛና ተወዳጅ ለመሆን ያበቃው የጋዜጠኝነት ሥራው ነው። በዘመናዊ ትምህርት አራተኛ ክፍልን ያልተሻገረው ጳውሎስ፣ በተፈጥሮ የታደለው የማንበብ፣ የመጠየቅና የመመራመር ተሰጥኦ በጋዜጠኝነት ሙያው አንቱታን አትርፎለታል። በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እንዲሁም በኢትዮጵያ ራዲዮ ሲሰራ “ጋዜጠኝነትስ እንደጳውሎስ!” የተባለለት ይህ ሰው፣ በርካታ መጽሐፍትንና ቲአትሮችንም ለአንባቢያን አበርክቷል። «ሁሉን እወቅ፤ የሚሆንህን ያዝ» የሚለው የሐዋርያው ጳውሎስ መልዕክት በውስጡ እንደሰረጸ ይናገር የነበረው ጳውሎስ, መንገድ ላይ ወድቃ የሚያገኛትን ቁራጭ ወረቀት ሁሉ በንበብ ልማዱና ከአማርኛ በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎችንም ይናገርና ይጽፍ እንደነበረ ግለ ታሪኩ ያመላክታል።

ጳውሎስ የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር በተባ ብዕሩ ሞግቷል። ይህ ተጋድሎውም ለማስፈራሪያ፣ ለዛቻና ለእንግልት ዳርጎታል። ጳውሎስ ጋዜጠኛ ብቻ አይደለም፤ ብዙ የሙያ ዓይነቶችን ከባለሙያዎቹ ባላነሰ መልኩ ይከውን ነበር ይባላል። ግልፅነት፣ ድፍረት፣ ለወገን ደራሽነትና ጨዋነትም የጳውሎስ መገለጫዎች እንደነበሩ ብዙዎች ምስክር ናቸው።
«የፊደል ገበታ አባት» በመባል የሚታወቁት ተሥፋ ገብረሥላሴ (ቀኛዝማች) ግንቦት 26/1992 የእስትንፋሳቸው መጨረሻ ቀን ነበረ።

ግንቦት እና ሹም ሽር
ሄኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ) ግንቦት 17/2010 ‹‹ግንቦት በታሪካችን ምዕራፍ›› በሚል በድሬቲዩብ ባቀረበው ጽሑፍ፣ ታሪክ ከግንቦት ጋር የተለየ ነገር አለው እንድንል የሚያደርገን ግንቦት የንግሥናም ወር በመሆኑ እንደሆነ ገልጾ፣ ግንቦት ቤተ መንግስት የገባው ኢሕአዴግ ብቻ አይደለም ሲል ተንትኗል፣ ለምሳሌ ዐጼ ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወራሻቸው ልጅ ኢያሱ መሆኑን የገለጹት ግንቦት 10/1901 እንደነበር ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፉ ጠቅሷል። የንጉሥ ሚካኤል ታሪክ ደግሞ በዚሁ ግንቦት 1906 ንጉሠ ወሎ ወ ትግሬ ተደርገው መንገሳቸውን ይነግረናል። ዳግማዊ አምደ ጽዮን የነገሡትም ግንቦት 13/1487 ነበር።
በ1788 ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ አራተኛ ሥልጣን ለቀዋል። በኹለተኛው ዓመት ግንቦት 1790 በዚሁ ስም የሚጠሩት አምስተኛው ዐጼ ተክለ ጊዮርጊስ የሥልጣናቸው ፍጻሜ ሆነ። በ1810 ግንቦት ዐፄ እጓለ ግዛታቸው መፈጸሙን ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌስር) በ‘ባሕረ ሐሳብ’ መጽሐፋቸው ይነግሩናል። ዳግማዊ ኢዮአስ የተባሉት ንጉስ ግዛት በ1813 ተፈጽሟል።

ግንቦት እና ጦርነት
የደጋው ክርስቲያን እና ኢማም አሕመድ ጦርነቶች የከፉት ግንቦት 1531 እንደነበር ለአዲስ ማለዳ ያስታወሱት የታሪክ መምህሩ ስዩም, የሸዋና የጎጃም ጦር ያለ አግባብ እምባቦ ላይ የተዋጋው ግንቦት 1874 እንደሆነ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል ብለዋል።
በታሪክ ድርሳናት እንደሰፈረው ደም አፋሳሽ ጦርነቶች የታዩበት ግንቦት, የንጉሥ ምኒልክ (በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ) እና የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር እምባቦ ላይ ከባድ ውጊያ አድርጓል። የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የደብረ ሊባኖስ ገዳምን ዘርፎ መነኮሳቱን በግፍ የጨፈጨፈውም በግንቦት ወር ነበር።

ግንቦት በታሪካችን ያልተለመዱ ክስተቶችን ያስተናገደ ወር እንደሆነ ለማየት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በጻፉት ‘ባሕረ ሐሳብ’ ላይ ግንቦት 25/በ1788 አመድ መዝነቡን ማየት ብቻ ይበቃል። ግንቦት አፄ ሱሲኒዮስ በወደቁበት የካቶሊክ ፍቅር አንወድቅም ያሉ የወግዳ መነኮሳት የተገደሉበት፣ የጣሊያን ሠራዊት ደብረ ሊባኖስን ዘርፎ መነኮሳትን ያረደበት፣ በአመዴ ልጅ ሊበን እነዞርአምባ እና ሳጋ ገዳማት የተቃጠሉበት ወር ነው።
ግንቦት 4/1990 ኢትዮጵያ በሻዕቢያ ተወረረች። በኹለቱ ግለሰቦች፣ ፓርቲዎች ኢኮኖሚያዊና ድሮ በርሃ በነበሩበት ወቅት በተፈጠረ ቁርሾ ከ70 ሺሕ በላይ ሰዎች (አንዳንዶች 100 ሺሕ ያደርሱታል) በወርሃ ግንቦት በተፈጠረ ግጭት ሰበብ ውድ ሕይወቱን አጣ።

ግንቦት እና መፈንቅለ መንግሥት
በቀረብኝ ኖሮ ለምን በላሁት
አያበቅለው የለ ሰኔና ግንቦት
የግንቦቱ ባሰ አረም በዝቶበት
(ምንጭ)

ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ፣ (‘አብዮቱና ትዝታዬ’፣ ገጽ-463) በሚለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት ማክሰኞ፣ ግንቦት 8/1981 የአገሪቱ ምርጥ ጄኔራሎች እርስ በእርስ ጦርነት እየተሠቃየች ላለች አገራቸው መፍትሔ ያሉትን የሚተገብሩበት ቀን ነበር።

ይህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮችና አመራሮቻቸው በጦርነት የተማረሩበት ወቅት እንደነበር የሚተርኩት ፍሥሐ ደስታ፣ ከጀኔራሎቹም በላይ በእነመንግሥቱ ኃይለማርያም ይሁንታን ያገኘ ካድሬ ስለወታደራዊ ስትራቴጅ ለመተንተን የሚቃጣበትና ጀኔራሎቹን ያማረረበት ወቅት እንደነበር እማኝነታቸውን ይሰጣሉ። በገፈፋና በግድ ጦር ሜዳ ይቀላቀሉ የነበሩ ወታደሮች በቁርጠኝነት ይዋጋ የነበረውን ሠራዊት መንፈስ እንደቀየሩት ታሪክን የኋሊት በማስታወስ፣ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ ያሳሰባቸው የጦሩ መሪዎች ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሥልጣን ካልተወገዱ ኢትዮጵያ የገባችበት ችግር ሊፈታ እንደማይችል አመኑ፤ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሔድም እንደወጠኑ ያወጋሉ።

አዲስ አበባና አስመራም የመፈንቅለ መንግሥት መሪዎቹ ማዕከል ሆኑ። ሆኖም የአዲስ አበባው ማታ ላይ እንዲሁም አስመራው ደግሞ ከአንድ ቀን በኋላ ግንቦት 9/1981 ከሸፈ። አዲስ አበባ ውስጥ ሙከራውን ያደረጉት ጀኔራሎች ራሳቸውን ገደሉ፣ ተገደሉ፣ ታሰሩ። አስመራ ላይ ደግሞ ግንቦት 9/1981 የ102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር በምሥራቅና በሰሜን የገጠማትን ጦርነት ሲመሩ የኖሩትን ጀኔራሎች ዓይናቸውን ጎልጉሎ፤ በየጎዳናው እየጎተተ፣ አንገታቸውን ቆርጦ ወታደር በመሪዎቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ጠላት በማረካቸው ላይ ሊያደርገው በማይታሰበው አረመኔያዊ ድርጊት አስመራን የደም አበላ አደረጋት።

በአጠቃላይ በመፈንቅለ መንግሥቱ ከ137 በላይ የጦሩ አመራሮች ታሰሩ። ከእነዚህ መካከልም 28 ጀኔራሎች፣ ከ20 በላይ ኮሎኔሎች፣ ከ20 በላይ ሻለቃዎች፣ ከ20 በላይ ሻምበሎች ይገኙበታል። ገንጣይ አስገንጣይ የሚባሉት ሳይቀሩ አንዳንዶቹ “የኢትዮጵያ መንግስት ቀኝ እጁን በግራ እጁ ቆረጠ!” ሲሉ, ሌሎቹ ደግሞ “ኢትዮጵያ የጦር መሃንዲሶቿን ገደለች፣ በላች” ብለው ጽፈውታል።

ከኹለት ዓመት በኋላ ግንቦት 13/1983 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ ‘ጓድ ሊቀመንበር’ን አሞካሽቶ የማይጠግበው ኢትዮጵያ ሬዲዮ “ጦርነቱ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም። ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆም፣ ስምምነት እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የአገሪቱ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ከሥልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከሥልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጭ ሔደዋል። ፕሬዝዳንቱ ከሥልጣን በመውረድ አገር ለቀው በመሔዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዘዳንት ሌፍትናንት ጀኔራል ተስፋዬ ወልደኪዳን ተክተው ይሰራሉ” ሲል አወጀ።
ግንቦት 20/1983 ሕወሓት/ኢሕአዴግ ኢዲስ አበባን ተቆጣጠረ፤ የመንግሥት ሥልጣኑነም ተረከበ።

ግንቦት እና ምርጫ
ግንቦት 7/1997 በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ምርጫዎች በተሸለ ሁኔታ የብዙኀን ፓርቲ ምርጫ ተካሔደ። ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ነጻ ለመውጣት በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ ጣቢያ የጎረፉትም በዚህ ቀን ነው ሲሉ አልጀዚራና ቢቢሲን ጨምሮ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በምርጫው ዕለት ማታ ከግንቦት 8/1997 ጀምሮ የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ። የምርጫውን ውጤት ተከትሎ በተወሰደ መንግሥታዊ እርምጃ ብዙዎችን ለሞት፣ ለእስርና ለስደት ዳርጓል።

ግንቦት እና ፍርድ
ግንቦት 18/1999 በደርግ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የሞት ተፈረደባቸው፤ ግንቦት 24/ 2003 የሞት ፍርዱ ወደ ዕድሜ ልክ እስር ተለወጠ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here