ሰባት የእስላማዊ ባንኮች በመቋቋም ላይ ናቸው

0
756

ሰባት የሚሆኑ እስላማዊ ባንኮችን ለማቋቋም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሦስቱ መሥራች ጉባኤ አካሒደው ወደ ምዝገባ ሒደት መሔዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። ዘምዘም፣ ሂጅራ እና ነጃሺ ባንኮች ሥማቸውን መርጠው መሰረት ከያዙት መካከል ሲሆኑ ኩሽ እና ሁዳ የሚባሉ ባንኮችም በምሥረታ ሒደት ውስጥ መግባታቸው ታውቋል። በተጨማሪም ኹለት ቡድኖች ሥም ያልመረጡ ቢሆንም በተመሳሳይ ሐሳብ ተሰባስበው በመምከር ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በመመሪያ ወደ ሥራ እንዳይገባ የተከለከለው ዘምዘም ባንክ መልሶ ለመቋቋም ባደረገው ጥረት ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን መጨረሱን ያለፈው ሳምንት ማስታወቁ ይታወሳል። በአዋጅ ከወለድ ነፃ ባንክ ማቋቋም ያልተከለከለ ሲሆን ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሰረት ግን ባንኮቹ መቋቋም ሳይችሉ እንደቀሩ ለአምስት ዓመታት በዘርፉ የማማከር አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የኤክስፕሎር ሞር መሥራች አባል አህባቡ አብደላ ያሲን ተናግረዋል።

እነዚህ ባንኮች በተለያዩ አገራት የሸሪአ ባንክ፣ የሥነ ምግባር ባንክ፣ ሁሉንም የሚያሳትፍ ባንክ ወይም እስላማዊ ባንክ ተብለው በተለያየ ሥም የሚጠሩ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከወለድ ነፃ ባንክ ይባላሉ። ይህ ሥም ባንኮቹን አይገልጽም የሚሉት አህባቡ ወለድ ሳይኖረው የሸሪአ መሰረት ከሌለው ሙሉ አይሆንም ብለው እንደሚያምኑ ተናግረው ዋነው ነገር ስም ሳይሆን ሥራው መሆኑን ይናገራሉ። አክለውም በአረብኛ ሥሞችን የሚጠሩ የሸሪአ ባንኮችን ወደ አገራዊ ሥሞች መቀየር በሌላው የዓለም ክፍል እየተለመደ መምጣቱን ተናግረው ይናገራሉ።

ከወለድ ነፃ ባንኮች ሲመሰረቱ ማንኛውም ሰው አክስዮን ለመግዛት እንደሚችል የሚገልፁት አህባቡ ይህ በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት የተፈቀደ ነው ሲሉ ይናገራሉ። እንዲሁም ወደ ሥራ ሲገቡም ማንኛውም ዓይነት እምነት የሚከተሉ ግለሰቦች ወይም ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች ጭምር መገልገል የሚችሉ ሲሆን በሸሪአው ላይ የተከለከሉ ድርጊቶችን የሚያከናውኑ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦችን ግን እንደማያሳትፍ ተናግረዋል።

አሁን ያሉት ባንኮች ያልደረሱባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ያልተነካው የኢኮኖሚ አካባቢዎች በመድረስ ኢኮኖሚው ላይ እስላማዊ ባንኮቹ ሚናቸው ትልቅ ነው የሚሉት አህባቡ የመደበኛ ባንኮችን ሥራ ይቀራመታሉ ብሎ ማሰብ ግን ትክክል አይደለም ሲሉ ይናገራሉ።

ከሙስሊሙ እና ሙስሊም ካልሆነው ማኅበረሰብ የሚመሰረቱት ባንኮች በዙ የሚል ሐሳብ መነሳቱን እንደማይደግፉት የሚገልጹት አህባቡ አብደላ፣ ሁሉም ስብስቦች ይሳካላቸዋል ማለት ግን እንዳልሆነም ያብራራሉ። የተወሰነ ርቀት በተናጠል ከሔዱ በኋላ በመጣመር ጠንካራ ባንኮችን የመመስረት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ።

የባንኮቹ መምጣት ከመደበኛው የባንክ አገልግሎት እጦት በተጨማሪ በብድር የሚወሰድ ማዳበሪያ ወይም የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ጭምር ከወለድ ጋር ባለው ግንኙነት ምክንያት ሙስሊሙ መጠቀም እንደማይፈልግ ገልፀው ይህም ምርታማነት እንዲቀንስ ያበረከተው አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ ይናገራሉ።

ኤክስፕሎር ሞር በተለያዩ ጊዜዎች ባደረጋቸው ጥናት እና ምርምሮች በሚሊዮን ብሮች የሚያወጡ ግመሎች ያላቸው አርብቶ አደሮች በድርቅ ጊዜ አልሚ ምግብ እና ውሃ ገዝተው የሚጠቀሙበት 30 እና 40 ሺሕ ብር በማጣት ሚሊዮኖች እንደሚከስሩ ይናገራሉ።

አህባቡ አብደላ እሳቸው መሥራች በሆኑበት ሂጅራ ባነክ ላይ እንኳን የዲስፖራው ተሳትፎ ከጠበቁት በላይ እንደሆነ እና ይህም በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም ለዕለት ከሚልኩት ገንዘብ በተጨማሪ በፋይናንስ ሴክተሩ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ዕድል ይከፍታል ይላሉ።

የሚመሰረቱት ባንኮች ገንዘብ ከሚያስቀምጡ ደንበኞቻቸው ላይ በአመት 2.5 በመቶ ለዘካ መስጠት ግዴታ ሲሆን የብድር ቅጣትንም ለድሆች የሚሰጡ ይሆናሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here