በጉምሩክ ኮሚሽን የሞጆ ደረቅ ወደብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከስልሳ ቀናት በላይ ሳይነሱ የቆዩ ምግብ ነክ ዕቃዎችና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች የያዙ 1 ሺሕ 345 ኮንቴነሮችን ለጨረታ ሊያቀርብ እንደሆነ አስታወቀ። አስመጪዎች በተለይም የሚጣልባቸውን ቀረጥ ለመክፈል ባለመቻለቸው እና የባንክ ሰነድ ማስተላለፍ ላይ የሚደርሱ መጓተቶች ለመዘግየቱ ዋና ዋና ምክንቶች መሆናቸው ተገልጿል።
አስመጪዎች በስልሳ ቀን ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ቀረጥ እና የባንክ ዕዳዎች አጠናቀው ከፍለው እቃውን ሳያወጡ ሲቀሩ አሳማኝ ምክንያት ከሌላቸው በቀር ኮንቴይነሮችን መሥሪያ ቤቱ ለጨረታ የሚያወጣ ሲሆን በተለይም በቶሎ የሚበላሹ ምግቦች፣ ኬሚካል እና መድኀኒት ሲሆኑ ግን ያለመዘግየት ለጨረታ እንደሚወጡ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ግርባ በንቲ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
ምንም እንኳን የጉምሩክ ባለሥልጣን አስገዳጅ የታሪፍ መረጃ ስርዓትን ከተገበረ ዓመት ቢሞላውም አስመጪዎች ግን አልተገለገሉበትም። አስገዳጅ የታሪፍ መረጃ ማለት አንድ አስመጪ የሚያመጣውን ዕቃ ዝርዝር መረጃ በመያዝ በዋና መሥሪያ ቤቱ በመሔድ የሚጣለውን ቀረጥ ቀድሞ በደብዳቤ የሚሰጠው ሲሆን ኮሚሽኑ ለሚሰጠው የቀረጥ ተመን ይገደዳል። አስመጪዎችም ዕቃው ከመምጣቱ ቀድሞ የሚጣልባቸውን ቀረጥ የሚያውቁ ሲሆን ትርፍና ኪሳራቸውን ቀድሞ ለመረዳትም ያገለግላቸዋል።
ከጉምሩክ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው ግን በአንድ ዓመት ውስጥ ከ10 የማይበልጡ አስመጪዎች በአገልግሎቱ የተጠቀሙ ሲሆን አብዛኛው አስመጪ ግን ባልተጠበቀ የቀረጥ ዋጋ ያመጡትን እቃ ለመተው ይገደዳሉ።
ኮሚሽኑ ወደ ጨረታ ከመግባቱ በፊት የጤና ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ዕቃዎች ምርመራ እንደሚደረግባቸው የሞጆ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። አክለውም በኢትዮጵያ የገቢ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የቀረጥና ታክስ መዘግየት እንደሚታይ እና ይህም አስመጪውን፣ ኅብረተሰቡን እና ኮሚሽኑን እየጎዳው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አስመጪዎችም የሚያነሷቸው ችግሮች ከኮሚሽኑ ጋር የሚመሳሰሉ ሲሆኑ ከጭነት አስተላላፊዎች መዘግየት፣ የመጋዘን እጥረት እና በተለይም ምግብ እና ምግብ ነክ ዕቃዎች ሲመጡ የምግብና መድኀኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጋር የሚፈጠሩ መጉላላቶች ዋና ምክንያቶች እንደሆኑም ያክላሉ።
የላቦራቶሪ ውጤቶች ምርመራ መዘግየት እና በሚታዘዙ የምርመራ ዓይነት ብዛት እና የናሙና አወሳሰዶች ላይ የሚከሰቱ አለመስማማቶች ኮንቴይነሮች እንዳይነሱ ያደርጋሉ። አልፎ አልፎም ከላኪው የሚጓደሉ አስፈላጊ መረጃዎች እና የቀረጥ ነፃ መብት ክርክሮች ለዕቃዎች መዘግየት ምክንያት ተደርገው እንደሚቀመጡ አዲስ የሞጆ ዘይት ኮምፕሌክስ አክስዮን ማህበር ዳይሬክተር የሆኑት እዮብ ወረታው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011