የሚያበራየውን በሬ አፉን ላለማሰር

0
1109

የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄን ሠርተው ለሚያድሩ ሠራተኞች እንደ ክህደት መቁጠር አግባብ አይደለም በማለት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የቅርብ ጊዜ ንግግርን የሚተቹት ቤተልሔም ነጋሽ፥ እንዲያውም ለሠራተኞች ተመጣጣኝ ክፍያ የሚያገኙበትን አሠራር በፖሊሲ ደረጃ ቀርፆ መከታተል ያስፈልጋል ይላሉ።

 

 

“የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር፥ ደግሞ ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል ይላልና”
1ኛ ጢሞ 5፡19
“ከሕይወት ጋር በሳንቲም ተደራደርኩ፣
የበለጠ ሊከፍለኝ አልቻለም
ቢሆንም በምሽት ለመንኩ
ያለኝን መንማና ስቆጥር፤
ሕይወት ቀጣሪ ነውና
የጠየቁትን ይሰጣል፣
ደመወዝህ አንዴ ከተወሰነ
ሥራውን መሸከም አለብህ፤
ለትንሽ ደመወዝ ሠራሁ
በኋላ ልረዳ በፀፀት፣
የምጠይቀውን ያን ያህል
ሕይወት እንደሚከፍል።”
– ጄሲ ሪተንሃውስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነጋጋሪ የሚባሉ ንግግሮችን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ሐኪሞችን ሰብስበው ችግሮቻችውን በሰሙበት ስብሰባ መፍትሔ ያቀርባሉ፣ ቢያንስ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች ያመላክታሉ ተብሎ ሲታሰብ የሥራ ማቆም አድማ ድረስ የደረሰ ተቃውሞ ማስተናገዳቸው ይታወሳል። መምህራንም ከዚያ በኋላ የደመወዝ ጭማሪ እንፈልጋለን የኑሮ ጫና ከአቅማችን በላይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም የመንግሥት ተቀጣሪ መልስ በሚመስል መልኩ “መንግሥት ባዶ ካዝና እንዳለው እያወቀ ደመወዝ ጭማሪ የሚጠይቅ ኢትዮጵያዊ ነው ወይ?” የሚል ሌላ አወዛጋቢ ንግግር ጨምረውልናል። ለዚህም አባባላቸው በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ትችት አስተናግደዋል። ከባለ ብዙ ቢሊዮን ብሩ የአዲስ አበባ አረንጓዴ መናፈሻ ጋር በማነፃፀር ሳይቀር ደመወዝ መጨመር አይቻልም የሚለውን ክርክር ውሃ አያነሳምም ተብለዋል።
ገቢ ሲያድግ ፍላጎት አብሮ ያድጋል የሚባል አባባል አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግSeት ሠራተኛ ደመወዝ ቤተሰብ ማስተዳደር አስማተኝነት ነው እየተባለም ይቀለዳል። ሰው የትኛውንም ያህል ቢከፈለው በቃኝ አይልም የሚባል ነገርም አለ። እኛ ያደግንበት ጊዜ ቢርቅ፣ ሠራተኛ ሆነን በኖርንባቸው ዘመናት ከዐሥር ዓመት በፊት እንኳን የምናገኘው ደመወዝ አሁን ካለው የዋጋ መናርና የኑሮ ውድነት አንፃር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ከላይ ያሉትን አባባሎች ትክክለኝነት ለጊዜው ወደ ጎን ብንተወው ባለፉት ዓመታት እጅግ በፈጠነው የኑሮ ውድነት መናር እና ከደመወዝ ጭማሪ ጋር ጭራሽ አለመመጣጠን በሁሉም ቤት ብሶት ሲብላላ መክረሙ ግልጽ ነው። ሌላው ቢቀር የሰሞኑ መብራት መጥፋት እንኳን ከእንጀራ ጀምሮ ዳቦና ሌሎች ሸቀጦች ዋጋቸው መናር ብቻ ሳይሆን ለማግኘት አስቸጋሪ የሚሆኑበትም አዝማሚያ ታይቷል።

መንግሥት ትልቁ ቀጣሪ በመሆኑ ስለ ደመወዝ ጭማሪ ሲነሳ ቀዳሚው ተጠቃሽ ሆነ እንጂ የግሉ ዘርፍም ለሠራተኛው የሚገባውን ቢቀር በአንፃራዊ መልኩ ለመሠረታዊ ፍጆታ በቂ የሆነ ክፍያ እየከፈለ ነው ለማለት ያዳግታል።

መንግሥት በየዓመቱ ከየትምህርት ተቋማት የሚመረቀውን የሰው ኃይል የመቅጠር አቅም ጨርሶ የሌለው ከመሆኑ አንፃር ከ107 ሚሊዮን ሕዝቧ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ወጣት በሆነባት ኢትዮጵያ ተስፋው ሥራ ፈጠራና ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋት አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው። ለዚህ እንደ አንድ ምሳሌ ሊወሰድ የሚችለው መንግሥት ፖሊሲ ነድፎ፣ ሥራውን የሚመራ መሥሪያ ቤት አቋቁሞ በከፍተኛ ትኩረት እያከናወነ ያለው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪን ያካተተው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ነው። በፓርኮቹ በተለይ ከተለያዩ አገራት መጥተው ሥራ ቦታቸውን እንደ ሐዋሳ ፓርክ ባሉ ሥፍራዎች ማድረጋቸው የዚህ ፖሊሲና መንግሥት የውጪ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያደረገው ከፍጠኛ ጥረት ውጤት ነው ለማለት ይቻላል።

በተለይ ሐሳቡ በተነሳበት ወቅት የአገሪቱ መሪ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፋብሪካዎቹ ወይንም የውጪ ባለሀብቶቹ ሲገቡ ቃል የሚገባላቸው ነገር አንዱ ርካሽ የሰው ጉልበት በመሆኑ ለሠራተኞቹ የሚገባቸውን ሳይከፍሉ፣ የሥራ ሁኔታቸውንም ሳያስተካክሉ እንዳይቀሩ በሚል ዝቅተኛ ደመወዝ ክፍያ ተመን መውጣት እንዳለበት አስተያየት ተሰጥቶ ነበር። ሆኖም በወቅቱ ጊዜው ገና ነው በሚል ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል።

ነጻ ገበያ በራሱ ከተተወ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የሚገባውን ይከፍላል የሚለው በአንድ ወቅት በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ ሐሳብ አከራካሪ መሆኑ ግልጽ ነው። ይኸውም በካፒታሊዝም ለሠራተኛው የሚገባውን መክፈል ብቻ ሳይሆን የተቻለውን ዝቅተኛ ክፍያ ከፍሎ ወጪ በመቀነስ ከፍተኛ ትርፍ ማምጣት ዋና ግብ ነውና። የዓለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች በየአገራቸው የሚጣልባቸውን ዝቅተኛ የሠራተኛ ክፍያና አመቺ የሥራ ሁኔታ ቁጥጥር ፍራቻ በታዳጊ አገሮች እየሔዱ ፋብሪካዎቻቸውን መክፈታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውም ለዚህ ነው። ለምሳሌ በተለምዶ እንግሊዝ የምንላት ዩናይትድ ኪንግደም የአገሪቱ ብራንዶች እንደሆኑ የሚታወቁት ኩባንያዎች ሳይቀር በአገራቸው ምርት የሚመረቱባቸው ቦታዎች የሏቸውም። ምርቶቻቸው በባንግላዲሽ ወይም ፓኪስታን የተመረቱ ናቸው።

በኢትዮጵያ ያሉት ታላላቅ የውጪ አገር ብራንዶች በዚህ መልኩ የገቡ ሲሆኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሠሩ ሠራተኞች የሚከፍሉት ክፍያ አነስተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ እንኳን ሲ ኤን ኤን የተሰኘው የዜና አውታር ግንቦት 5 ቀን 2011 በወጣው እትሙ “ከዓለማችን ታላላቅ ታዋቂ የልብስ ብራንዶች ውስጥ ለሚጠቀሱ ሥሞች የሚሠሩት ኢትዮጵያውያን የመጨረሻውን ትንሽ ክፍያ ያገኛሉ” በሚለው ዘገባው እንዳተተው በተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በሚገኙት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የሚሠሩት ኢትዮጵያውያን ደመወዝ 750 ብር ወይም 26 የአሜሪካን ዶላር ነው። በአብዛኛው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ሠራተኞቹ ሴቶች መሆናቸውን ስናይ ደመዎዛቸው አዲስ አበባ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው ከሚሠሩ ሴቶች ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ያነሰ መሆኑን መረዳት እንችላለን። የኢንዱስትሪዎቹ ሠራተኞች የምግብና የቤት ኪራይ ወጪ ከዚችው ክፍያ እንደሚቀንሱም ሲታይ የደመወዙ አነስተኛነት ግልጽ ይሆናል።
ዘገባው ጨምሮ እንዳለው ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሠራተኛ ደመወዝ ለግሉ ዘርፍ ያላስቀመጠች ሲሆን በደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ ያሉ ሠራተኞች በወር 244 የአሜሪካን ዶላር (6100 ብር) ሲከፈላቸው በኬንያ 207 ዶላር (5796 ብር) እንደሚያገኙ አትቷል።

በኢትዮጵያ ያለውን ዝቅተኛ ክፍያ በሚመለከት ከታዋቂ ዓለም ዐቀፍ ኩባንዎች መካከል ሲኤንኤን የጠየቃቸው ተወካይ ገንዘቡ ያነሰው መንግሥት ለሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች ባወጣው ዝቅተኛ ደመወዝ ላይ መሠረት አድርጎ የተተመነ በመሆኑ ነው ብለዋል። የመንግሥት ዝቅተኛ ተመን በምን ደረጃ ለሠለጠነ ባለሙያ እንደተተመነና የሥራ ባሕሪው ከጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ሠራተኞች የሥልጠና ደረጃና አስፈላጊ ክኅሎት አንፃር ግን ጥያቄም አልቀረበም፣ ማብራራያውንም አላካተተውም።

ይህ ዓይነቱ ዜና የዓለምን ትኩረት መሳቡ ሲታወቅ መንግሥትም ለችግሩ መፍትሔ መስጠት እንዳለበት ያመነ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ አበበ አበባየሁ ኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ የደመወዝ ስኬል የምትወስንበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ክፍተቶች እንዳሉ መንግሥት መገንዘቡን የጠቀሱት ኃላፊው ያንን ክፍተት ለመሙላት ለመሥራት ወስነናል ብለዋል።

ይሄ ጥሩ መነሻ በመሆኑና በአስቸኳይ ይተገበራል ብዬ በማመን እንዲሁም በሌሎች የሥራ ዘርፎችም መንግሥት ለሲቪል ሰርቪስም ሆነ ለግል ዘርፍ ሠራተኞች በጥናት ላይ የተመሠረተ የደመወዝ አከፋፈል፣ ከሌለውም ላይ ቢሆን ቀናንሶና ሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎችን አስወግዶ መሥራት እንዳለበት በማመን የዝቅተኛ ደመወዝ መወሰን ያለውን ጥቅምና ሊፈጥር የሚችለውን ክፍተት በማተት ጽሑፌን አበቃለሁ።

በገበያ ጥናት ላይ የተመሠረተ የዝቅተኛ ደመወዝ ተመን ማውጣት በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ቤተሰቦች ከኑሮ ውድነት መጨመር ጋር አብረው እንዲጓዙና እንዳይጎዱ ያደርጋል። ገንዘብ ቢያገኙ ጥቅም ላይ ስለሚያውሉትም ወደ ኢኮኖሚው ገንዘብ እንዲገባ ለማድረግ አንድ ዘዴ ነው። ገንዘብ ያለው ኢኮኖሚ ደግሞ ተጨማሪ የሰው ኃይል ፍላጎት እንዲፈጠር በማድረግ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ሠራተኞችም የተሻለ ከፋይ ፍለጋ ከመሔድ ይልቅ አንድ የሥራ ቦታ ላይ እንዲቆዩ ሲያደርግ ለድርጅቶችም ለቅጥርና ለሥልጠና የሚያወጡትን ወጪ በመቀነስ ትርፋማነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል። ይሄም ሥራ አጥነት እንዲቀንስ፣ የደመወዝ መጠን ከፍ እንዲል በማድረግም የግብር ገቢ እንዲጨምር ያደርጋል።

ዝቅተኛ ደመወዝ ተመን ማውጣት አዎንታዊ ገጽታ ብቻ የለውም አንዳንድ ድርጅቶች ከተለመደው ክፍያ ከፍ ያል እንዲከፍሉ ሲጠየቁ በጀት ቀንሰው ሠራተኛ በማባረር ገበያ ውስጥ የመቆየት ስትራቴጂ አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። ከዚህ ሌላ በተለይ አምራች ድርጅቶች ሠራተኛው ላይ የጨመሩትን ተጨማሪ ወጪ በተጠቃሚው ላይ ዋጋ በመጨመር ለመወጣት የሚሞክሩበት ሁናቴም ሊከሰት ይችላል። ከላይ የጠቀስነው የሥራና ማምረቻ ቦታዎችን ዝቅተኛ ክፍያ ወዳለባቸው አገሮች የመውሰድ አዝማሚም ሊከሰት ይችላል።

ነገር ግን ከአሉታዊ ጎኑ ጋር አብሮ ሊነሳ የሚገባው እውነታ አብዛኞቹ ድርጅቶች የሚያጋብሱት ትርፍና ለሠራተኞቻቸው ደመወዝ የሚያወጡት ገንዘብ ልዩነት የትየለሌ መሆኑ ነው።

አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ ጓደኛዬ ባለፈው ሳምንት ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ የልብስ ሱቅ ገብታ ለባለቤቷ የሚሆን ካናቴራ (ቲ ሸርት) አየች። ዋጋውን ስትሰማ መገረም አይደለም፣ በድንጋጤ “ለቲሸርት 9500 ብር አካባቢ ተጠየቅኩ” ብላ መልዕክት ላከችልኝ። ቲ ሸርት ነው ብላ ነግራኝ እንኳን ድንጋጤዬ መለስ ሲልልኝ፣ ሸሚዝ ነው ብዬ አስቤ “የተሠራው ከምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ ነበር የመጀመሪያ ምላሼ። ሱቁ ውስጥ ተቀጥረው የሚሠሩት ልጆች ወደ ሱቁ ለመግዛት የሚመጡ ደንበኞች ዋጋውን ሲሰሙ የሚያሳዩትን ድንጋጤ ማየት የለመዱት ልጆች ስሜቷን አይተው ሲስቁ በተፈጠረ የመነጋገር አጋጣሚ እያንዳንዳቸው 3500 ብር ተከፋይ እንደሆኑ ነግረዋታል።

ስለዚህ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ወጪና ተመጣጣኝ ትርፍን የሚያገናዝብ የተሻለ ክፍያ፣ ቢያንስ መሠረታዊ ፍላጎትን አሟልቶ ከድህነት የሚሻል ኑሮ የሚያኖር ደመወዝ መጠን ሊወሰን የግድ ይላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here