አስተናጋጅ፣ እንግዳና መስተንግዶ

0
765

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ተመሳሳይ ጉዳዮችን እንደ ዓውዱ የተለያየ አድርገን የምንረዳበት አጋጣሚ አለ፤ ሁሌ ስህተት ባይሆንም አንዳንዴ ግን ትክክል ሳይሆን ይቀራል። ለምሳሌ አንዱ የመስተንግዶ ነገር ነው። አንድ ሰው “አስተናጋጅ የት ነው ያለው?” ብሎ ቢጠይቅ አስቀድሞ ሐሳባችን የሚያቀናው ወደ ምግብና መጠጥ ቤቶች አካባቢ ነው።

ይሁንና አገልግሎታቸውን ፈልገን የምናቀናባቸው የመንግሥት ተቋማትም ውስጥ መስተንግዶ አለ። በታክሲ፣ በአውቶብስ፣ በገበያ ማዕከላት፣ በመንገድ…ብቻ አንዳች አገልግሎት ለማግኘት ባቀናንበት ስፍራ ሁሉ “ምን እንታተዝ?” የሚሉን ሰዎች አሉ፤ የሚያስተናግዱን።

ታድያ በምግብና በመጠጥ ቤቶች ውስጥ ሲሆን የመስተንግዶ ነገር መልኩ ይቀየራል። በተለይ ነገሩን ከሴቶች አንጻር ስናየው አስተናጋጅነት “ማንም!” እንደፈለገ የሚያዝዝበት የርካሽ ፍላጎት ባለቤቶች መፈንጫ ተደርጎ ይወሰዳል። ነገሬም ብዙዎቻችን በቶሎ ወደ ሐሳባቸው ከሚመጣው የመስተንግዶ ዓይነት ነው።

በዚህ ከማኅበረሰቡ ጀምሮ፣ በተስተናጋጅና አስተናጋጅ በሚቀጥሩ ተቋማት ድረስ የዘለቀ ችግር አለ። አንዳንድ ተስተናጋጅ ለምግብና ለመጠጥ ብሎ በከፈለው ገንዘብና በጨመረው ጉርሻ ተጨማሪ የተለየ አገልግሎት ይጠብቃል። አልያም “እንዳሻኝ ብሆንና ባደርግ መብቴ ነው! ከፍያለሁ” በሚል እንዳመጣለት ሲሆን ይታያል።

ያም ብቻ አይደለም የምግብና የመጠጥ ቤት ባለቤቶች ከሚሰጡት አገልግሎት በላይ አስተናጋጆች ላይ ያተኩራሉ። እንደ ንግድ ሰው ትክክል ይሆናሉ፤ ዕይታቸው ግን የተበላሸ ነው። ለምሳሌ ከከተማ ወጣ ባልን ጊዜ ቀሚሳቸው ከጉልበታቸውም ሆነ ከታፋቸው እጅግ ያፈገፈገ፣ ከላይም በጠባብ ማንጠልጠያ ከገላቸው የተጣበቀ አላባሽ ያደረጉ ሴቶችን በአንዳንድ ምግብ ቤቶች እንመለከታለን።

“ይሔ አለባበስ ተመችቷችሁ ነው?” ብላችሁ ብትጠይቁ፤ ምላሹ “ባለቤቶቹ እንዲህ እንድለብስ ስለሚያዝዙን ነው” የሚል ነው። ይህ የምግብ ቤቶቹ ባለቤቶች የአስተሳሰብ ችግር ታድያ መራራውም እውነት ሲነግረን፤ የሴት አስተናጋጆች ሰውነት በአለባበስና አኳኋን በተጋለጠባቸው ቦታዎች ገበያተኛ ይበዛል ይለናል።

አንዲት ሴት አስተናጋጅ በዛ ካለ ፈገግታ ጋር፣ በጥሩ መስተንግዶ ጎንበስ ቀና ብላ ያስተናገደች እንደሆነ፤ “ምን ፈልጋ ነው?” የሚሉም አይጠፉም። ነገሩ በዚህ አያበቃም፤ በተለይም በአየር መንገድ የሚሠሩ ሴት አስተናጋጆች በተመሳሳይ ይነሳሉ። ለጥቅም ሲሉ ራሳቸውን የሚሸጡ ተደርገው ይቆጠራሉ፤ መስተንግዷቸው ከአንዳች ጥቅም ፍለጋ ጋር ተደምሮባቸዋል።
እንግዲህ ይህን ያነሳነው “አስተናጋጆች ንፁሐን ብፁዓን ናቸው» ለማለት አይደለም። ሴቶች በብዛት ይገኙበታል ተብሎ እንደሚታመን የሙያ ዘርፍ ግን፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ሊደረግ እንዲሁም ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚለውን ለማሳሰብ ነው። እንዲሁም ሴትን እንደ ሰው የሚያከብር፤ አስተናጋጅነትን እንደሙያ የሚመለከት ሰው በብዛት ስለመኖሩም ለማጠየቅ ጭምር ነው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here