ዐሥሩ የተሳሳቱ ጤና ነክ መረጃዎች

0
1081

በዘመናችን የመረጃ እጥረት አለመኖሩ እርግጥ ቢሆንም, የሚሠራጭ መረጃ ሁሉ ግን ትክክል አለመሆኑን ለማሳየት ዶክተር ሰላም ታደሰ በተለይ ከጤና ጋር በተያያዘ የሚሰራጩትን መረጃዎች ሳያጣሩ ከመጠቀም በፊት ትክክለኝነታቸው መታወቅ አለባቸው ሲሉ መታረም ያለባቸውን ልምዶች ጠቁመዋል።

 

መረጃን ማግኘት ከማንኛውን ጊዜ አሁን ቀላል ሆኗል፤ ቢሆንም ግን ብዙ ጤናን የተመለከቱ የተሳሳቱ መረጃዎች አሁንም በአገራችን ይሰማሉ። እነዚህ እምነቶችና መረጃዎች አንዳንዴ ከባሕላዊ ልምዶች ሊመነጩ ይችላሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከተሳሳተ መረዳት ሊመጡ ይችላሉ። በተለምዶ የምናምናቸውን ነገሮች መተው አስቸጋሪ ቢሆንም ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ትክክለኛውን ነገር ማወቅ ያስፈልጋል። በዚህ ጽሁፍም አንዳንዶቹን ለማረም እሞክራለሁ።

በወር አበባ ጊዜ ግንኙነት መፈጸም እርግዝናን አያስከትልም።
ይህ ብዙ ጊዜ የሚደጋገምና የሚስፋፋ መረጃ ቢሆንም በፍጹም ልክ አይደለም። አንዲት ሴት የወር አበባን ስታይ የማሕፀኗ ውስጠኛው ክፍል ተለይቶ ይወገዳል። ይህ ክፍል ሌላ ጊዜ የሚፈጠረውን እርግዝና የሚያፋፋ ነው። በወር አበባ ጊዜ የሚወገድ ቢሆንም የወንዱ ዘር በማሕፀኗ ከ3 እስከ 7 ቀን ሙሉ መቆየት ይችላል። ስለዚህ የማሕፀኑ ውስጠኛ ክፍል እንደገና ሲፈጠር አብሮ እርግዝና ሊከሰት ይችላል።

ቡናማ ስኳር ከነጭ ስኳር የበለጠ ለጤና ጠቃሚ ነው።
ነጭ ስኳር ጥቁር ስኳር ሲጣራ የሚገኝ ነው። ማለትም ጥቁር ስኳር ከነጭ ስኳር በበለጠ ፖታሲየምና ማግኒሲየምን የመሳሰሉ ንጥረ ነገሮች ይኖሩታል፤ ተጣርቶ ነጭ ስኳር ሲሆን ግን እነዚህ ንጥረ ነገሮች ይወጣሉ። ነገር ግን ኹለቱም ሰውነታችን ውስጥ ሲገቡ ወደ ግሉኮስ ይለወጣሉ። ይህ ማለት ልዩነት አይኖራቸውም ማለት ነው። ስለዚህ የጤና ባለሙያዎች ከስኳር ነጻ የሆነን አመጋገብ ሲመክሩ ወይም ሲያዙ ጥቁር ስኳርና ማር ማስወገድ ይኖርብናል።

ቀጭን ሰው የፈለገውን መብላት ይችላል።
ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው። አንድ ሰው በውጭው ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት ባይታይበትም ወይም ምንም ዓይነት የውፍረት ምልክት ባይታይበት ጤነኛ ነው ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ቀጭን ሰዎች በተለይም የስኳር በሽታ ያለባቸው ተመርምረው ከፍተኛ ኮሌስትሮል እንዳለባቸው ሊነገራቸው ይችላል። የሰውነታችን ክብደት ሳይወስነን ሁላችንም ጤናማ ምግቦችን መመገብና ጤናችንን በጥንቃቄ መከታተል አለብን። የአንድን ሰው ጤና ዝም ብለን በማየት መገመት አንችልም።
በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጡንቻ ወደ ስብ ክምችት ይቀየራል።

የስብ ሴሎች የጡንቻ ሴሎች ኹለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። አንዱ ወደ አንዱ ሊቀየር አይችልም። በቂ እንቅስቃሴ ሳይደረግ ሲቀር የጡንቻ ሴሎች መጠን ይቀንሳልና የስብ ሴሎች መጠን ይጨምራል እንጂ አንዱ ወደ አንዱ ሊለወጥ አይችልም። ይህንን ለማስቀረት በቂ ጡንቻ ገንቢ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሰውነታችን ሲቃጠል ቫዝሊን ወይም ቅቤ ወይም ዘይት መቀባት አለበት።
ይሔ በጣም ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ስህተት ነው። የተቃጠለውን አካል ዘይት፣ ቫዝሊን ወይም ቅቤ ስንቀባ ሙቀቱ ቆዳ ላይ ተይዞ እንዲቀር እናደርጋለን። የተቃጠለው አካል እንዳይቀዘቅዝና ቁስሉ እንዲብስ እናደርጋለን። ትክክለኛው አካሔድ በባለሙያ መታየት ነው። እንደ ቁስሉ ደረጃ ወይ መድኀኒት ተደርጎ በፋሻ ይሸፈናል ወይም ደግሞ አየር እንዲያገኝ ይደረጋል። ቁስሉ አነስተኛ ከሆነ ዓየር ማግኘቱ ቶሎ እንዲድን ያደርገዋል።
ሱሰኛ መሆን የራስ ምርጫ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሱስ የሚያመጣን ነገር መጠቀም በእርግጥ ሰው መርጦ የሚያደርገው ነው። ይሁንና ወደ ሱስ ደረጃ ሲደረስ ሱሰኛው የሚገፋፋው በተለያዩ ነገሮች ነው። ለምሳሌ ቤተሰብ ውስጥ ሱስ ያለበት ሰው ካለ በሱስ የመያዝ ዕድሉ ክፍ ይላል። በተጨማሪም የተለያዩ የአእምሮ ጤና ችግሮች ያሉባቸው ሰዎችም ለሱስ በጣም ተጋላጭ ይሆናሉ። ከዚያም በተጨማሪ አንዳንድ አደንዛዣ ዕጾች በሰውነታችን ውስጥ የሚፈጥሩት ፍላጎትም ሱስ እንዲቀጥል ሊያደርገው ይችላል። በመሰረቱ በሱስ የተያዘ ሰው በብዙ ነገሮች ሱሱን ለመቀጠል ሊገፋፋ ስለሚችል ሙሉ ለሙሉ የራሱ ጥፋት ነው፤ እንደሆነ ይሁን ማለት አይቻልም።

በየቀኑ ቡናን መጠጣት ጎጂ ነው።
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ የሚሉት አብዛኛውን ጊዜ ቡናን በማዘጋጀትና በመጠጣት የሚጠፋውን ጊዜ በማየት ነው። በዚያውም ቡና በተጠቃሚዎች ላይ የሚያመጣውን ሱስ እያዩ ነው። ነገር ግን አንዳንድ በቅርብ ቡና ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለተለያዩ የጤና ችግሮች መፍትሔ ወይም መከላከያ መሆኑን ያሳያሉ። ለምሳሌ ፓርኪንሰን (ሰውነትን ያለማቋረጥ የሚያንቀጠቅጥ በሽታ)፣ አልዛይመር (የመርሳት በሽታ)፣ ድባቴና አንዳንድ የስኳር በሽታ ዓይነቶች ያሉባቸው ታማሚዎች ቡናን በተወሰነ መልኩ ቢጠቀሙ ሕመማቸውን ለመከላከል እንደሚረዳላቸው የሚያመለክቱ ጥናቶች አሉ። ይሁንና ከፍተኛ የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ቡናን በጭራሽ መጠጣት የለባቸውም።

ዲዮዶራንት (ብብት ላይ የሚቀባ ጥሩ መአዛን የሚያመጣ ቅባት) መጠቀም የጡት ካንሰርን ሊያከትል ይችላል።
ይህ አስተሳሰብ ዲዮዶራንት ውስጥ ከሚገኘው የአልሙኒየም መጠን ጋር የተገናኘ ነው። አንዳንድ ሰዎች ይህ ንጥረ ነገር በቆዳ ውስጥ አልፎ ወደ ጡት ይገባል የሚል ፍርሃት አላቸው። በአሜሪካ ካንሰር ማኅበር የተሠራ ጥናት እንደሚያመለክተው ዲዮዶራንት ውስጥ ከሚገኘው አልሙኒየም 0.012 በመቶ ብቻ በቆዳ ውስጥ እንደሚያልፍ ነው። ይህ ቁጥር ከምንበላው ምግብ የሚመጣውን የአልሙኒየም መጠን ያካትታል። በጤነኛ የጡት አካል እና ካንሰር ባለበት አካል ውስጥ የሚገኘው የአልሙኒየም መጠን ተመሳሳይ ነው።

በተጎዳ አካል መራመድ ወይም መንቀሳቀስ ከቻልን ስብራት የለበትም ማለት ነው።
በአጥንት የተደገፈ አካላችንን ምንም ዓይነት ጉዳት ሲደርስበት ማንቀሳቀስ ከቻልን ያለ ችግር የመዳን ዕድላችን ክፍ ያለ ነው። አጥንታችን ቢሰበርም መገጣጠሚያዎችን የሚያያይዙ ክፍሎች (‘ሊጋመንትና ተንደን’) እንቅስቃሴ መፍጠር እንዲችል ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገር ግን አንዳንዴ ሳይታወቀን የሚጎዱ ክፍሎች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ እንቅስቃሴን ለማድረግ የሚያስችሉ ሊጋመንትና ተንደን ሊጎዱ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የሕክምና ዕርዳታ ካላገኘን የሰውነታችን አካል በትክክለኛው መልኩ ላይድን ይችላል። ይህ ደግሞ ለአካል ጉዳት ያጋልጣል።

ሴት የወር አበባ ስታይ በሙቅ ውሃ ገንዳ ሞልታ መታጠብ የለባትም።
ብዙ ከጤና ጋር የተያያዙ የተሳሳቱ እምነቶች ከኋላቸው የሆነ መረጃ አላቸው። ይሁንና ይሔንኛው ምንም ዓይነት የሚደግፈው መረጃም ሆነ ማስረጃ የለውም። የተሳሳተ መረዳት አንዳንድ ሴቶች በወር አበባ ጊዜ በሙቅ ውሃ መዘፈቅ መካንነትን ያስከትላል ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፤ ግን ይህ ምንም የሚያመጣው ጉዳት የለም። እንዲያውም ከወር አበባ ጋር የሚከሰተውን ሕመምና ድካም በሙቅ ውሃ መዘፈቅ ያስታግሳል። በመሆኑም ብዙ የጤና ባለሙያዎች በሙቅ ውሃ መዘፈቅን ሕመምን ለማስታገስ የሚመክሩት።

ዶክተር ሰላም አጠቃላይ ሐኪም ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው selamtad909@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here