ኢሳት እና ኢትዮ 360°

0
706

ላለፉት ጥቂት ሳምንታት ያዝ ለቀቅ እያለ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች መከራከሪያ ሆኖ የሰነበተው በኢሳት ጋዜጠኞች መካከል እንዲሁም በጋዜጠኞቹና በቦርዱ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ሲሆን በዚህ ሳምንት ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል። የተባረሩትና ራሳቸውን ያገለሉ ጋዜጠኞች በኅብረት ኢትዮ 3600 የሚባል የፌስቡክና የዩቲዩብ ሚዲያ መጀመራቸውን በዘመቻ መልክ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ አስታውቀዋል።

ያለመግባባቱ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ውስጥ ውስጡን የሚብላሉ ነገሮች መኖሩን ማኅበራዊ ትስስር ገፆችን የሚከታተል ሰው ሁሉ ያወቀውና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነበር። በአንድ ወገን የፈለግነውን እንዳናቀርብ አፈናና ከፍተኛ ተፅዕኖ ተፈጥሮብናል፤ በተለይ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት መሰንዘራችንን ያልወደዱት አካላት አሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

በሌላ ወገን ደግሞ ኢሳት እስካሁን በሔደበት የትግል መንገድ መቀጠል የለበትም። ኢትዮጵያ ውስጥ ይብዛም ይነስም ለውጥ መጥቷል፤ ስለዚህ እየተካሔደ ካለው ለውጥ ጋር ራሳችንን አስተካክለን ለውጡ ወደሚፈለገው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲሸጋገር ማገዝ አለብን የሚሉ አሉ። በተጨማሪም ይህ ቡድን በኢሳት ውስጥ ለተፈጠረው ልዩነት በዋና ምክንያትነት አንዳንድ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ለውጥ አልመጣም በሚል ዓይን ያወጣ አቋም ማራመዳቸው ለልዩነቱ መስፋት አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረጉን በለቀቋቸው ጽሑፎችና ባደረጓቸው ቃለ ምልልሶች አስታውቀዋል።

ይህ በኢሳት ውስጥ ያጋጠመው ልዩነት በተከታታዮቻቸውም ዘንድ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፤ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮችም ላይ በሰፊው ተንጸባርቋል።

አንዳንዶች ለታፈኑት ድምጽ ነኝ የሚል ሚዲያ እንዴት ሆኖ ነው የራሱን ጋዜጠኖች ሥራ የሚያፍነው፣ ተጽዕኖ የሚያደርሰው እና ሳንሱር የሚያደርገው ሲሉ ሞግተዋል። ይሔ አካሔድ ተቋሙ ቆሜለታለሁ ከሚለው ጋር የሚፃረር ነው ሲሉም ተችተዋል።
ሌሎቹ ኢሳት ከለውጡ ጋር መለወጥ ሲገባው አንዳንድ ጋዜጠኞች ግን ቆሞ ቀር ሆነው ወቅታዊውን ሁኔታ መረዳት አቅቷቸዋል ብለዋል። ኢሳት አሁን ሙያዊ አገልግሎት መስጠት የሚገባው ጊዜ ነው ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል።

ከኹለቱ ጎራ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱት በበኩላቸው ለእስካሁኑ ኢሳት ጉዞ እውቅና በመስጠት ከዚህ በኋላ እንደበፊቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሚዲያ እንደማይሆን ተንብየዋል፤ ወደ ተፈጥሯዊ ሞቱም በማዝገም ላይ ይገኛል ሲሉ መከፍፈሉን ለማስረጃነት አቅርበዋል። እነኚህኞቹ ኢሳትም ሆነ ኢትዮ 3600 ከእንግዲህ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቀጠል ዳገቱን ለመውጣት ትንፋሽ ያጥራቸዋልም ሲሉ ደምድመዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here